“ተቋሙ መድሃኒት አያመርትም፤ የአቅርቦት ስራ ነው የሚሰራው” – አቶ ዘመን ለገሰ

በገነት ደጉ

ንጋት፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ዘመን፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ትውልድ እና እድገትዎን ቢያስተዋውቁን?

አቶ ዘመን፡- የተወለድኩት ባሁኑ ሸበዲኖ ወረዳ ሞሮቾ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው። እድገቴ ደግሞ በሀገረ ሰላም ነው፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በገታማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተልኩ ሲሆን የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በአለታ ወንዶ ከፍተኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትዬ በ1998 ዓ.ም ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪዬን ከተማርኩ በኋላ እራሴን ለማሻሻል ከፋርማ የግል ኮሌጅ በዴቨሎፕመንት ማናጅመንት እንዲሁም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም በህብረተሰብ ጤና ሁለተኛ ድግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በህብረተሰብ ጤና የ3ኛ ዲግሪ /PHD/ ተማሪ ነኝ፡፡

የሥራ ህይወቴን በተመለከተ ከ2002 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል የፋርማሲ ባለሙያ እና ኃላፊ በመሆን ለዘጠኝ ወራት ያህል ያገለገልኩ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ስራ ሂደት ኃላፊ በመሆን ከስድስት ዓመት ተኩል በላይ ሰርቻለሁ፡፡

ከህዳር 18/2010 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ድርጅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር አስተባባሪ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፡- ተቋሙ የተቋቋመበት ዓላማ ምንድንነው?

አቶ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ከዚህም በፊት የመድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ፈንድ በመባል ነው የሚታወቀው፡፡ አሁን ላይ መንግስት ተቋማትን ስያሜያቸውንና አደረጃጀታቸውን እንደገና ሲያደራጅ የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ይህ ተቋም በተለያዩ ስያሜዎች እና አደረጃጀቶች ከ75 ዓመታት በላይ የመድሀኒት አቅርቦትን እና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ለህክምና እና ለጤና ተቋማት ሲያቀርብ የቆየ ተቋም ነው፡፡

ዋና ዓላማውም ለህብረተሰቡ መድሀኒቶችን እና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማቅረብ ነው፡፡ አቅርቦቱም በሁለት መልኩ ነው፡፡ ለህብረተሰብ ያለ ክፍያ የሚቀርቡ መድሀኒቶች እና በክፍያ በጤና ተቋማት የሚቀርቡ ናቸው፡፡

በነፃ ስንል ለምሳሌ የክትባት አገልግሎት መድሀኒቶችን ሕብረተሰቡ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ በክፍያ ሳይሆን በነፃ ነው የሚያገኘው።

ይህም ማለት ወጪያቸውን ሌላ ሶስተኛ ወገን ይሸፍናል ማለት እንጂ ወጪ የላቸውም ማለት ግን አይደለም፡፡ የአሜሪካው ዩኤስ ኤይድ፣ ግሎባል ፈንድ እና ዩኒሴፍ የመሳሰሉ ድርጅቶች ወጪያቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ዋና ተልዕኮው መድሀኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ማቅረብ ነው፡፡

ንጋት፡- ከመድሀኒት አቅርቦት እና ጥራት ጋር ያሉ ችግሮች እንዴት ይገለፃል?

አቶ ዘመን፡- የተቋሙ ዋናው ተልዕኮ እና ተግባር የህክምና መገልገያዎችንና መድሀኒቶችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እና ጥራታቸውን ጠብቀው በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ነው። ስለዚህም ተልዕኳችን ላይ ጥራት የሚለው በግልፅ የተቀመጠ ነው፡፡

ተቋሙ መድሀኒት አያመርትም፡፡ የአቅርቦቱን ስራ ነው የሚሰራው፡፡ ከ85 በመቶ በላይ ያሉት መድሀኒቶች አሁን ባለው ሁኔታ ከሀገር ውጪ ነው የሚገቡት፡፡ የሀገራችን የመድሀኒት ምርት ገና የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡

ስለዚህ አቅርቦቱን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን የአቅርቦት ሰንሰለቱ ብዙ ባለድርሻ አካላት ያሉት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከሚፈልገው አንፃር አቅርቦቱን ለማሻሻል ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡

ተቋሙ ይህንን ችግር ለመፍታት ብዙ የለውጥ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አቅርቦት ስንል መድሀኒቱ ከተመረተበት ህብረተሰቡ ጋር እስኪደርስ ድረስ ያለውን ሰንሰለት የሚይዝ ሲሆን ተቋማችን አንዱ የሰንሰለቱ አካል ነው እንጂ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለውን ሙሉ በሙሉ እርሱ አይደለም የሚመራው፡፡

ለምሳሌ ከሀገር ውጪ መድሀኒት ሲገባ የብሔራዊ ባንክ፣ የሎጂስቲክ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህም በተጨማሪ የባህር ሎጂስቲክ አገልግሎት እንዲሁም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የራሱ ሚና ያለው ሲሆን የጤና ተቋማትም የራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ ሰንሰለቱም እነዚህን ባለድርሻ አካላትን የያዘ ነው፡፡

ንጋት፡- የመድኃኒት ፍላጐትን ለማሟላት የተሰሩ የለውጥ ሥራዎችስ ምን ይመስላሉ?

አቶ ዘመን፡- እንደሚታወቀው የመድሀኒት አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህም የሚሆን የለውጥ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ለውጡ በቅንጅት ተሰርቶ ይፋ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የመንግስት ተቋም የተሰጠውን ተልዕኮ መሸከም የሚችል አደረጃጀት እንዲኖረው መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ወይም ቢፕአር ከዚህም በፊት በተቋሙ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በዚህም ብዙ መሻሻሎች ታይተዋል፤ ሆኖም ግን ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ያህል ሙሉ ለሙሉ ችግሮች የሉም ማለት እንዳልሆነ ልንረዳው ይገባል፡፡ የጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የኳሊቲ ማናጅመንት ሲስተም የጥራት አመራር ስራዎችን በመዘርጋት አይሶ 9 ሺ1/2015 የሚባለውን ሰርተፊኬት የያዘ ተቋም ነው፡፡

ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት የአዳማ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ አይሶ ሰርቲፋይድ የሆኑ ተቋም ናቸው፡፡

ይህ ማለት አንድ ተቋም 174 የዓለም ሀገራት አንድ ስራ እንዴት መመራት አለበት የሚለውን የአሰራር ስርዓት ደረጃ አለ፡፡ ያን ደረጃ አሟልቶ እውቅና አግኝቷል ማለት ነው። በዚህም ላይ ያሉትን ብዙ መሰፈርቶችን አሟልቶ ነው እውቅና ያገኘው፡፡

ሌላው በመድሀኒት አቅርቦት አንዱ የካይዘን ፍልስፍና ሲሆን ብክነትን ለመከላከል የካይዘንን ትግበራ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጪ ተወዳዳሪ ሆኖ የአፍሪካን የ2021 የካይዘን ፍልስፍና አሸናፊ የሆነ ተቋም ነው፡፡

በሀገራችን ማንኛውም ዕቃ የሚገዙበት እና መድሀኒት የሚገዛበት ስርዓት አንድ ነው፡፡ ይህም በቀጣይም የግዥ ስርዓቱ የሚስተካከል ይሆናል፡፡

የዓለም ዓቀፍ ጫናው በራሱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአብዛኛው መድሀኒት የሚገዛው ከውጪ በመሆኑ ምክንያት ተደማሪ ጫናዎች እንደነበሩ ሆነው ግን አቅርቦቱ ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የዓለም ዓቀፉ ሁኔታዎች ተጽዕኖ አሳርፈዋል፡፡

ንጋት፡- በተቋሙ አሰራርን የማዘመን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምን ይመስላል?

አቶ ዘመን፡- ለአንድ ተቋም ቴክኖሎጂ መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ በተቋሙ ብዙ የተሰሩ ስራዎች ያሉትን ያህል አሁንም ብዙ ትግል ላይ ያሉ ስራዎችም አሉ፡፡

ለአብነትም ተሽከርካሪዎቻችን ላይ ጂፒኤስ በመግጠም መድሃኒት ጭነው ወደሚፈለገው ቦታ ሄደዋል ወይ? የሚለውን መቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡

ተቋሙም ደህንነቱ መጠበቅ ስላለበት የመድሀኒት ክምችት አካባቢዎች ላይ ለ24 ሰዓት የሚሰሩ የደህንነት ካሜራዎች ተገጥሞላቸዋል፡፡ ኢንትሮጂን ዲቴክተር የሚባሉ ቴክኖሎጂዎች ወደ መድሀኒት መጋዘን ሰዎች የሚጠጉ ከሆነ አላርም ሴንሰር ያለው እና እሳት አደጋ አላርም ያለው ሲሆን በአጠቃላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ስንጠቀም ቆይተናል።

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙን ለመለወጥ ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒግ ሲስተም በተቋሙ አለ፡፡ ይህም ሲስተም ሙሉ ለሙሉ የተቋሙን የአሰራር ሲስተም ዲጅታላይዝ አድርጎታል፡፡ በዚህም የመድሀኒት አመራር ስርዓታችን፣ በሰው ሀብት ቅጥር እስከ ጡረታ ያለውን እና ፋይናንስ አሰራር ስርዓታችን ዲጂታላይዝድ ተደርጓል፡፡

እነዚህ ሶፍትዌሮች በአንድ ተናበው ኢንተርፕራይዝ ሶርስ ፕላኒግ የሚባለውን በዓለም ላይ ትላልቅ ተቋማት የሚጠቀሙት ሶፍትዌር ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ስራዎች ሲሰሩ ቆይቶ የመጨረሻ ትግበራ ምዕራፍ ላይ ተደርሶበታል፡፡

ንጋት፡- ተቋሙ ከተደራሽነት አንፃር ምን እየሰራ ነው?

አቶ ዘመን፡- ተቋሙ የፌዴራል መንግስት ተቋም ነው፡፡ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ፣ ሲዳማ ክልል አጎራባች ላይ ያሉትን የኦሮሚያ እንዲሁም የደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ይህን ስንል መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር 19 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች አሉት፡፡ እኔ የደቡብ ክላስተር አስተባባሪ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ ደቡብ ክላስተር ውስጥ አርባምንጭ እና ቦረና እራሳቸውን የቻሉ ስራ አስኪያጅ ያላቸው ቅርንጫፍ ናቸው፡፡

ስለዚህም ከተደራሽነት አንፃር ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ተደራሽ ለማድረግ ቅርንጫፎችን ማብዛት ብቻ ሳይሆን አቅማቸውን በማጎልበት ወደ ህብረተሰቡ በማድረስ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በፊት በነበረን አሰራር የጤና ፕሮግራሞችን መድሀኒት ለዞን፣ ወረዳና ለጤና ጣቢያዎች ይሰጥ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ዞኖችና ወረዳዎች በአሰራር ሂደት ምንም ዓይነት እሴት አይጨምሩም፡፡

ወረዳ እና ዞን ላይ የክትባት አገልግሎት አይሰጥም፡፡ ስለዚህም መድሀኒቱ በቀጥታ ከእኛጋር ወጥቶ ለጤና ተቋም በቀጥታ ማድረስ ነው፡፡ ከዚህም አንፃር ሲዳማ ላይ 165 የጤና ተቋማት በቀጥታ ከእኛ ተቋም ነው መድሀኒት የሚያገኙት፡፡

የሀዋሳ ማዕከል የግል ተቋማትን ጨምሮ 815 ደንበኞች አሉት፡፡ ለ444 የጤና ተቋማት ነው የሚሰጠው። ይህም ማለት ተደራሽ ከማድረግ አንፃር እሴት የማይጨምሩትን ተቋማት ከሰንሰለቱ በማውጣት በቀጥታ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ነው፡፡ ከጤና ተቋም አንፃር ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም፡ ፡ ምክንያቱም ነፃ ስለሆነ። በግዥ የሚቀርቡ መድሀኒቶች አንፃር ግን የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ በቀጣይ መሰራት ያለባቸው ቀሪ ስራዎች አሉ፡፡

በግዥ የሚወጡ መድሀኒቶችን የጤና ተቋማት ክፍያ ፈፅመው ነው መውሰድ ያለባቸው፡፡ ግዥ ላይ በዱቤ የሰጠናቸው መድሀኒቶች ክፍያ በአግባቡ ተመላሽ አይደረግም፡፡ እንደ ሀዋሳ ቅርንጫፍ ከ120 ሚሊየን ብር እንደ ደቡብ ክላስተር ደግሞ 165 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብሳቢ ገንዘብ የጤና ተቋማት አለባቸው፡፡

ተቋሙ በመንግስት በጀት ተበጅቶለት የሚንቀሳቀስ ተቋም አይደለም፡፡ በራሱ በሚያገኘው ገቢ ነው የሚተዳደረው፡፡ ከዚህም አንፃር መድሀኒቱ እዚህ እያለ ዕዳ ስላለባቸው ብቻ መጥተው የማይገዙ ተቋማት አሉ፡፡ ችግሮቹ የተወሳሰቡ ናቸው፡፡

የጤና ፕሮግራም መድሀኒቶች የምንላቸው የወባ፣ ቲቪ እና የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒቶች ደግሞ በስፋት ብክነቶች አሉባቸው፡፡ በየቦታው ወጥተው ሲሸጡ ደግሞ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህም ማለት ህገ- ወጥ መድሀኒት ዝውውር አለ ማለት ነው፡፡ በዚህም በየቦታው የአሰራር ክፍተት እና ብክነት ያለ ሲሆን ይህንንም በአሰራር መዝጋት ስላለብን በሲዳማ ክልል በልዩ ሁኔታ የፖለቲካ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

ንጋት፡- ተቋሙ ከአቻ ተቋማት ጋር ያለው ትስስር እንዴት ይገለፃል?

አቶ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት 19 ቅርንጫፎች ያሉት የፌዴራል ተቋም ነው፡፡ ይህንን ተቋም በቀጣይ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ተልዕኮ ያለው ነው፡፡ ይህም ማለት ሌሎች መስሪያ ቤቶች መጥተው የሚማሩበት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ስለዚህም ተቋማዊ ባህላችን አንዳችን ከአንዳችን መማር ነው፡፡ ለዓብነት በ2011 ዓ.ም የአዳማው ቅርንጫፍ የልህቀት ማዕከል ሴንተር ኦፍ ኤክስለንሲ ተብሎ የውጪ አማካሪ ተቀጥሮለት በመስራት ውጤት አምጥቷል፡፡

ይህም ተቋም ምንም ዓይነት አማካሪ ሳያስፈልገው ወደ ተቋሙ በመሄድ ከእህት ተቋም ጋር ተሞክሮ በመውሰድ አሻሽሎ ውጤት ያመጣበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡

ሌላው በራሳችን በመስራት በድሮኖች በመጠቀም መድሃኒቶችን ለጤና ተቋማት ለማድረስ ስራዎች ተሰርተው ተጠናቀዋል። ያለው የስራ ባህልም ጤናማ የሆነ የፉክክር መንፈስ ከሌላውም ለመማር እና እራሳችንም ለማስተማር የገነባነው የተቋም ባህል ነው፡፡

ንጋት፡- ተቋሙ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ድርሻው ምንድነው?

አቶ ዘመን፡- ተቋሙ በዋናነት ከሚሰራባቸው ተግባራት መካከል ኢመርጀንሲ /ድንገተኛ አደጋ/ ዋናው ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ፈጣን ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የተፈጥሮ አደጋ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ነው ሲሰራ የቆየው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ጤና ቢሮዎች አደጋዎች ተከስተዋል በሚሉበት ወቅት ፈጣን ምላሽ እንሰጣለን፡፡

ተቋማችን አደጋዎች ሲከሰቱ በሚቀርበው ጥያቄ መነሻ መሰረት በራሳችን ተሽከርካሪ እስከ ቦታው ድረስ ነው መድሃኒቶች እና የህክምና ቁሳቁሶችን የምንወስደው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ሀዋሳ ቅርንጫፍ ሙሉ ለሙሉ የሲዳማ ክልል፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ግማሽ፣ ጌዴኦ ሙሉ ለሙሉ እና ከማዕከላዊ ክልል የም ዞን ሲቀር ሁሉም እና ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ፣ ሻሸመኔ ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ቦረና እና ጉጂ አገልግሎቱን እዚሁ ነው የሚያገኙት፡፡

አጠቃላይ የሀዋሳው ቅርንጫፍ ለ815 ለመንግስት እና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡

ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?

አቶ ዘመን፡- የህብረተሰባችን የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት አንዱ ሌላው ላይ ጣት መቀሳሰሩ ምንም ፋይዳ አለመኖሩን ተረድቶ ሁሉም በሰንሰለቱ ውስጥ ያለው ባለድርሻ አካላት ጥረት በማድረግ በጋራ ሊሰሩ ይገባል የሚለው መልዕክቴ ነው፡፡

በተለይም ጤና ተቋማት በጀት መድበው ከእኛ ተቋም መድሀኒት በመግዛት አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ በማድረስ ተልዕኳቸው ጉልህ በመሆኑ ያለባቸውን ዕዳ ከፍለው ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ዘመን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡