በሞቱ ህይወትን

በመለሰች ዘለቀ

የትንሳኤ በዓል ከሀይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡ የቤተእምነቶቹ ተከታዮች በዓሉን ልዩ ትርጉም በመስጠት ያከብሩታል፡፡ ትንሣኤ የሚለው ቃል “ተንሥአ” ከሚለው ከግእዝ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም መነሣት፣ አነሣሥ፣ ወይም አዲስ ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው፡፡

የትንሳኤው ምንነትና ለሰው ልጆች ያስገኛቸውን ድሎች እንዲያብራሩልን ከሀይማኖት መሪዎች ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

መልአከ አርያም ቀሲስ አስረስ መልአኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሲዳማ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ የትንሳኤ በዓል በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተእምነት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ያብራራሉ፡፡ ከበዓሉ ቀደም ብሎ የ40 ቀናት የጾምና የጸሎት ስርዓት ይፈጸማል፡፡ ይህም አብይ ጾም ሲሆን ትርጓሜውም “ትልቁ ጾም” ማለት ነው፡፡

ቀሲስ አስረስ እንዳስረዱት አብይ ጾም የሁላችንም ፈጣሪ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጾመው ጾም ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኃላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመግባት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በጾም አሳልፏል፡፡

ይህንን ፈለግ በመከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከትንሳኤው በፊት ለአርባ ቀናት በጾም ታሳልፋለች፡፡ ምዕመናኑ በዚህ ወቅት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው በጾም ከፈጣሪ ጋር የሚገናኙበት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ቀሲስ አስረስ ገለጻቸውን ይቀጥላሉ፡- ትንሳኤ ማለት መነሳት ማለት ነው፡፡ ይህም ተለያይተው የነበሩ ነፍስና ስጋ ተመልሶ አንድ የሚሆኑበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሞትን መነሳት ተስፋ የምናደርግበት ነው፡፡ በምድራዊ ህይወት መውደቅ መነሳት እንዳለ ሁሉ የመጨራሻ ተስፋ ትንሳኤ ነው፡፡

የሰው ልጅ ሲፈጠር ሞት እንዲስማማው ሳይሆን ህያው ሆኖ እንዲኖር ነበር፡፡ ነገር ግን አዳምና ሄዋን በሰሩት ሀጢአት ምክንያት ሞት ወደ ሰው ልጆች መምጣቱን መጽሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ይህንን ወደ ሰው ልጆች የመጣውን ሞት በመሻር ህይወትን ለመስጠት ኢየሱስ በስጋ ከድንግል ማሪያም ተወልዶ፣ በምድር ላይ ተመላልሶ፣ ተጠምቆ፣ ጾሞ የመጨራሻ የሆነውን የህመማት ጊዜ አሳልፎ የሰው ልጆችን ሀጢአት ተሸክሞ መስቀል ላይ መዋሉን ቀሲስ አስረስ መልአኩ ገልጸዋል፡፡

ከሞተ በኃላ በሶስተኛው ቀን በሀይሉ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቷል፡፡ ክርስቶስ ሲነሳ ለእኛም ከሞት በኃለ ስላለው ህይወት ትንሳኤያችንን አውጇል፡፡ ስለዚህ ትንሳኤ ከሞት ወደ ህይወት የተሸጋገርንበት በዓል ነው፡፡ ለዚህም የትንሳኤ በዓል በጉጉት የሚጠበቅና በደስታ የሚከበር እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ “ብትችሉ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ስለሚል በዓሉን ስናከብር ሰላምን አጥብቀን መፈለግና ስለሰላም መጸለይ እንዳለብን ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ቀሲስ አስረስ ገለጻ፣ የትንሳኤ በዓልን ስናከብር መርሳት የሌለብን አቅመ ደካሞችን መርዳት ነው፡፡ በቤተ እምነቱ ይህ ተግባር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይተገበራል፡፡ ለአቅመ ደካሞች ጾም ማስፈቻ በየደረጃው በየቤተክርስቲያናት ገቢ ይሰበሰባል፡፡ እነሱም በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ድጋፍ ይደረጋል፡፡

በመጨረሻም የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ እያልኩ በዓሉን ስናከብር የትንሳኤ ልቦና ኖሮን፤ በክፋት፣ በተንኮልና በሀጢአት ያንቀላፋን ሰዎች ከወደቅንበት የሀጢአት ጉድጓድ ወጥተን በንስሃ ልቦና መሆን አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡  

መልአከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ብርሃኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገር ስብከት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሀላፊ ናቸው፡፡ ትንሳኤ በዓል በቤተእምነቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ያነሳሉ፡፡ ጌታችን፣ አምላካችን፣ መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ህይወቱን ሰጥቶ ዓለምን ያዳነበት በዓል ነው፡፡

ስለበዓሉ ዳራ ሲያነሱም ከ5 ሺህ 500 ዘመን በፊት በአዳምና ሄዋን ሀጢአት ምክንያት ሞት በሰው ላይ ተፈርዶ ነበር፡፡ ይህንን ሞት ለመሻር ከድንግል ማሪያም ተወልዶ በመስቀል ሞቶ በሶስተኛ ቀን ተነስቷል፡፡ በመስቀል ሞቶ ደሙን አፍስሶ ስጋውን ቆርሶ የሞት እዳን አስወግዶልናል፡፡ በሞቱ ህይወትን ለሰው ልጆች ሰጥቷል፡፡ በሞቱ ሞትን በማስወገድ በትንሳኤው ትንሳኤን አውጆልናል፡፡

እንደ ቀሲስ ሰሎሞን ብርሃኑ ገለጻ በቤተእምነቱ ትንሣኤ ማለት ሕሊና ነው፡፡ ይህም ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ማለት ነው፡፡ የዚህም ምሥጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡

ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ያመላክታል፡፡ ይህም ከዓለም ህልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ የሚያመላክት ነው፡፡

ገለጻቸውን ሲቀጥሉም በዓለ ትንሣኤ ምእመናን የክርስቶስን ትንሣኤ የምናከብርበት ዕለት ነው ይላሉ፡፡ ይህ በዓል ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከውርደት ወደ ክብር፣ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነጻነት፣ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ ሕይወት የተሻገርንት በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ይከበራል፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስርዓቶች በዓሉን እናከብረዋለን፡፡

የኢትዮጵያ ምስጋና ወንጌላዊት አብያተቤተክርስቲያናት ደቡብ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፣ የሲዳማ ክልል ወ/አ/ክ/ህብረት ቦርድ አባል እና የሲዳማ ክልል ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስራ አስፈጻሚ አባል መጋቢ ሳሙኤል ቱንሲሳ በበኩላቸው የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተበትን አላማ በመገንዘብ መሆን አለበት ይላሉ፡፡

በማብራሪያቸውም፡- የእግዚብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለምን ሞተ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ከቁጥር 16 ላይ ሲናገር “በእርሱ የሚያምን የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” ይላል፡፡ በሌላ በኩል በ1ኛ ዮሀንስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 7 ላይ “የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሀጢአት ሁሉ ያነጻል” ይላል፡፡

በአዳም አለመታዘዝ ሀጢአት የመጣውን የዘላለም ሞት በኢየሱስ ክርስቶስ መሻሩን በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ከቁጥር 22 ቃሉ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የትንሳኤ በዓሉን ስናከብር ከሞት ወደ ህይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ አርነት ለማውጣት የሞተልንን የክርስቶስን ሞትና ትንሳኤን በማሰብ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም የትንሳኤን በዓል ስናከብር ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ያለብን ፍቅርን ነው ይላሉ፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ በዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ከቁጥር 12 ላይ ሲናገር፡- “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በራሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡ ትእዛዜን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ” ይላል፡፡

ክርስቶስ ራሱን ለሰው ልጆች ሀጢአት አሳልፎ በመስቀል ላይ ሲሰጥ ከፍጹም ፍቅር የተነሳ ነው፡፡ በመሆኑም የትንሳኤን በዓል ስናከብር በትንሽ በትልቁ መገፋፋትን ትተን ከእርሱ በተማርነው ፍቅር መሰረት በመዋደድና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ስለ ሰላም በመጸለይና ሰላምን በመፈለግ መሆን እንዳለበት መጋቢ ሳሙኤል ያስረዳሉ፡፡ በዕብራዊያን መጽሀፍ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 14 ላይ ሲናገር፡- “ከሰው ሁሉ ጋር ሠላምን ተከታተሉ፤ ትቀድሱም ዘንድ ፈልጉ፤ ያለእርሱ ጌታን ማየት የሚችል የለምና፡፡” ይላል፡፡

የትንሳኤ በዓል ዋነኛው አላማ በመስቀል ላይ ስጋውን ቆርሶ ለሰው ልጆች እንደሰጠ እኛም ካለን ላይ ቀንሰን ለድሆች መስጠት ይኖርብናል ሲሉም መክረዋል፡፡ በያዕቆብ መጽሀፍ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 ላይ፡- “ንጹሕና ነውር የሌለው አምልኮ ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና ባልቴቶችንም ከመከራቸው መጠየቅ ነው፣ በዓለም የሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” ሲል ያስረዳል፡፡

በዓሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነውን ፍቅር የምናስብበት፣ የሞተልንን ዓላማ የምንፈጽምበትና የምንኖርበት፣ ለሀገራችን ሠላምና ዕድገት የምንፀልይበትና የምንሠራበት፣ የመታደስ ዓመት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ ሲሉም መጋ ሳሙኤል ቱንሲሳ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡