“በምድር ላይ ስትኖሪ የጦር አውድማ ላይ እንዳለ ወታደር ነሽ” – አርቲስት ሃና ፈቃዱ

“በምድር ላይ ስትኖሪ የጦር አውድማ ላይ እንዳለ ወታደር ነሽ” – አርቲስት ሃና ፈቃዱ

በአለምሸት ግርማ

ይርጋለም ከተማ ያፈራቻት የኪነ-ጥበብ ፈርጥ ናት። ለቤተሰቧ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን ሁለት እህቶችና ሁለት ወንድሞች አሏት። ልጅ እያለች ጥሩ ጋዜጠኛ ወይም የህግ ባለሙያ መሆን ነበር ህልሟ- አርቲስት ሃና ፈቃዱ።

ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ይርጋለም መዋዕለ ህፃናት ገብታ ፊደል በመቁጠር ወደ መደበኛ ትምህርት ተሸጋግራለች። ይርጋለም አዳራሽ ትምህርት ቤት በመግባት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የተከታተለች ሲሆን በቤተሰብ የስራ ዝውውር ምክንያት ወደ ሃዋሳ ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር መጣች። በሃዋሳ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ትምህርቷን እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተከታተለች። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመግባት “በጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት” ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን አገኘች።

አርቲስት ሃና ተማሪ እያለች በሀዋሳ ቤተሰብ መምሪያ እና ፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ክበብ ግንዛቤን የሚፈጥሩ ስነ ፅሁፎችን እና ቲያትሮችን በማዘጋጀት እና በመተወን ተሳትፎ አድርጋለች። ከዚህ በተጨማሪ ገና የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት ከጓደኞቿ ጋር በመተባበር የጎዳና ልጆችን ሰብስበው ትምህርት ያስጠኑ ነበር። ለታክሲ ተብሎ ከሚሰጣቸው በመቀነስ ለልጆቹ ዳቦ መግዣ ይሰጧቸው ነበር። በዚያም ደስተኞች እንደነበሩ አጫውታናለች።

በተለይም በስነ-ተዋልዶ፣ በኤች አይ ቪ፣ የሴት ልጅ ንፅህና አጠባበቅ ላይ በትኩረት ይሰሩ ነበር። ሜሪጆይንና የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያን በማስተባበር ለሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙም ያደርጉ ነበር።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም በአካባቢው ያሉ አቅመ ደካማ ታዳጊዎችን በተለይም በልመና የተሰማሩ ሴቶችን ሊስትሮና ሱቅ በደረቴ እንዲሰሩ የማድረግ ስራን ስትሰራ ቆይታለች።

“ማድረግ የምችለው ነገር ከፍ እያለ ሲመጣ ያለኝን እውቅና በመጠቀም የተሻለ ነገር ለመስራት እየሞከርኩ ነው። ያኔ በልጅነት የተጀመረው የበጎ አድራጎት ስራ አድጎ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አዛውንቶች ድጋፍ እንዲያገኙ እየሰራሁ ነው። አብረውኝ ከሚሰሩ ጓደኞቼ ጋር በመተባበር አረጋዊያንን ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ አቅመ ደካማ ለሆኑ ህፃናት የቁርስ ምገባ እያደረግን ነው። ህፃናት በምገባው ከታቀፉ ጀምሮ ትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ የደረጃ ተማሪ መሆን ችለዋል። በዚህም ደስተኛ ነኝ” ትላለች።

“ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሆንኩ ለአረጋዊያኑ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራውን አብሬ እሰራለሁ። ከኪነ-ጥበብ ስራው ይልቅ የበጎ አድራጎት ስራው ላይ ነው ሰፊ ጊዜዬን የማሳልፈው። በዚህም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እየደገፉን ይገኛሉ።”

ለሀዋሳ ከተማ እና አካባቢው በአይነቱ የመጀመሪያ የነበረውን “የሞት_ሜዳልያ” የተሰኘውን ፊልም የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለች በመሪ ተዋናይነት ተጫውታ ብቃቷን አሳይታለች። በጊዜውም ፊልሙ ላይ ባሳየችው ድንቅ ብቃቷ የወርቅ ሜዳልያ ተሸልማለች። በአሁኑ ወቅትም ሰባት ጊዜ ሰባ በተሰኘው ፊልም ተወዳጅነትን አትርፋለች።

ከትምህርቷ ጎን ለጎን አጫጭር የፋሽን ዲዛይኒንግ ትምህርቶችን ትከታተል ስለነበር በዲላ ዶምቦስኮ ኮሌጅ በፋሽን ዲዛይኒንግ እና በሀዋሳ ከተማ አንጋፋ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአምስት ዓመታት በመምህርነት አገልግላለች። በትወናው ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የፊልም እስክሪፕቶችንም ፅፋለች። ሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሚሰሩ የፊልም ድርሰቶች በአብዛኛው የሂስ እና የማሻሻያ ሀሳብ አሻራዋን አሳርፋለች። ለታዳጊ ሴት አርቲስቶች አርዓያ መሆን የምትችል በስራ እና በጥረት መለወጥ እንደሚቻል ድንቅ ማሳያ የሆነች ጠንካራ ሴት ናት።

ከተሳተፈችባቸው ስራዎች መካከል ትርፍ አንጭንም፣ ዶክተሩ፣ ተነቃቃን፣ ባንቺ መንገድ፣ እንከባበር፣ በመንገዴ፣ ግሩም ቃል፣ በአንድ ቀን፣ ዳረኝ ይጠቀሳሉ። ግሩም ቃል፣ አንድ አለኝ እና ሰባት ጊዜ ሰባ በድርሰት የተሳተፈችባቸው ፊልሞች ናቸው።

በተጨማሪ አርቲስት ሐና በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በትኩረት የምትሰራ፤ ለበርካቶች መድህን የሆነች በሳል ወጣት ናት። አርቲስት ሀና ፍቃዱ በቅርቡ ከትወናው እና ከድርሰቱ በተጨማሪ የራሷን ፊልሞች ፕሮዲውስ በማድረግ ዝግጅቷን ጨርሳ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ተቀላቅላለች።

የኪነጥበብ ስራ፣ የበጎ አድራጎት ስራ፣ ሴትነትና የቤት ውስጥ ኃላፊነትን እንዴት እየተወጣሽው ነው? ስንል ላነሳንላት ጥያቄ እንዲህ ስትል መልሳልናለች፦

“ምንም እንኳን ጫናዎች ቢኖሩም በበዓላት ወቅት በአብዛኛው ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የማሳልፈው። የመጀመሪያ ልጅ በመሆኔ በቤት ውስጥ ኃላፊነትን በመወጣት ነው ልጅነቴን ያሳለፍኩት። ያ ልምድ ጠንካራ እንድሆን ረድቶኛል። በማህበራዊ ህይወት ማለትም በደስታም ይሁን በሀዘን እሳተፋለሁ። እንዲያልፈኝ አልፈልግም። መስራት ያለብኝን እሰራለሁ፤ ስራዬ ከቤተሰቤ አላራቀኝም።

“ሴትነትና ጥንካሬ በተፈጥሮ የተሳሰረ ነው። ሴቶች በተፈጥሮ በተለየ ሁኔታ ጥንካሬ ተሰጥቶናል። ፈተና በሁሉም ሰው ይኖራል። በተለይ በሴቶች ከፆታ ጋር ተያይዞ ተደራራቢ ውጣ ውረዶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ፈተና ሲኖር ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለራስ ጊዜ መስጠት ለችግራችን መፍትሔ በማፈላለግ ህይወትን እንድናስቀጥል ይረዳናል።

አባቴ በህይወት እያለ እንዲህ እያለ ይመክረኝ ነበረ፦

“በምድር ስትኖሪ የጦር አውድማ ላይ እንዳለ ወታደር ነሽ። ወታደር እየቆሰለ ሀገሩን እንደሚጠብቅ ሁሉ፤ ፈተና ቢገጥምሽም ራስሽን መጠበቅ አትርሺ” አባቴ የመከረኝ ምክር ጠንካራ አድርጎኛል። ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙኝም በሰዓቱ ያደክሙኝ ይሆናል እንጂ አልጣሉኝም። ከአባቴ ምክር የተነሳ እኔም ራሴን በሩጫ ላይ እንዳለ አትሌት ነው የምቆጥረው። ቢወድቁም ተነስቶ የመሮጥ ዕድል እንዳለ ነው የማምነው።”

እስከ አሁን 11 ፊልሞች ላይ ተሳትፋለች። ሶስት ፊልሞች ላይ ደግሞ በድርሰት። በሃዋሳ የሚገኘው ዳግማዊ አሰፋ የህይወት ዙሪያ ላይ መሰረቱን ያደረገ “ዳግማዊ” የተሰኘ ርዕስ ያለው ተከታታይ ድራማ ላይም ተሳትፋለች። በኪነ-ጥበብ እና በበጎ አድራጎት ተግባሯ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፋለች። የራሳቸውን ዓላማ ሲያሳኩ ስኬታቸው ወይም ምቾታቸው ሳይዛቸው ሌሎችን ለመደገፍ እረፍት የሚያጡ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። አርቲስት ሃና ደግሞ ከእነዚህ ውስጥ ትካተታለች።

ስለቀጣይ እቅዷ እንዲህ ስትል አጋርታናለች፦

“በቅርቡ ለእይታ የሚቀርብ ተከታታይ ድራማ አለ። በቀጣይ ዓመት የምታሳትመው መፅሐፍም ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። መጽሐፉ እውነተኛ ታሪኮች ፣የግል የህይወት ውጣ ውረዶችና ተሞክሮዎች ስበስብ ሲሆን መጽሐፉ እዚህ እንዲደርስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል።”

የዛሬ ሁለት ዓመት “በአንድ ቀን” በሚል ፊልም ላይ በነበራት ተሳትፎ በለዛ አዋርድ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ እጩ ተወዳዳሪ በመሆን ምርጥ አምስት ውስጥ መግባት ችላለች። በዘንድሮው ለዛ አዋርድም የራሷ በሆነው ሰባት ጊዜ ሰባ ፊልም በምርጥ ፊልም፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይና በምርጥ ሴት ተዋናይት ዘርፍ ለውድድር የቀረበች ሲሆን እሷ በምርጥ ሴት ተዋናይት ዘርፍ ምርጥ አምስቱን እየመራች ትገኛለች። በዚህ ውድድር የህዝብን ፍቅር አይቼበታለሁ ትላለች። የህዝብ ድምፅ በሚሰጥበት ላይ ብዙዎች በመምረጥና ቅስቀሳ በማድረግ ለኔ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋልና ላመሰግናቸው እወዳለሁ ብላለች።

የአንድ ልጅ እናት ለሆነችው አርቲስት ሃና  ከልምድሽ በመነሳት ለሴቶች ምን ትመክሪያለሽ? ብለን ላነሳንላት ጥያቄ እንዲህ ብላለች፦

“ሴቶች ትልቅ ቦታ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን በጥንካሬ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። ፈተናዎች ቢኖሩም በያዙት ሙያ ሊበረቱ ይገባል። ዓላማን አለመርሳት ደግሞ ለስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ችግሮች በሁሉም ሰው ላይ ይደርሳሉ። አንዳንድ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ የምናየው ምስሎች ላይ ሲስቁ የምናያቸው ሁሉ ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውላቸው አይደለም። ምናልባትም ከጀርባ ብዙ ችግሮችን ተሸክመው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ራሳችንን እያነፃፀርን ተስፋ መቁረጥ አይገባም። በተለይም በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች የእኔ ህይወት ጥሩ ማሳያ ሊሆናቸው ይገባል። ብዙ ሴቶች ትምህርታቸውና ቤተሰባቸውን ትተው፤ አንዳንዴም ያለ ዕድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ ይሔዳሉ። ነገር ግን እኔ የምላቸው ባሉበት ቦታ ሆነው መስራት ይችላሉ። ፊልም መስራት ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪም መሆን ይቻላል። ስለዚህ ባሉበት ሆነው ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ስራቸውን መስራት ይችላሉ። የእኔ ህይወት ለእንደነሱ ዓይነት ሴቶች ትልቅ ትምህርት ነው።”

የበጎ አድራጎት ስራውን በተመለከተ ስትናገር፦

ስራው የሚሰራው ደጋፊ አካል ኖሮ አይደለም። ህብረተሰቡ በተለይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሌላቸው ነገር ላይ ቀንሰው እየረዱን ነው። በዚህም ስራውን እያስቀጠልን ነው። የልደት ቀኔን በማስመልከት ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ አሰባስባለሁ። አሁን በቀን አንዴ የምንመግባቸውን በቀን ሶስቴ መመገብ እና ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ሳያሳስባቸው እንዲማሩ ማድረግ እንፈልጋለን። ከቻልንም ወደ ማዕከል የማሳደግ ዕቅድ አለን። በመሆኑም ህብረተሰቡ በቻለው ቢያግዘን ስትል ጥሪዋን አስተላልፋለች።