የተከራይን ጭንቀት ይፈታል

የተከራይን ጭንቀት ይፈታል

በደረሰ አስፋው

በቤት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በመጠቀም ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ በሀገሪቱ ከተሞች ይስተዋላል። በዚህም ሳቢያ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ አድርጓል። በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነትንም እያባባሰው ይገኛል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የመንግሥት አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ በሆነበት በዚህ ጊዜ አዲሱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ. ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል።

አዋጁ “የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ መንግሥት አዋጁ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት ማርቀቁን አስታውቋል። በአዋጁ መሠረት ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ተከራይ እስከ ሁለት ዓመት የመከራየት መብት አለው፡፡

አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ሆኖ በ3 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው ይህ አዋጅ የአዋጁን አፈፃፀም ለመቆጣጠር በሚቋቋም ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል በአመት አንድ ጊዜ አከራዮች አሁን የሚያከራዩበትን የገንዘብ መጠን መነሻ አድርጎ በሚያወጣው ተመን ቤት ማከራየትን የሚመራ ይሆናል፡፡ ይህም ከዚህ በፊት በአከራዮች የነበረን የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ ያስቀራል ተብሏል።

ከአውሮፓ ጀርመን፣ ከእስያ ቻይና፣ ከአፍሪካ ኬኒያ ሕጉን ለማውጣት ልምድ ተወስዶበታል የተባለለት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ አንዱን ጎድቶ ሌላውን የመጥቀም አላማ የለውም ተብሎለታል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የቤት ክራይ ዋጋ ጭማሪ ክልከላ “ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው እንዲሁም የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት” ነው ብለዋል።

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው አዋጁ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ በደላሎች የሚመራውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ሥርዓት ማስያዝ የዚህ ሕግ አላማ መሆኑን አብራርተዋል። ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ከ25 እስከ 30 በመቶ በላይ ለቤት ኪራይ ማዋል የለባቸውም ያሉት ሚኒስትሯ፣ አንድ ተከራይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይደረግበት በተከራየው ቤት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ተረጋግቶ መኖር እንዲችል አዋጁ መብት እንደሚሰጠው አስረድተዋል፡፡

አዋጁ “የተከራይን ሰቀቀን እና ጭንቀት ይፈታል” የሚል እምነት እንደተጣለበት የገለፁት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ ሕጉ አስተዳደራዊ መሆኑን ገልፀው፣ በአፈፃፀም ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩ የሚኖረው ቅጣትና ተጠያቂነትም አስተዳደራዊ እንጂ የወንጀል እንደማይሆን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች ከሚታወቁ ሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ነው፡፡ መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያየ ጥረት ቢያደርግም ከፍላጎቱ ጋር ግን መጣጣም አልቻለም።

የኪራይ ዋጋ ጭማሪን በተመለከተም በተቆጣጣሪው አካል ከሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ዓመት የፀና የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ አንድ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ አይችልም። የቤት ኪራይ ውልና ዋጋ እንደ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ መወሰን እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፣ ይህንንም የሚቆጣጠር በክልል ደረጃ የሚሰየም አካል አለው፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጉዳዩን ተቆጣጣሪው አካል እንደሚመለከተውና ወደ ፍርድ ቤት እንደማይሄድ በህጉ ተመላክቷል። ይህም የሆነው በመደበኛ የሕግ ሒደት ላይ ጫና እንዳይፈጠር በማሰብ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተናግረዋል፡፡

አዋጁ ስለቤት ኪራይ ሲያብራራ፣ ለመኖሪያ ቤት የሚያገለግል ከአንድ ክፍል ቤት ጀምሮ መሆኑን፣ ለአጭር ጊዜ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ማለትም ሆቴል፣ ሪዞርት፣ እንዲሁም አልጋ ቤቶችን እንደሚያካትትም በአዋጁ ሰፍሯል።

ተከራዩ ውሉን ማቋረጥ ቢፈልግ ከሁለት ወራት በፊት ቀድሞ ማሳወቅ እንደሚኖርበት በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ቤቱን ተከራይቶ ሲኖር የኪራይ ክፍያውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለ15 ቀናት ካሳለፈና ለሁለተኛ ጊዜ ለሰባት ቀናት ካሳለፈ፣ አከራዩ ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

አከራዩ ቤቱን ለመሸጥ ሲፈልግ ለተከራዩ የማሳወቅ ግዴታ ባይኖርበትም፣ ቤቱን የሚገዛው ግን ውሉ እንዲቀጥል ካልፈለገ ለተከራዩ የስድስት ወራት ጊዜ መስጠት እንደሚኖርበት፣ ለአዲስ ተከራይ ሲያከራይም ከዚህ በፊት ከነበረው የኪራይ ዋጋ በላይ አድርጎ ማከራየት እንደማይችል ተደንግጓል። ነገር ግን ቤቱ የሚተላለፈው በስጦታ ከሆነ የውል ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ውሉ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡

ቀደም ሲል ሲከራይ የነበረ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው የተጠናቀቀ አዲስ ቤት ያለ አገልግሎት ከስድስት ወራት በላይ እንዲቀመጥ ከተደረገ፣ አከራዩ ሊከፍል ይችላል፡፡ የነበረውን የኪራይ ገቢ ግብር ተሠልቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ የቤት ኪራይ ክፍያን በተመለከተም በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ የኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ብቻ እንዲፈጸም በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የነበሩ የአከራይ ተከራይ ውሎችን የሚያስቀር አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ ሲወጣ የነበረ ውል እስከ ቀጣዩ ሦስት ወራት ድረስ እንዲመዘገብ ይጠበቃል፡፡ ይህን አዋጅ የጣሰ አከራይና ተከራይ የወንጀል ቅጣት እንደማይጣልበት፣ ነገር ግን አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት በጸደቀው አዋጅ ላይ ከሰፈሩ አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ አዋጁ የአከራዩንና የተከራዩን መብት በማጣጣም የሚያስከብር ነው፡፡ በሁለቱ መካከል አለመግባባት ካለ በተቆጣጣሪው አካል በሚደረግ አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚቀረፍ ነው የሚሆነው፡፡

በስድሰት ክፍሎች የተዋቀሩ ሰላሳ ሁለት አንቀጾችን የያዘው አዋጅ ከመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋና የኪራይ ውል ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት የሚያበጅ ከመሆኑ ባሻገር፣ መንግሥት ከቤት ኪራይ ገቢ ሊያገኝ የሚገባው የኪራይ ግብርን በአግባቡ እንዲከፈል በማድረግ የከተሞችን ገቢ ለማሳደግ እንደሚያስችልም ተስፋ ተጥሎበታል።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን የተመለከተው የአዋጅ አንቀጽ የመኖሪያ ቤት አከራዮች በዘፈቀደ የኪራይ ዋጋ እንዳይጨምሩ ይከለክላል፡፡ አዋጁ አከራይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚችለው ተቆጣጣሪው አካል በዓመት አንድ ጊዜ ነባራዊ የኢኮኖሚውን ሁኔታና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት ሊወስን የሚችለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ “የቤት ኪራይ ውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ወይም በዚህ አዋጅ ከተፈቀደው ሁኔታ ውጪ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም” ሲል አዋጁ አስገዳጅ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡

በአዋጁ መሰረት ተቆጣጣሪ አካል ማለት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውልን እና ዋጋን እንዲቆጣጠር በክልሎች የሚሰየመው አካል ነው፡ ፡ ከዚህ በተጨማሪ አከራይ ከሁለት ወር የቤት ኪራይ በላይ ቅድመ ክፍያ መጠየቅ እንደማይችል አዋጁ ያትታል፡፡ የቤት ኪራይ ክፍያዎች በባንክ ወይም በሌላ ህጋዊ የኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንደሚፈጸም የሚደነግገው አዋጁ፤ አከራይና ተከራይ “የቤት ኪራይ ክፍያ ሰነዶችን አደራጅተው የመያዝ ግዴታ አለባቸው” ይላል፡፡

ማንኛውም የቤት ኪራይ ውል በጽሁፍ የሚደረግ ሆኖ በተቆጣጣሪው አካል መረጋገጥ እና መመዝገብ እንዳለበት አዋጁ ላይ ሰፍሯል። አክሎም ሁለቱም ወገኖች የቤት ኪራይ ውል በተፈረመ ሰላሳ ቀናት ውስጥ ውሉን አቅርበው እንዲረጋገጥ እና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ በአዋጁ መሠረት “በዚህ አንቀጽ ያልተረጋገጠ እና ያልተመዘገበ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እንዳልተደረገ ይቆጠራል፡፡” አዋጁን ተከትሎ የሚደረግ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ከሁለት ዓመት ሊያንስ እንደማይችል አዋጁ ያትታል፡፡

አዋጁ የደነገገው ሌላኛው ጉዳይ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ስለሚቋረጥበት ሂደት ነው። ማንኛውም ቤት ኪራይ ውል የኪራይ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በአከራይ እና ተከራይ ስምምነት ተከራይ ቤቱን መልቀቅ ሲፈልግ የሁለት ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይኖርበታል። አከራይ ያለማስጠንቀቂያ የቤት ኪራይ ውሉን ማቋረጥ የሚችልበት ምክንያቶች እንዳሉ በአዋጁ ላይ ተመላክቷል፡፡

ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንደኛው፤ ተከራዩ ቤቱን ያለአከራይ ፈቃድ ከመኖሪያነት ውጪ ወይም ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ከሆነ ነው፡፡ የቤት ኪራዩን በውል በተመለከተው የመክፍያ ጊዜ ለመጀመሪያ ከሆነ አስራ አምስት ቀን ካሳላፈ፤ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ 7 ቀን ካሳለፈ አከራዩ ውሉን ሊያቋርጥ እንደሚችል አዋጁ ላይ ተመልክቷል። ተከራይ በቤቱ ወስጥ የወንጀል ተግባር የሚፈጽም ወይም ቤቱን ለወንጀል መፈጸሚየ የሚጠቀምበት ከሆነ አከራይ ውሉን ሊያቋርጥ ይችላል፡፡