“ቅል ራስ”
በይበልጣል ጫኔ
የአራተኛ ክፍል ስዕል አስተማሪዬን አገኘኋቸው። አርጅተዋል። ግን ደግሞ አልረሱኝም። ታክሲ እየጠበቁ ነበር በድንገት ያየኋቸው። ከኤሊ ትንሽ ከፍ የምትል ሞተሬን ፊትለፊታቸው አቁሜ፦
“ወዴት እየሄዱ ነው?÷ እኔ ልሸኝዎት እችላለሁ” አልኳቸው። ቀና ብለው ተመለከቱኝና፦
“እ … አጅሬው÷ አንተ ነህ እንዴ?” ብለው÷ ሞተሬ ላይ ተፈናጠጡ።
የማስታወስ ችሎታቸው ይገርማል። ሳንተያይ ሃያ ዓመታት ነጉደዋል። ሲያውቁኝ ህፃን ነበርኩ÷ አሁን ትልቅ ሰው ሆኛለሁ። ሳውቃቸው ጎልማሳ ነበሩ÷ አሁን አርጅተዋል። ሆኖም አልረሱኝም።
እኔን ከማስታወሳቸው በላይ የገረመኝ÷ በዚያ ጊዜ ተጣልተን እንደነበር አለመርሳታቸው ነው። በእርግጥ በዚያ ጊዜ÷ ፊቴ ላይ የፈነዳ ጥፊ መተውኝ ስለነበር÷ እኔ ባልረሳቸው እውነት አለኝ። ከነ ተረቱስ “የወጋ ቢረሳ …”÷ አይደል የሚባል÷ እሳቸው ግን እኔን ላለመርሳት ምክንያት ያላቸው አልመሰለኝም ነበር። የሆነው እንዲህ ነበር፦
መሰረታዊ የስዕል አሳሳል ጥበቦችን በሚመለከት ጥቂት ቀናት ካስተማሩን በኋላ÷ ስዕል እንድንስል አዘዙን። እንዲሳል የፈለጉት ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስ ምስል ነበር። ስዕሉን ከመጀመራችን በፊት ስለአፄው በታሪክ ያነበቡትን ነግረውናል። ከዚህም በተጨማሪ ኮስተር ያለ ባለሹሩባ መሆኑን ፊት ለፊታችን በሰቀሉት ባለቀለም ስዕል አሳይተውናል። ከዚህ በኋላ ነው፦
“እኔ ካስተማርኳችሁም ይሁን በተለያየ አጋጣሚ ከሰማችሁት÷ ንጉሱን ይገልፃል ብላችሁ የምታስቡትን የፈጠራ ሃሳብ ጨምራችሁ ሳሉ። አስር ማርክ አለው” ብለው÷ ፊትለፊታቸው ያለ ሰፊ ጠረጴዛ ላይ ክንዳቸውን ተንተርሰው አረፍ አሉ። በዚያው እንቅልፍ ወሰዳቸው።
ከቆይታ በኋላ የተማሪው ጫጫታ ከፍ ሲል ነቁ። ተነስተው ወደ’ኛ መራመድ ሲጀምሩ÷ ክፍሉ ፀጥ አለ። በበሩ ባለው ግድግዳ በኩል ወደ መጀመሪያው ወንበር ተራመዱ። አፄ ቴዎድሮስን ከመሳል ይልቅ÷ ሽጉጣቸውን መጠጣት የሚቀለው ጓደኛችን የሚቀመጠው እዛጋ ነው። ወደእሱ እየቀረቡ መሆናቸውን አውቆ ስዕሉን ለመደበቅ ሞከረ። ግን አልተሳካለትም። አጠገቡ ደርሰው ነበር። ስዕሉን ተቀብለው እየተመለከቱ፦
“ልጆች አፄ ቴዎድሮስ ራስ ላይ ያለው ምንድነው?” አሉ። በአንድ አፍ መለስንላቸው፦
“ሹሩባ!”
“ታድያ ይኼ ምኑ ነው ሹሩባ የሚመስለው?” ብለው÷ የጓደኛችንን ስዕል ከፍ አድርገው አሳዩን። እውነትም ምኑም ሹሩባ አይመስልም። ለነገሩ እሳቸው ለይተው ሹሩባውን ብቻ ጠቀሱ እንጂ÷ ሙሉ ስዕሉ ቴዎድሮስን ቀርቶ ሰው አይመስልም ነበር። ፀጉራቸው ደግሞ ከሹሩባ ጉንጉንነት ለቀንድነት ይቀርባል። የሆነ ብዙ ቀንድ ያለው መልከ ጥፉ አይነት ሰው።
እዚህ ጓደኛችን ላይ መብረቅ የሆነ ኩርኩም አውርደውበት÷ ወደሚቀጥለው ተማሪ ተሸጋገሩ።
ቀጣዩ ስዕል ንጉሱን ባይመስል እንኳን ሰው ይመስላል። ግን ደግሞ ፈገግም ኮስተርም ማለቱ አያስታውቅም። ወረቀቱን ወደ አይናቸው ቀረብ አድርገው ከመረመሩት በኋላ፦
“ምንም አይልም። ግን ደግሞ ስሜት የለውም። አፄ ቴዎድሮስ ኮስተር ያሉ ንጉስ ናቸው። የሳቸው ስዕል ሲሰራ÷ ኮስተር ተደርጎ መሆን አለበት” ብለው ወደሚቀጥለው ተማሪ ሊያልፉ ሲሉ፦
“ቲቸር÷ ንጉሱ ብዙ ጊዜ ቢኮሳተሩም አንዳንድ ጊዜ ፈገግ ሊሉ ይችላሉ። ለዚያ ነው ግንባራቸው ላይ መኮሳተር ያልጨመርኩበት” አላቸው። መምህሩ ትንሽ ፈገግ ብለው እርምጃቸውን ቀጠሉ።
ተማሪዎቹ የሰሯቸውን ስዕሎች እያዩ÷ በአንዳንዱ እየተገረሙ÷ ለአንዳንዱ ደግሞ ኩርኩም እየሸለሙ እኔ የተቀመጥኩበት ሥፍራ ደረሱ።
እኔ መጀመሪያም ስዕል እወድ ስለነበር÷ የተሰጠንን የክፍል ሥራ ለመስራት አልተቸገርኩም። እንዲያውም ከዚያኛው ጥግ ማየት ስለጀመሩ መምህሩ እኔ ጋ እስኪደርሱ÷ ስዕሌን ሳሰማምር ቆየሁ። ተራዬ ደርሶ ስዕሌን አዩት። ያዩት ነገር ግራ አጋብቷቸዋል። አንዴ ቀረብ÷ አንዴ ራቅ እያደረጉ ከመረመሩት በኋላ÷ ስዕሌን ለተማሪዎቹ እያሳዩ፦
“ና እስኪ የስዕሉን ሃሳብ ንገረን” አሉ። ፈጠን ብዬ ተማሪዎቹ ፊት ቆሜ÷ ስለ ስዕሉ ማውራት ጀመርኩ፦
“እኔ የሳልኩት ከተለመደው የንጉሱ ስዕል ትንሽ ወጣ አድርጌ ነው። እንደምታዩት ንጉሱ ዙፋን ላይ ተቀምጠዋል። ዙፋን የንግስና ምልክት ስለሆነ ነው የተጠቀምኩት። እዚህ ጋ ደግሞ ንጉሱ አጠገብ÷ በግራና በቀኝ ሰዎች አሉ። እነሱ ደግሞ በዚያ ዘመን የነበረውን ህዝብ ይወክላሉ። እንደምታዩት የንጉሱ ጭንቅላት ትልቅ ነው። የሰዎቹ ጭንቅላት ደግሞ ትናንሽ ነው። አባቴ ሲል እንደሰማሁት÷ ንጉሱ ዘመናቸውን የቀደሙ መሪ ነበሩ። የዘመናቸው ሰዎች ደግሞ አይረዷቸውም ነበር። እሱን ለመግለፅ ነው÷ ጭንቅላታቸውን ትልቅ እና ትንሽ ያደረግኩት” አልኳቸው።
መምህሩ በጣም ደስ አላቸው። ሦስት ጊዜ ደጋግመው አስጨበጨቡልኝ። ቀጠል አድርገው፦
“ሥዕሉ ያልከውን ሁሉ ሃሳብ የሚገልፅ ባይሆንም÷ ሃሳብህ ግሩም ነው” አሉኝ። አያይዘውም÷ በኛ ዕድሜ የተባለውን ስዕል መሳል ቀላል እንዳልሆነና ተሰጥኦ እንዳለን ወይም እንደሌለን ለመለየት÷ እንዲሁም በአጋጣሚው ስለንጉሱ የነገሩንን እንዳንረሳ ፈልገው ሥዕሉን እንዳሳሉን ነገሩን። ከክፍል ሊወጡ ሲሉም÷ ሁላችንም ለራሳችን እንድናጨበጭብ ስላደረጉን ደስ አለን።
ዓመቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው÷ እኚሁ የስዕል አስተማሪያችን አንድ ትዕዛዝ ሰጡን። የፈለግነውን መምህር ስዕል እንድንሰራ ነበር ትዕዛዙ።
አንዳንዱ ተማሪ ገራፊ መምህራንን ከነአለንጋቸው፣ አንዳንዱ ጎበዝ መምህራንን ከነመፅሐፋቸው ሳለ። በአጭር ጊዜ ስዕልን በደንብ መረዳት የቻለው ጓደኛዬ÷ ስፖርት አስተማሪያችንን ኳስ አስይዞ ስሏቸው በጣም ተደነቀ። ከሩቅ ሆነው ወደኔ እያዩ፦
“አንተስ ማንን ነው የምትስለው?” ሲሉኝ፦
“ርዕሰ መምህራችንን” አልኳቸው።
በዚያች ቅፅበት÷ ርዕሰ መምህሩ በክፍላችን በኩል እያለፉ ነበር። ስዕል አስተማሪያችን ርዕሰ መምህሩን ጋብዘዋቸው ክፍል ገብተዋል። በተማሪ የተሰራ ስዕላቸውን እንዲያዩ። ይኼንን ቀና ብዬ ያላየሁት እኔ÷ አቀርቅሬ ስዕሌን ለመጨረስ እጣደፋለሁ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ÷ ስዕሌን ጨርሼ ቀና ስል ስዕል አስተማሪዬ እና ርዕሠ መምህሩ አጠገቤ ደርሰዋል። በደመ ነፍስ ወረቀቱን አንስቼ ሰጠኋቸው። ሁለቱም ወረቀቱን አይተው ተፋጠጡ። እኔ ደግሞ የምገባበት ቸገረኝ።
ርዕሰ መምህራችን አጠር ያለ ቁመት ያላቸው÷ ወፍራም ሰው ነበሩ። ጥቁር ሙሉ ልብስ በነጭ ሸሚዝ መልበስ ያዘወትራሉ። ያገኙትን ተማሪ ሁሉ “ቅል ራስ” እያሉ መሳደብ ለምዶባቸዋል። ኋላ ላይ ስሰማ÷ ሲናደዱ መምህራኑን ሁሉ “ቅል ራስ” ማለት ይቀናቸው ነበር።
ጥቁር ሙሉ ልብስ የለበሰ አጭር ሰውዬ ከሳልኩ በኋላ÷ በጭንቅላቱ ቦታ ከአንገቱ ላይ የሚመዘዝ ሀረግ ሰርቼ ቅል አንጠለጠልኩበት። ይኼንን ስዕል አይተው ነው የስዕል መምህሬ እና ርዕሰ መምህሩ የተፋጠጡት።
ከብዙ መፋጠጥ እና ዝምታ በኋላ÷ መምህሬ ነጎድጓዳማ እና ብልጭታ የተቀላቀለበት ጥፊ ፊቴ ላይ አሳረፉ። የዚያን ጊዜ ባለኝ መረዳት ሳስበው÷ የዚያ ጥፊ ድምፅ ሱዳን ድረስ የሚሰማ ይመስለኛል። ያ ከግድያ የማይተናነስ ጥፊያቸው አልበቃ ብሎ÷ከትምህርት ቤት ተባረርኩ። ይኸው ከዚያ ጊዜ ወዲህ ስዕል እርም ብዬ ተውኩ።
በነገራችን ላይ ሁነኛ ታሪክ መዝጋቢ ባለመኖሩ እንጂ÷ መምህሬ ራሳቸውን ለመታደግ የፈፀሙብኝ ክህደት÷ ከይሁዳ ቀጥሎ በምድር ላይ የተፈፀመ ታላቁ ክህደት ተብሎ መመዝገብ ነበረበት።
ዛሬ በድንገት ካገኘኋቸው የስዕል መምህሬ ጋር ይኼንን ሁሉ አወጋን። በዚያ ምክንያት ስዕል ማቆሜን ሲሰሙ አዘኑ። ጥቂት አሰብ አድርገውም፦
“ያኔ እኮ የእንጀራዬ ነገር አሳስቦኝ እንጂ ልክ ነበርክ። ልክ ነህ ማለት ግን አልችልም ነበር” አሉኝ።
ይገርማል። ብዙዎቻችን አንድ የሆነ ቦታ ላይ ልክ የሆነን ነገር እንዳልሆነ አስቆጥረን፣ ነጩን ጥቁር ብለን፣ በሰዎች ትላንትና ላይ ተረማምደን እዚህ ደርሰን ይሆናል። “ልክ ነበርክ” ለማለት ግን እናረፍዳለን። ልክ እንደኔ የስዕል መምህር።
ይኸው በ’ሳቸው ምክንያት÷ ሰዓሊ መሆን የነበረብኝ ሰውዬ መካኒክ ሆንኩ።
“እዩት ያን ግንበኛ …
ሙዚቀኛ ሆኖ ኑሮውን ሲገፋ፣
ዋሽንት እየመታ ክራር እየነፋ”
ያለው ገጣሚ ማን ነበር?÷ ማንም ይሁን … ይኼ ግጥም የተፃፈለት ሰው ግን እኔ ነኝ። ብሩሼን ጥዬ መፍቻ ያነሳሁ።
ከመምህሬ ጋር ከመለያየታችን በፊት ይህን አልኳቸው፦
“ያኔ እርሶ ልክ ነበሩ። ዛሬ እኔም ስጎለምስ ፈሪ ሆኛለሁ። ያ ባይሆንማ÷ በስዕልም ባይሆን በቃል÷ ስንት “ቅል ራስ” የምለው ሰው ነበረኝ”
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው