ትዝታን በግጥም

ትዝታን በግጥም

በአንዱዓለም ሰለሞን

በልጅነቴ አባቴ የታዋቂ ሰዎችን ጥቅሶችና አባባሎች የሚሰበስብበት ደብተር ላይ ያነበብኩት አንድ አባባል ሁሌም ሳስበው ይገርመኛል፤ እንዲህ ይላል፡-

“ሰው ማርጀቱን የሚያውቀው በተስፋ ፈንታ በትዝታ መኖር ሲጀምር ነው፡፡”

እንግዲህ እኔም አረጀሁ መሰል፣ ዛሬ ስለ ትዝታ ላወጋችሁ ነው፤ ስለ ትዝታ በተከተቡ የስንኝ ቋጠሮዎች፡፡

እነሆ ከዕለታት ስራ በፈታሁበት አንድ ቀን አመሻሽ፣ ከቤት ውጪ ዱካ ላይ ቁጭ ብዬ፣ ባለ ኮብል ስቶኑ ንጣፍ መንገድ ላይ ኳስ የሚጫወቱ ህጻናትን እያየሁ ነበር። ለስሙ በእጄ አንድ መጽሀፍ የያዝኩ ቢሆንም ትኩረቴ ከመጽሀፉ ይልቅ የልጄ እና የጓደኞቹ ጨዋታ ላይ ነበር፡፡

በእነርሱ ልጅነት ውስጥ የእድሜዬን መንጎድ እያሰብኩ፣ የኖርኩትን ህይወት በእድሜዬ ሚዛን እየመዘንኩ ብሎም ያለፈ የልጅነት ትዝታዬን እያሰብኩ ተቀምጫለሁ፡፡

ድንገት አንድ ሙዚቃ ከሩቅ የሰማሁ መሰለኝ፤ ልክ እንደ ዋሽንት ዜማ በንፋስ እየተገፋ እንደሚመጣ፣ እንደ ሩቅ ምስራቅ ሙዚቃ ዓይነት፣ መሳጭ፡፡ …

“ገና ልናይ ብዙ ዓለም፣

አርጅተናል አንልም፡፡

ደስታ ሳይለየን፣ ስቀን በየለቱ፣

እኖራለን ገና እንደ ቸርነቱ፡፡

ካብራካችን ከፍሎ ሰጥቶናል መጽናኛ፣

ልጆቻችን ካሉ አናረጅም እኛ፡፡”

እውነቱን ለመናገር ሙዚቃው ከውስጤ ያደመጥኩት ይሁን ከርቀት የሰማሁት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምናልባት የእድሜዬ ሚዛን የኖርኩትን ህይወት ከተግባሬ አንጻር መዝኖ፣ ከወጪ ቀሪ ያሳየኝ “ያልተኖረ ዘመን” በዝቶብኝ፣ ተሳቅቄ ራሴን ለመደለል ስል ያሰብኩት ሀሳብ ጆሮዬ ላይ አቃጭሎብኝ ይሆንን? አላውቅም፡፡ …

ብቻ ግን እንዳልኳችሁ ልጆቹን እያየሁ በሀሳብ ርቄ ሄጄ፣ በትዝታ ነጉጃለሁ፤ ልጅነቴን እያሰብኩ፣ የወጣትነት ዘመኔን እየከለስኩ፣ ወደ ትናንት ተመልሻለሁ፡-

ዕድሜ ይስጠው ለዕድሜ፣ ዕድሜ ይስጠው በጣም፣

የሚያበላው ቢያጣ ትዝታ አያሳጣም!

ያለው ገጣሚ ማን ነበር? … ይህን ግጥም ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩ ዕለት እንዴት እንደተደመምኩ፡፡ የአንዳንድ ሰው ነገር ግን ይገርማል፤ ሰው እንዴት በሁለት ስንኞች ብዙ ብዙ አንቀፆችን ይጽፋል? ብቻ በአጭሩ፣ ግጥሙ ምናለ ገጣሚ በሆንኩ ካስባሉኝ የስንኝ ቋጠሮዎች አንዱ ነው፡፡

የዛሬው ወጌ የሚያተኩረው በትዝታ ዙሪያ በሚያጠነጥኑ ግጥሞች ላይ ነው ብያችሁ የለ፤ ይህን ብዬ ቀጣዩን ግጥም አለመጥቀስ አይቻለኝምና እነሆ ግጥሙን፦

“ዓይንህን በዓይኔ ፀንሼ፣ የቀስቱን ጮራ እንደቋጠርኩ

ሌሊት በህልሜ አማምጨህ፣ ህመምህን እየፈጠርኩ

ቀን ጥላህን እንደለበስኩ

የፍቅራችንን ነበልባል፣ በቁም ሰመመን እንዳቀፍኩ

ልብ ውስጥ እንዳዜሙት ሙሾ፣ የሲቃ ስልት እንዳቃጨልኩ

የነፍሴን የእሳት ዘለላ ጎዳናህ ላይ እንዳነጠብኩ

እንደ ገደል ዳር ቄጠማ፣ የሥጋት እምባ እንደቃተትኩ

ህይወቴን ላንተ እንዳሸለብኩ

ህልምህን በጄ እንደዳሰስኩ

ያን የመጀመሪያ ሞቴን፣ በመሸ ቁጥር እንደሞትኩ

አለሁ እንደ ብኩን መረብ፣ ትዝታህን እንዳጠመድኩ፡፡”

ይህን በተመረጡ ቃላት የትዝታ ምስጢርና ጥልቅ ስሜት የተገለፀበትን ግጥም በማሰብ ለሎሬቱ ያለኝን አድናቆት እየገለጽኩ ወደ ሌሎቹ የስንኝ ቋጠሮዎች ልለፍ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ በእጄ ይዤው ከነበረውና የተለያዩ ገጣሚያንን የግጥም ስብስቦች ከያዘው መጽሀፍ ላይ ሶስት ትዝታን የሚያወሱ የስንኝ ቋጠሮዎች ይገኛሉ፡፡ ሁለቱን ግጥሞች በተከታታይ እነሆ፡-

“ዐይኔ መቅበዝበዙን አንቺን ማየት ተወ

ርቀትሽን ደከመ፣

እግሬም ወዳንቺጋ መሄድን ረገመ፣

ለሽቦ ጥሪውም ጆሮዬ በደነ አፌ ዶለዶመ

ጣቴም ለሰላምታ ብእር ተቀየመ ለመፃፍ ለገመ፡፡

ትዝታዬ ብቻ ሰንጋ ፈረስ ጭኖ ሄደ ሸመጠጠ

ጫካ ዱር ገደሉን፣ ባህሩን ሳይፈራ እያቆራረጠ።

ምን ላድርገው ይሆን? መርሳት የፈራውን፣ ይህን አመፀኛ

ሌሊቱን ጠብቆ ብቸኝነት አይቶ

ሲያገላብጥ የሚያድር

የእንቅልፍ ቀበኛ፡፡

አንቺስ? ፍቅሬ ጠሬ?

አይንሽም እግርሽም አፍ ጆሮ ጣትሽም እንደኔው ከሆኑ

እንዴት አርጎሽ ይሆን ትዝታ አባ ጨካኝ ባለሩቅ ዘመኑ፡፡

እንጃልን!

እንጃልን!

ይህኛው “ትዝታ በሽታ” በሚል ርዕስ የተፃፈ ነው፡፡ ቀጣዩንና “ዘፈን” በሚል ርዕስ የተከተበውን ግጥም ደግሞ እነሆ፡-

“ስትወጂኝ ስወድሽ፣ መዋደድ ሳናጣ

ሊያቆየን ተሳነው፣ ፍቅር አቅም አጣ

በእንባ ተለያየን፣ አማላጅም ጠፋ

ግድ ሆነ መለየት፣ እውነት በኛ ከፋ

እንግዲህ ፍቅርዬ፣ ደህና ሰንብችልኝ

ከትዝታሽ ኑሪ፣ እኔም ትዝታ አለኝ

ካንቺ እንጂ የኔ ፍቅር፣ መለየት ቢያፋታኝ

ቅርሴ ነው ትዝታሽ፣ አይችልም ሊነፍገኝ

ሰማይ በጠቆረ፣ ቀኑ በፈገገ፣ አስታውስሻለሁ

በአድማስ መስታወት ላይ

እከስትሻለሁ

አካልሽ ቢርቀኝ፣ አንቺን ግን አላጣሽ

ትመጫለሽ ባይኔ፣ ታጫውችኛለሽ

ልቤን ያሞቀዋል፣ የህጻን ፈገግታሽ

ልክ እንደ በፊቱ፣ በፍቅር ዐይኖችሽ፣ ትማትሪኛለሽ

‹ትዝታሽ ዘወትር፣ ወደኔ እየመጣ

‹ትዝታሽ ዘወትር፣ ወደኔ እየመጣ፣…›”

አንዳንድ ትዝታ ግን ይገርማል። የስሜት ጥልቀቱ ፍቅርን ያህል ነው፡፡ ለነገሩ ከፅኑ የፍቅር ስሜት የተቀዳ ትዝታ ከሆነ ግዝፈቱ እንዲያ ቢሆን አይደንቅም። ይህን ያልኩት ከቀጣዩ የሜሮን ጌትነት የግጥም ሀሳብ በመነሳት ነው፡፡ ስሜቱን እምቢኝ፣ አሻፈረኝ ለማለት በቂ ምክንያት እያለን “የትዝታ እስረኛ” የምንሆንበት ነገር ምን ይባል ይሆን? በማለት ራሴን እንድጠይቅ አድርጎኛል። ምናልባትም እዚህ ላይ ይሆን የትዝታ ጥልቅ ምስጢር ያለው!? … ለማንኛውም ግጥሙን እነሆ፡-

“ለቃልህ ባትኖር ባይገዛህ ህሊና

እምነትን ሸኘሁት ደህና ሁን አልኩና

ዞረህ እንደማታይ ያወቀለት ሆዴ

ስሜቴን በእንባዬ አጠበው ልማዴ

ጠብቄ ባላገኝ እውነቴን ታቅፌ

ፍቅርህንም ሸጥኩት ለሌላ አሳልፌ

እንደማትመለስ በማለዳ አውቄ

የቀረኝን ተስፋ ገደልኩት አንቄ

አʼለቅ ያለኝ ደዌ እስከ አጥንቴ ዘልቆ

ትዝታህ ብቻ ነው ነፍሴ ላይ ተጣብቆ።”

እንግዲህ ትዝታን ስለሚዘክሩ ግጥሞች አንስቼ የተወሰኑትን እንዲህ አስነበብኳችሁ። ስንብቴን የማደርገው “ጉራማይሌ” በሚል ርዕስ የተለያዩ ፀሀፊያን ግጥሞችና አጫጭር ትረካዎች በቀረቡበት መጽሀፍ ላይ ካገኘኋቸው የስንኝ ቋጠሮዎች ቀጣዩንና “አንድ ላይ ይንጋልን” የሚለውን ግጥም ጀባ በማለት ነው፡-

“እሩቅ አገር ያለሽ፣ አንቺ ፍቅሬ ሆይ

ለምንድነው ከቶ፣ የምንለያይ

ብቸኛ ነፍስሽን፣ ምነው መሸሸግሽ፣ በሌሊቱ ጥላ

ላኪው ትዝታሽን፣ ስደጂው ወደኔ፣ ከኔ ያገኛል መላ

የፍጥረት ዓለሙ፣ መንፈስ እንደረጋ

የሚያማልል አዚም፣ በልብ ውስጥ ሲተጋ

በመስከረም ንጋት

ሰማይ ደም ሲመስል፣ ሲነግስ ውብ ስሜት

ፀጥ – ረጭ ስትል፣ ተፈጥሮ አረብባ

ሚስጥሯ ሲገለፅ፣ ውበቷ ሲያባባ

ድንገት ስርቅ ብለሽ፣ ግቢ ከሃሳቤ

አንድ ላይ ይንጋልን፣ ሆነሽ አጠገቤ፡፡