በአንዱዓለም ሰለሞን
…ካለፈው የቀጠለ
የዓለም ጸሐይ ግጥሞች ተራ የስንኝ ድርድሮች አይደሉም። ጥልቅ ሀሳብ ያላቸውና በውብ ቃላት የተከሸኑ፣ የተፈለገውን መልእክትም በአግባቡ የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ገና በወጣትነቷ ሳይቀር ከእድሜዋ በላይ የበሰሉ ሥራዎችን ለመስራት ችላለች፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ስትናገር የሰዎችን አስተያየት በመቀበል ስህተቷን እያረመችና ራሷን እያበቃች በመሄዷ፣ የማወቅ ፍላጎቷ ተገድቦ የማያውቅ በመሆኑና በአንባቢነቷ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡
በዚህ ረገድ ደግሞ የቅርብ ሰዎቿ የሆኑትን ማለትም የ “ኬሪዮግራፊ” ባለሙያ የሆነውን የመጀመሪያ ባሏን (ታደሰ ወርቁ) እና የሙዚቃ ባለሙያ የሆነውን ሁለተኛውን ባለቤቷን (ደጀኔ ገረመው) አስተዋጽኦ በዋንኛነት ትጠቅሳለች፤ በሥራዎቿ ላይ የሰላ ሂስና ገንቢ አስተያየት በመስጠት እንደ ደገፏት በመግለጽ። ከዚህ ባሻገርም ለቅርብ ጓደኞቿ እንዲሁም ለኪነ ጥበብ ሰዎች ሥራዎቿን የማስገምገም ልማድ እንዳላትና የሙገሳውን ያህል ነቀፌታውንም ያለመከፋት እንደምትቀበል ትገልጻለች፡-
“በዙሪያዬ የነበሩት ሰዎች ጥሩ ተቺዎች ነበሩ። በጥበብ ዓለም ብዙዎቻችንን የሚያጠፋን ነገር የሚያደንቀንን ሰው ብቻ መጠጋታችን ነው። ትክክለኛ ሀያሲያን ከሌሉ ጥበብ አያድግም። ሀገራችን ውስጥ ያለው ችግርም ይኸው ነው”፣ በማለት፡፡
ተወዳጇ የኪነ ጥበብ ሰው በብዙ ተመስጦ በጥልቅ መመሰጥ ውስጥ ሆና የከተበቻቸው ስንኞች በምርጥ ድምጻዊያን ሲዜሙ ድንቅ ሙዚቃ እንደሚሆኑ ሁሉ አንዳንድ ጊዜም የሚፈጠሩ እንከኖች አይጠፉም፡፡ ያኔ ታዲያ ሙዚቃውን ስትሰማው ስህተቱ ይጎረብጣትና ስቅቅ እንደምትል ሳትገልጽ አላለፈችም፡፡
ከዚህ አንጻር በባለሙያ ስህተት ሳይሆን በሳንሱር ምክንያት የገጠማት አንድ ጥሩ ያልሆነ ገጠመኟ እዚህ ላይ የሚነሳ ይሆናል። ነገሩ እንዲህ ነው፡-
በደርግ ዘመን ነው፡፡ የዓለም ፀሀይ “እዳ ቀለለ ስል ፍቅሯን አዘዘብኝ” የሚለውና ለሙሉቀን መለሰ ልትሰጠው የነበረው ግጥም በሳንሱር ምክንያት እንዲቀየር ተደረገ፡፡ በግጥሙ አዝማች ላይ ያለው አንድ ቃል ሲቀየር በግጥሙ መልዕክት ላይ ስለሚያስከትለው መፋለስ ግን “በአብዮት ጊዜ ዕዳ የለም” ያሉት ሳንሱር አድራጊዎች ደንታ አልነበራቸውም፡፡ እናም ሙሉቀን መለሰ እነርሱ ሳንሱር ባደረጉት መሰረት “ፍቅሯ ቀለለ ስል እሷን አዘዘብኝ” በማለት ዘፈኑን ተጫወተው ፡፡ ዓለም ጸሀይ ስለ ሁኔታው የሚሰማትን ስሜት ስትገልጽ፡-
“ብዙ ሰው ሙዚቃውን ስለሚወደው አያስተውለው ይሆናል እንጂ ትልቅ ተቃርኖ ነው የተፈጠረው፡፡ እኔ እንዴት ፍቅሯን ከተፈቃሪዋ ነጥዬ እጽፋለሁ፡፡ ይህ የማይሆን ነገር ነው፡፡ በዚህ ስህተት የተነሳ ሙዚቃውን በሰማሁ ቁጥር ሁሌም እሳቀቃለሁ”፣ ብላለች።
አርቲስት ዓለም ጸሀይ ወዳጆ በግጥም ሥራዎቿ ከሚቸሯት አድናቆት ባሻገር ብዙዎች አንድ ጥያቄ ያነሱላታል፡፡ ተዋናይ አበበ ባልቻ እና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም ደግሞ ጥያቄውን ቃል በቃል ያቀረቡላት የኪነ ጥበብ ሰዎች ናቸው፤ “ወንድ ሆነሽ ታውቂያለሽ?” በማለት።
የዚህ ጥያቄ መነሻ ወይም ምክንያት ሴት ሆና ሳለ ሴትን ልጅ የሚያወድሱና የሴት ልጅ ውበት ጎልቶ የተገለጸባቸውን በርካታ የሙዚቃ ግጥሞችን በመጻፏ ነበር። ከዓለም ጸሀይ ስንኞች ውበትን የመግለጽ ጉልበት አንጻር በርግጥም ጥያቄው የተጋነነ አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለዚህ እንደ አብነት ለመጥቀስ ድምጻዊ ዳዊት መለሰ ከተጫወተውና ግጥሙ የአርቲስቷ ከሆነው አንድ ሙዚቃ ጥቂት ስንኞችን እንመልከት፡-
መጠሪያ አልተገኘም የሚሆንሽ ላንቺ ተስማምቶ፣
ቁንጅና ራሱ ነሽ ውበት ነፍስ ህይወትም ዘርቶ፡፡
አልተፈጠረም ሰው የለሽም አምሳያ፣
የቁንጅና ጣሪያ የውበት ማሰሪያ፡፡
በሰፈሩ ሁሉ የሚያማምር ሞልቶ፣
ውበትሽ እንደ አርማ የሚታየው ጎልቶ፡፡
የንግስት ግርማ አለሽ አንገት የሚያስደፋ፣
ቃልሽ ምስክር ነው እውነት እንዳልጠፋ።
ቢፈጠር ርቀት ከሰማይ ሰማይ፣
እመጣ ነበረ ዐይንሽን እንዳይ፡፡
ዝልፍልፍ ነው ፀጉርሽ እንዳሻው ተኝቷል፣
ወገብሽን እንዳላይ ደብቆ ይዞታል፡፡
እያለ ይቀጥላል፡፡ …
በጣም ተወዳጅ የሆኑትን የጥላሁን ገሰሰን “ኢትዮጵያ” እና የመሀሙድ አህመድን “ሰላም” የተሰኙትን ሙዚቃዎች ግጥሞች የጻፈችውም ይህችው እፁብ ድንቋ የጥበብ ሰው ዓለም ፀሀይ ወዳጆ ነች፡፡ እኔም አርቲስቷ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን የሰጠቻቸውን ቃለ ምልልሶች መሰረት በማድረግ ያዘጋጀሁትን ጽሁፍ ሳበቃ ስንብቴን ኢትዮጵያ ከሚለው የሙዚቃ ግጥም ጥቂት ስንኞችን በመቆንጠር ነው፡-
የሰው ዘር ትስስር ልዑል ሀብት መቁጠሪያ፣
የነጻነት ምኩራብ የታሪክ መስፈሪያ፣
የእግዚአብሔር ብሩክ ምድር ቅድስት ኢትዮጵያ፡፡
የጥቁር ህዝብ ክብር የመአዘን ድንጋይ፣
የተጋድሏት መርህ የደም ፍሳሽ ብቃይ፣
የምድር ፍቅር ብስራት የመስዋዕት ሜዳ።
ባህል ቅርስ ቋንቋ ሰገነት፣
ኢትዮጵያ ሀገረ ገነት!
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ