“ትንሳኤ ሰዎች ከዘላለም ሞት የዳኑበት ነው” – ፓስተር ተሰማ ታደሰ

“ትንሳኤ ሰዎች ከዘላለም ሞት የዳኑበት ነው” – ፓስተር ተሰማ ታደሰ

የዛሬው የንጋት እንግዳችን ፓስተር ተሰማ ታደሰ ይባላሉ፡፡ የሲዳማ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ለ28 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ የትንሳኤ በዓል እንዴት መከበር አለበት በሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በገነት ደጉ

ንጋት፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ፓስተር ተሰማ፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- እንደ ቤተ-ክርስቲያን አስተምህሮት ፋሲካ ማለት ምን ማለት ነው?

ፓስተር ተሰማ፡- ፋሲካ በእግዚአብሔር ቃል ዘጸአት ላይ እንደምንመለከተው እግዚአብሔር የእስራኤልን ህዝብ በግብጽ ሀገር በባርነት  ከቆዩበት እንዲያወጣቸው ሙሴን ልኮ ህዝቤን እንዲያገለግለኝ ልቀቅ ብሎ ለፈርኦን እንደነገረ ያስረዳል፡፡

 ፈርኦንም ልቡን በማደንደን በተደጋጋሚ እግዚአብሔር በሚያሳየው ምልክቶች ባለማመን አስር ዓይነት መቅሰፍቶችን በሀገሩ ላይ አድርጎ በአስረኛውና በመጨረሻው መቅሰፍት እግዚአብሔር ራሱን ያሳየበት እና የገለጠበት ሲሆን  በግብፃዊያን ቤት ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ ያለው እንዲሞት አዘዘ፡፡

ሰው ሁሉ ያንን ሞት ይዞ እያለ ለእስራኤል ልጆች የሚወጡበትን ምልክት ይሆን ዘንድ እያንዳንዱ የእስራኤል ቤተሰብ ለራሳቸው በነፍስ ወከፍ አንድ ጠቦት እንዲያዘጋጁ የዚያ ጠቦት ደም በእያንዳንዱ ቤተሰብ መቃን እንዲቀባ እና እግዚአብሔር ደም የተቀባው ቤት ከሞቱ እንዲያልፍ እና ደም ያልተቀባው በኩራቸውን እንዲገድል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የእስራኤልም ልጆች ያንን ትዕዛዝ ተቀብለው የጠቦቱን ደም እንደቀቡ ያንን መቅሰፍቱን ይዞ የመጣው መልዓክ ደግሞ የእስራኤልን ቤት ወይም ደም የተቀባበትን እያለፈ እንደሄደ እንመለከታለን። ያም ፋሲካ ተብሎ የተጠራ ሲሆን “ፋሲካ ማለት ሞት አለፈ የሚል ትርጉም አለው” የእስራኤል ልጆች መቃኑ ላይ ደም ቀብተው ሞቱን እንዳለፉ የሚያመለክት ነው፡፡

ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ የጠቦቱ ምልክት ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ደሙን አፍስሶ ከዘላለም ሞት ያዳነበት ትርጉም ነው፡፡ 

ንጋት፡- ትንሳኤ በዓል ለህዝበ ምዕመናኑ ምን የተለየ ትርጉም አለው?

ፓስተር ተሰማ፡-  ትንሳኤ በዓል በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር የእንስሳትን ደም ለእርቅ ይጠቀም እንደነበር እና ለሀጢአት ስርየት እንከን የሌለባቸውን እንስሳቶችን ሕዝቡ አቅርቦ ያርድና ከሀጢአታቸው ይሰረይ እንደነበር መጽሐፍ ይናገራል፡፡

ይህንንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሰውንና የፈጣሪን እርቅ እንዲፈጽም የተላከው ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ለሰው ልጆች የታረደበትና በእርሱ በኩል እግዚአብሔር ከዘላለም ሞት የሰው ልጆች ድነት ያገኙበት ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ከዘላለም ሞት እና ኩነኔ የዳኑበት እንደሆነ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ የምንመለከተው፡፡ ፋሲካ ሲመጣ የምናስታውሰው ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ የሰጠበት እና ምን ያህል ዋጋ እንደከፈለልን የምናስታውስበት ነው፡፡ የሰው ስጋ ለብሶ ደም ቢያፈስም የሞተው ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉም እንደተናገረው በሶስተኛ ቀን ከሙታን የተነሳ እና ተመልሶ ህያው የሆነበት ነው ትንሳኤ፡፡

በዚህም አዲስ አካል ለብሶ በአባቱ አብ ቀኝ በሰማይ አርጎ እንዳለ የምናስታውስበት ነው፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ የዘላለምን ህይወት ያገኙ ዘንድ እንደዚሁም በዚህ ምድር ላይ የስጋን ሞት ቢሞቱም እንደሚነሱ ምልክት ሆኖ የተነሳበት በመሆኑ ትንሳኤውን እያበሰርን ደስታን ምንጎናፀፍበት እና የምንገልጽበት በዓል ነው፡፡

እንግዲህ አንደ ቤተ እምነቶች የአከባበር ስርዓቱ ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ በዓሉ ሲከበር የኢየሱስ ክርስቶስ ህማማቱ፣ ስቃዩ፥ አምላክ ሆኖ ሳለ ሁሉን ማድረግ እየቻለ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት በሀጢአተኛ ምትክ ሀጢአተኛ ሆኖ እራሱን ለሰው ልጆች የቆረሰ እንደሆነ፣ ከራሱ ይልቅ ለሰው ልጆች ሞቶ የሚሞቱ ሰዎችን ያዳነባት መሆኑን የምናስብበት ነው፡፡

ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የቆረሰው ለሌሎች ነው፡፡ ሌሎች እንዳይሞቱ የዘላለም ህይወት ለሰዎች የሰጠበት ነው ትንሳኤ፡፡ 

ንጋት፡-  ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን መከራ እና ዋጋ እንዴት መረዳት አለብን?

ፓስተር ተሰማ፡- ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ አስቀድሞ ለ33 ዓመት ተኩል ያህል በምድር ሲያገለግል ይህንኑ ነው ያስተማረው፡፡ እርሱም የመጣበት ዓላማ ለሌሎች እንደሆነ እና ምን መስራት እንዳለበትም  አስተምሮ ነው የሄደው፡፡

በተለይም ለሌሎች ስለሚኖረው ፍቅር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ባልንጀሮቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን መውደድ እንዳለብን እንዲሁም እግዚአብሔርን መውደድ የሰው ልጆችን መውደድ እንደሆነም የገለጠበት ነው።

በብሉይ ኪዳን ላይ ያሉትን ሁለት ትዕዛዛትን አጠቃሎ በፍፁም ነፍስ በፍፁም ሀሳብ  አምላክን መውደድ እንዳለብንና ባልንጀሮቻችንን መውደድ እንዳለብን በትዕዛዛት ነው ያሳየው፡፡

እግዚአብሔርን የሚወድ የሰው ልጆችን መውደድ እንዳለበት አስተምሯል፡፡ ያንን አስተምሮ ፍቅር በተግባር ነው የገለፀው፡፡ ለሰው ልጆች ያለውን መስጠት ብቻ ሳይሆን ህይወቱን ሰጥቶ ነው ፍቅሩን በተግባር የገለፀው፡፡

በምድር ላይ ሲያስተምር የነበረውን በራሱ ላይ ፈርዶ ህይወቱን ሰጥቶ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት ነውና እኛም እሱን የምናምንና የምንከተል ከዚህ መማር አለብን፡፡

ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሌሎች ራሱን ከቆረሰና ከሰጠ ያለንን ማካፈል እንዳለብን፣ ለሌሎች መኖር እንዳለብን፣ የሌሎች ህመም ህመማችን እንደሆነ፣ የሌሎች ችግር ችግራችን እንደሆነ፣ የሌሎች ረሃብ ረሃባችን እንደሆነ በማሰብ ባለንና በምንችለው አቅም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ በሆነበት እኛም ያለንን ለሌሎች በማካፈል ህማማቱንና መከራውን መጋራት እንዳለብን ነው የሚያስተምረን፡፡

ንጋት፡- የትንሳኤን በዓል ከመቻቻል እና ከአብሮነት አንፃር እንዴት ማሳለፍ አለብን?

ፓስተር ተሰማ፡- በሞቱ ጊዜ የሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ሲሞት አህዛብ እና አይሁድ የሚባሉት ነበሩ፡፡ በዚህም ጎራ እንዳለ እንመለከታለን፡፡ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን የእኛ አምላክ የሚመጣው በዚህ መንገድ ነው ብለው ሲያስቡ ነበር፡፡ በህጋቸውም እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ተብሎ የተለዩ ነበሩ፡፡

አህዛብ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳይደሉ እና ከእግዚአብሔር መንግስት የተገለሉ እንደሆኑ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ራሱን አሳልፎ በመስጠት በሰው ልጆች መካከል  የልዩነት ግድግዳ እንደፈረሰ እንመለከታለን፡፡

በዚያን ጊዜ በብሉይ ኪዳን ቤተ-መቅደስ የተለየ ቦታ እና ክፍሎች ነበሩ፡፡ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ወይም የእግዚአብሔር ታቦት መገኛ እንደዚሁም አደባባይ የሚባሉ ቦታዎች ነበሩ።

እነዚያ ቦታዎች መግባት የሚችሉት  የተመረጡ ብቻ ናቸው፡፡ በዚህም አንድ ካህን ብቻ ነው በዓመት የሚገባበት፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሞት ግን ያ ግድግዳ ፈርሶ ከእግዚአብሔር ከአምላኩ ጋራ ወደ እርሱ በቀጥታ መግባት እንደሚቻል እና የጥል ግድግዳን እንዳፈረሰ እናያለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ በመስቀል ላይ እያለ እንኳን በቀኝ እና በግራ የተሰቀሉ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳ ከሁለት አንዳቸው በማመን መንግስተ ሰማያት የገቡበት ነበር፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በህማማቱ ጊዜ ተጣልተው የነበሩ መንግስታት ይህ ከእኔ በላይ ነው፤ ይህ ለእኔ ይገባል እያሉ በእነርሱ መካከል ያለው ፀብ እርቅ እንዳደረገላቸው እንመለከታለን፡፡

ሲሞትም ደግሞ በሰው ልጆች መካከል ያለውን ብቻ ሳይሆን በመንግስታትም መካከል ያለው ግድግዳ ወደ እርቅ እንደመጣ እናያለን፡፡ በዚህም አህዛብ የሚባሉ ሁሉ በእርሱ ሞት ምክንያት ከአይሁድ ሰዎች ጋር የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ተብለው እኩል ርስት እንዲኖራቸው የተደረገው፡፡

በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረም፣ ሆነ በሞቱም ጊዜ ተለይተው የነበሩ ሰዎች እንዲታረቁ እና ሰዎችም ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ አድርጓል፡፡

እንዲሁም በብሔር እና በጎሳ ተለይተው አይሁድ የሚባሉ ሰዎች ሁሉ እንዲታረቁ እና ያም ማለት በእግዚአብሔር መንግስት እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለው ዋጋ የልዩነትን ግድግዳ ያፈረሰ እንደሆነ ነው የምናየው፡፡

በአሁኑ ጊዜም እንደ ሀገር ስንኖር ሀይማኖታችን የተለያየ ቢሆንም በመከባበር እና በመተሳሰብ አንዱ አንዱን ሳይጎዳ እና ሳንጠፋፋ መኖር እንዳለብን ነው የሚያሳየው።

የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤውን በዓል ስናከብር እርሱ የሰራቸውን ስራዎች በማስታወስ በአብሮነት ማሳለፍ እንዳለብን በማሰብ መሆን አለበት፡፡ 

ንጋት፡- ሀገራችን ላይ አሁን እየታዩ ያሉት የሀይማኖት መቃረኖች ከምን የመነጩ ይሆን?

ፓስተር ተሰማ፡- በሀገራችን ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች መቃቃሮች አሉ፡፡ በብሔር ወይም በጎሳ እንዲሁም በሀይማኖት የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ እንመለከታለን፡፡

እንግዲህ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም ያንኑ መቻቻል የሀይማኖት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ መስራት ስላለብን የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡

በዋናነት የሚሰራው በሰላም እና በአብሮነት ላይ ነው፡፡ በሀይማኖታችን እንደየእምነቶቻችን መንቀሳቀስ እንደምንችል  ነገር ግን በግጭቶች ላይ መስራት እንዳለብን ተቋሙ ያምናል፡፡

ምክንያቱም ሰላም ሲኖር ነው ማንኛውንም ነገር መስራት የምንችለው፡፡ ዜጎቻችንም በሰላም ገብተው መውጣት እንዲችሉ በሰላም ጉዳይ ላይ መስራት ግድ ይላል።

ተቋሙ በዋናነት ወርቃማ ህግ ብሎ የሚጠቀመው በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በማንም ላይ አታድርግ፤ ላንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለሌሎች አድርግ የሚለውን ነው፡፡

እንደ ሃገር የሚስተዋሉ ግጭቶችን ስንመለከት ይህንን ወርቃማ ህግ ካለማክበር የሚመነጩ ናቸው፡፡ እኔ ስነካ የሚያመኝ ከሆነ ደግሞ ሌላውን አለመንካት የሀይማኖቶች ወርቃማ ህግ ነው፡፡

ስለዚህም በሀገራችን ያሉ ግጭቶች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የትኛውም ይሁን ግን ሌላውን መጉዳት እና ጥፋት እንዲደርስበት ማድረግ ሀይማኖታዊ አስተምሮ ላይ የሌለ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በዓል ስናከብር የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በተለይም ሰላምን ከማወጅ አንፃር ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሲያገለግል ሰላምንና እርቅን ዘርቶ እንደሄደ ነው፡፡ ስለዚህም ለተጎዱ እና ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች እንደ እኔ እየተሰማኝ መርዳት፣ መደገፍ፣ ሰላም በጠፋው አካባቢ ሰላም መፍጠር፣ ቁርሾ ካለም ወደ እርቅ በማምጣት በመቻቻል፣ በአብሮነትና በመደጋገፍ በዓሉን ሊያከብሩ ይገባል፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ቤት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡

የትኛውም እምነት መጎዳዳትን አያስተምርም፡፡ ምናልባት ቤተ እምነቶች የእምነቱን ተከታዮች በስርዓት ካለማስተማር እና ባለመግራት ሊሆን ይችላል።

ንጋት፡- ከፆም ወቅት ህብረተሰቡ ምን መማር አለበት?

ፓስተር ተሰማ፡- በእርግጥ ፆም ከእህልና ከውሃ መለየት ሲሆን ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ኢሳያስ የሚያስተምረው ክፋትን መፆም እንዳለብን ነው፡፡

ከእህልና ከውሃ መራቁ ምናልባት ሰዎች ተንኮል ለመስራት እንዳይበረታቱ እና አቅም እንዳይኖራቸው እንደሆነ ይታሰባል። መንፈስን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ለመፀለይ ሲሆን እርሱ የሚበረታታ ነው፡፡

ዋናው ፆም ግን እህልና ውሃ መፆም ብቻ አይደለም፡፡ ክፋትን መተው፣ ሌላውን ለመጉዳት አለመነሳሳት ነው፡፡

ስጋችን ታብዮ ለክፋትና ለሀጢአት እንዳይነሳሳ የተደረገ ሲሆን ትልቁ እና በእግዚአብሔር ፊት የሚታየው ፆም ሀጢአትንና እግዚአብሔር ደስ የማይሰኘውን ነገር መፆም ነው፡፡ ይህን ጊዜ ወገኖች ስላጠፉት ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት ይቅርታን ለመጠየቅ በመፀፀት ዳግም ላለመስራት ቃል የሚገቡበትና ለሌሎች ደግሞ መልካም ለማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ቃልኪዳናቸውን የሚያድሱበት ነው፡፡

ንጋት፡- በዓሉን ከተቸገሩት ጋር በአብሮነት ከማሳለፍ አንፃር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ፓስተር ተሰማ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበጎ አድራጐት ተግባራት በተለይም በወጣቶች እየተበራከቱ መጥቷል፡፡ ደስ ሚል ተግባር ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በትጋት የሚያገለግሉ ወገኖች አሉ፡፡ በቤታቸው ደግሰው እና አብሮ ከመጠጣት እና ከመብላት ይልቅ ሌሎችን ማብላት እና ለማስደሰት ቅድሚያ ሰጥተው የሚያገለግሉ  ሰዎች እየተበራከቱ ነው። እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡

የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ መብላትና መጠጣትን ለየት አድርገን ልንሰራ እንችላለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ያንን ዕድል ያላገኙ ሰዎች አሉና እነሱን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ጎዳና ላይ የወጡ ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን በዓል እቤታቸው ሆነው ግን ወደ ጎዳና ለመውጣት አፍረው የተቀመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ከጎዳናም ኑሮ ያልተናነሰ ኑሮ የሚኖሩ ወገኖች እንዳሉ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠት ከፈጣሪም ክብርን የሚያስገኝና መጽሐፍ ቅዱስም ሲናገር ባልቴቶችንና አቅመ ደካሞችን መርዳት ትክክለኛ አምልኮ ነው ይላል፡፡

በምድር ላይ አገልግለው ጧሪ እና ቀባሪ ያጡ በማዕከልም ይሁን ከማዕከል ውጪ ካሉ ወገኖች ጋር በማሳለፍ ከበረከቱ እንዲካፈሉ ማድረግ በጌታም ይሁን በሰው ፊት ትልቅ በረከት ነው፡፡

እምነት በስራ እንደሚገለጥ እና ከስራ የራቀ እምንት ባዶ እንደሆነ ሁሉ የታረዘውን በማልበስና የተራበውን በማብላት አቅማችን በፈቀደ መጠን ፆማችንን በተግባር መገለጽ አለበት፡፡

ንጋት፡- ሀገራችን ካለችበት አንፃራዊ ችግር እንድትወጣ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ፓስተር ተሰማ፡-  ሁሉንም የሚችለው ፈጣሪ ነው፡፡ ሁሉም በእርሱ ፊት ነውና የአማኞች ድርሻ በየትኛውም ሁኔታ ላይ  ፀሎት ማድረግ ነው፡፡

ሀገራችንን ፈጣሪ ወደ ሰላም እንዲያመጣ እና ከመበላላት እና ከመጠፋፋት መቆጠብ እንዲሁም በባለስልጣናት ላይ ፈጣሪ እውቀትን እንዲጨምር ለፈጣሪ በመስጠት ምድሪቱን በስርዓት እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር ፊት መሆን ያስፈልጋል፡፡

ከዚያም በዘለለ መምከርና ማስተማር እግዚአብሔር በሰጠው ፀጋ ቤተ-እምነቶች ምዕመናኑን፥ ምዕመናኑም ደግሞ የቤተ-እምነቶችን እና የአባቶችን ምክር መስማት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ሀገራችን አሁን ካለችበት ወጥታ ሁሉም ተደስቶ የሚኖርባት፣ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሳይሆን ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሚሆንባት ሀገር እንድትሆን ሁላችንም ድርሻ ስላለን የበኩላችንን መወጣት አለብን፡፡

ንጋት፡-  የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት ዕድሉን ልስጥዎ?

ፓስተር ተሰማ፡- ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ እንኳን ለጌታችንና ለመድሐኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ፡፡

የትንሳኤን በዓል ስናከብር እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው አደራ አለ፡፡ ሁላችን በምድር ስንኖር ለሰው ልጆች መልካም በማድረግ ዋጋ ያለው ኑሮ በእግዚአብሔር ፊት መኖር አለብን፡፡

የጎዳናቸው ወገኖችና ያዘኑብን ሰዎች ካሉ ይቅርታ በመጠየቅ እና እኛ ኖሮን እየበላንና እየጠጣን ሌሎች ደግሞ ሳይኖራቸው በዓሉን በችግር የሚያሳልፉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲያሳልፉ እመኛለሁ፡፡ ሀገራችንን ፈጣሪ ይባርካት ሰላሟም ይበዛ እላለለሁ፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ፓስተር ተሰማ፡- እኔም  አመሰግናለሁ፡፡