የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ዶ/ር አደገ አለሙ ይባላሉ፡፡ የሲዳማ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያና የእንስሳት መኖ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከባለሞያነት እስከ ኃላፊነት ቦታዎች ለ12 አመታት አገልግለዋል፡፡ በክልሉ እየተደረጉ ስላሉ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጋብዘናቸዋል፡፡ ማብራሪያቸውም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በመለሰች ዘለቀ
ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶ/ር አደገ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- የትውልድ፣ የትምህርትና የሥራ ቆይታዎን ቢገልፁልን?
ዶ/ር አደገ፡- ትውድልና እድገቴ በሲዳማ ክልል በንሳ ወረዳ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በተወለድኩበት አካባቢ ተከታትያለሁ፡፡ የመጀመሪያ ድግሪዬን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ሙያ ተከታትያለሁ፡፡ በመቀጠል በወንዶ ገነት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳት ሀኪም በመሆን ለሁለት አመታት ሰርቻለሁ፡፡ ቀጥሎም በጽ/ቤቱ የእንስሳት ሀብት ልማት ስራ ሂደት አስተባባሪ በመሆን አገልግያለሁ። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ የእርሻ ማዕከል ኃላፊ ሆኜ ለሶስት አመታት ሰርቻለሁ፡፡ በመቀጠል በሀዋሳ ከተማ እንስሳት ሀብት ልማት ጽ/ቤት የእንስሳት ህክምና ስራ ሂደት አስተባባሪ በመሆን ለአንድ አመት አካባቢ አገልግያለሁ፡፡
ንጋት፡- የሌማት ትሩፋት ማለት ምን ማለት ነው?
ዶ/ር አደገ ፦ የሌማት ትሩፋት ማለት እንደ ስሙ ማዕዳችንን በአይነትና በብዛት በመሙላት ምግቡ የተመጣጠነ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃ የአካባቢውን ጸጋ በመጠቀም ማዕዳችንን የተሟላ የማድረግ ስልት ነው፡፡ ይህም አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
ንጋት፡- በክልሉ ያለውን የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ እንዴት ይገልጹታል?
ዶ/ር አደገ ፦ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ መርሃ ግብር በ2014 ዓ.ም ጥቅምት 24 ነበር በአርባ ምንጭ ከተማ በይፋ የተጀመረው፡፡ ከዚያ በመቀጠል ሁሉም ክልሎች እንደየ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር ገብተዋል፡፡ የሌማት ትሩፋት በዋናነት ሶስት ፓኬጆችን ይይዛል፡፡ እነዚህም የወተት፣ የዶሮ እና የማር ምርቶች ላይ ነው፡፡
በሲዳማ ክልል የሌማት ትሩፋት ቀደም ተብሎ ነበር የተጀመረው፡፡ በክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት በ7 ፓኬጆች ነበር የተጀመረው። ከእነዚህ የወተት፣ የዶር እና የማር ምርቶች በተጨማሪ የጓሮ ዓሳ እርባታ፣ የሀር ልማት፣ የቀይ ስጋ ምርት እና የበጎች ዝርያ ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ንጋት፡- በክልሉ የሌማት ትሩፋት ምርታማነትና ውጤታማነት ምን ይመስላል?
ዶ/ር አደገ፡- ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚለው የግብርና ጠቅላላ ሞቶ/መፈክር/ ነው፡፡ ወደ ሌማት ትሩፋት ስንመጣ ግን የተትረፈረፈ ገበታ ማለታችን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩም ራዕይ እሱ ነበር። አንድ መሶብ በሰብል፣ በእንስሳትና ፍራፍሬ ምርት የተሟላ መሆን አለበት የሚል ነው። ለምሳሌ አንድ ሌማት ላይ ወተቱ፣ ማሩ፣ ቅቤው፣ እንቁላሉ፣ ዓሳውና ፍራፍሬውም እንደየስነ ምህዳሩ ተሟልቶ በአንድ መሶብ መቅረብ ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ እንቁላል፣ ዓሳና ወተት የቅንጦት ምግቦች መሆን የለባቸውም። ማርና ፍራፍሬ ከማዕዱ ላይ መጥፋት የለባቸውም፡፡ ምርቱ በኢትዮጵያ የሚመረት እስከሆነ ድረስ እንችላለን፤ እንስራ ነው የሌማት ትሩፋት መፈክር፡፡
በክልሉ የሌማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታ ገጠም የአመራረት ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የህብረተሰቡን አመለካከት በመለወጥ ሁሉም ሰው እንዲሰራና ተጠቃሚ እንዲሆን እቅድ አውጥተን በመንግስት ደረጃ ንቅናቄ ተፈጥሮ ወደ ተግባር ተገብቷል። የሌማት ትሩፋት በይፋ ከተጀመረ አንድ አመት ከ6 ወር አካባቢ ሆኗል፡፡ በዘርፉም በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል። በተለይም በወተት፣ በማር ምርት፣ በዓሳ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ንጋት፡- የሌማት ትሩፋት ጠቀሜታዎችን እንዴት ይገልጹታል?
ዶ/ር አደገ፡- የሌማት ትሩፋት የሚሰራው በቤተሰብ ደረጃ ነው፡፡ የመጀመሪያ ጠቀሜታ ስርዓተ ምግብ ማሻሻል ነው፡፡ ቤተሰብ በራሱ ጓሮ ያመረተውን መጠቀም እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ይህም የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ተግባራችንን ያቀላጥፈዋል። ሁለተኛ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምግቦችን ለመተካት ያግዛል። የወተት ምርትና የዶሮ ስጋ ከውጭ ሀገራት በስፋት ይገባል፡፡ የሌማት ትሩፋት አላማ እነዚህንና ሌሎች ከውጭ ሀገር የሚገቡ የምግብ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ የምግብ ምርቶችን መጨመርም ሌላው ጥቅም ነው። ለምሳሌ ወደ ውጭ የሚላኩ የማር፣ የቀይ ስጋ እና የመሳሰሉ ምርቶች መጠን በማሳደግ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ነው፡፡
የሌማት ትሩፋት ሶስተኛ ጥቅም ደግሞ ገበያን በማረጋጋት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው፡፡ አራተኛው ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ያለው ፋይዳ ነው፡፡ ለምሳሌ በክልላችን በሁሉም ወረዳዎች ትርፍ የእንቁላል ምርት ይገኛል፡፡ ብዙ ማህበራት በዚህ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ንጋት፡- በክልሉ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ?
ዶ/ር አደገ፡- የወተት ምርታማነትን በተለየ ሁኔታ ለማሳደግ ልክ የሌማት ትሩፋት እንደተጀመረው የመጀመሪያ አመት 300 የወተት መንደሮችን ለማደራጀት ታቅዶ ዕቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት ተችሏል። በዚህ አመት ደግሞ 468 የወተት መንደሮችን ለማደራጀት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን 78 ከመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ የወተት ፓኬጁ በ22 ወረዳዎች ላይ የሚተገበር ሲሆን በቀሩት ሁለት ወራት የቀረውን ማሳካት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ንጋት፡- የዶሮና የእንቁላል ምርታማነትን ለማሳደግ ምን እየተሰራ ነው?
ዶ/ር አደገ፡- የዶሮ ፓኬጅ በክልሉ በ37 ወረዳዎች ላይ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በ37ቱ መዋቅሮች ወደ 555 የዶሮ መንደሮችን በማቋቋም 4 ሚሊዮን የእንቁላል ዶሮዎችን ለህብረተሰቡ ማሰራጨት ተችሏል። ይህንንም እቅድ ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህንን ዕቅድ በእጥፍ ማሳደግ አለብን የሚል አቋም ተወስዶ በዚህ አመት ደግሞ 8 ሚሊዮን እንቁላል ጣይ ዶሮ ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ወደ 8 የዶሮ መንደሮችን አቋቁመናል፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 6 ሚሊዮን 800 ሺህ አካባቢ ወይም 85 ከመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ የዶሮ መንደር ሲባል የዶሮ ቤት ግብአት፣ የክትባት አገልግሎት፣ የመኖ አገልግሎት በአንድ ማዕከል የሚገኝበት ማለት ነው፡፡ አንድ መቶ አካባቢ ወጣቶች በአንድ መንደር ውስጥ በኩታ ገጠም በሆነ መንገድ በዘርፉ ላይ እየተሰማሩ ይገኛሉ፡፡
ንጋት፡- የዓሳ ምርታማነት በክልሉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶ/ር አደገ፡- በክልሉ ዓሳ ምርታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሲዳማ ውስጥ በብዛት የሚከፋፈለው አንድ ዝርያ ብቻ ነው። ባለፈው አመት በ12 ወረዳዎች ላይ ነበር እቅዳችን የነበረው፡፡ የዓሳ ምርታማነት ማሳደግ ሲባል በወንዞችና ሀይቆች ላይ የሚሰራውን አያጠቃልልም፡፡ ለምሳሌ በሲዳማ ውስጥ ሁለት የተፈጥሮ ሀይቆች ይገኛሉ፡፡ እነሱም የሀዋሳ ሀይቅና የሎካ አባያ ሀይቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ የጊዳቦ ግድብ አለ፡፡ እንዲሁም በጣም ብዙ ወንዞች አሉ የአሳ ምርታማነትን በእነዚህ የተፈጥሮ ሀይቆችና ወንዞች ላይ አንሰራም፡፡ እኛ የምንሰራው ሁሉም ቤተሰብ ኩሬ በማዘጋጀት ለቤተሰቡ የሚሆነውን ዓሳ መሰብሰብ ይችላል፡፡ ስለዚህ ግብአት የማቅረብና ድጋፍ የማድረግ ስራ ነው የምንሰራው፡፡ ይህንንም የሌማት ትሩፋት ይፋ ሲደረግ በመጀመሪያ አመት በ12 ወረዳዎች ላይ ነው መስራት የጀመርነው። በ12ቱም ወረዳዎች ላይ ሁለት መቶ ሰማኒያ የቤተሰብ ኩሬ ለማዘጋጀት እቅድ የተያዘ ሲሆን 300 ኩሬ በማዘጋጀት ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ተችሏል፡፡ በየቀበሌው ሁለት ሁለት ሞዴል አርሶ አደሮችን በመምረጥ በዚህ ስራ እንዲሳተፉ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል። ስልጠና በመስጠት ፣ የዓሳ ጫጩትና ግብዓት በመስጠት ቀጥታ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህ አመት ተጨማሪ ወረዳዎችን መጨመር አስፈላጊ በመሆኑ በ14 ወረዳዎች ላይ እየተሰራ ይገኛል። የዚህን አመት 89 ከመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ በቅርቡ 375 ኩሬዎች ላይ ለመስራት የታቀደ ሲሆን በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 313 ኩሬዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ ገብተናል፡፡
ንጋት፡- የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለጻሉ?
ዶ/ር አደገ፡- ወደ ማር ምርት ስንመጣ ንቦች ማዳበሪያ የማይፈልጉ ሰራተኛ የማይቀጠርላቸው የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ ድካማቸውን በማገዝ በደንብ ተንከባክበን አዘምነን ቴክኖሎጂ እና ግብዓት ጨምረን ስንሰራ ከጥቂት ቦታ ብዙ ጥቅም ማግኘት ይቻላል፡፡ እንደ ክልል ልዩ ትኩረት ሰጥተን ነው የምንሰራው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ስነ ምህዳር ለማር ምርት ምቹ ነው፡፡ የሲዳማ ሁሉም ወረዳዎች ቡና አብቃይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በቂ አበባዎች ይገኛሉ፡፡ የአበባና የፍራፍሬ ዛፎችም በብዛት የሚገኝበት ክልል ነው፡፡ እንደዚህ የተፈጥሮ ደኖችም ለዚህ ስራ የተሰጠ ነው፡፡
በመጀመሪያ አመት የሌማት ትሩፋት ሲጀመር 15 ወረዳዎችን ለይተን 30 ቀበሌዎችን መርጠን በየቀበሌ አንድ የንብ መንደር እንዲመሰረት አድርገናል፡፡ ከፌደራል የተላከ ክትትልና ግብረ መልስ ቡድን ይህንን አረጋግጦ እውቅና ሰጥቷል፡፡ በሁለተኛ አመት ወይም በዚህ አመት ላይ የወረዳውን ቁጥር ለመጨመር ሳይሆን የታሰበው የመንደር መጠን ነው እንዲጨመር የተደረገው፡፡ በ15 ወረዳዎች ላይ 48 መንደሮችን ለመፍጠር ነበር ታቅዶ ወደ ተግባር የገባነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 48 መንደሮችን አዳርሰናል፡፡ የግብአት አቅርቦትን በተመለከተ በዚህ አመት ብቻ ወደ 50 ሺህ የንብ ቀፎ ለማሰራጨት ነበር ዕቅዳችን፡፡ በእስካሁን ክንውን 42 ሺህ 216 ቀፎዎችን ወይም 84 ከመቶ ለማሳካት ተችሏል፡፡ ቀሪው 15 ከመቶ በቀሪ ሁለት ወራት ውስጥ የሚሳካ ይሆናል፡፡
የሌማት ትሩፋቱን ክልሉ ወደ ማሳካት ደረጃ የደረሰ ሲሆን በዘርፉም ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግቧል፡፡ በተግባር የሚታይ ስራ መስራት ተችሏል፡፡ የንብ መንጋ አየር ላይ ስለሆነ የሚንቀሳቀሰው አርሶ አደሮች በባህላዊ መንገድ ነበር ቀፎ አዘጋጅተው ለመሰብሰብ ሲሞክሩ የነበረው፡፡ ይህንን ለማስቀረት ሶስት ንግስት ንብ ማባዣ ማዕከል አቋቁመናል። በሶስቱም በቀላሉ ንግስቲቷን በማባዛት አዲስ የንብ መንጋ የመፍጠር ስራ ይሰራል፡፡ ከዚያ ወደ አርሶ አደሮች ቀፎ በቀላሉ እንዲገባ ይደረጋል፡፡
ንጋት፡- የበጎችን ዝርያ የማሻሻልና ምርታማትን የማሳደግ ተግባር ምን ይመስላል?
ዶ/ር አደገ፡- የበግ ዝርያ የማሻሻል ፓኬጃችን ደጋማውን አካባቢ ያቀፈ ነው። የበጎችን ማዕከል በ12 ደጋማ ወረዳዎች ላይ ነበር በስፋት የሰራነው፡፡ በምርምር የተረጋገጡ እና የተሻሻሉ የበጎች ዝርያ ከቦንጋ በማስመጣት በ12 ወረዳዎች ላይ እንዲዳረስ አደርገናል፡፡ የአካባቢ በጎችን ከእነዚህ በጎች ጋር በማዳቀል ምርታማነቱን የማደሳደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በጎች በአመት ሁለት ጊዜ የሚወልዱ ሲሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎች ደግሞ በአንዴ ሁለት እና ከዚያ በላይ መውለድ ይችላሉ፡፡ በዚህም 51 ሺህ 815 የበጎችን ዝሪያ ለማሻሻል ነበር በዚህ አመት እቅድ የተያዘው። ከዚህ ውስጥ ወደ 44 ሺህ 464 ወይም 84 ከመቶ በጎችን ዝርያ የማሻሻል ስራ ተሰርቷል። በ12 ወረዳ ሁለት ሁለት መንደሮች ስላሉ ወደ 24 የሚያህሉ መንደሮች የዝርያ ማሻሻል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
ንጋት፡- የቀይ ስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎችን እንዴት ይገልጹታል?
ዶ/ር አደገ፡- ቀይ ስጋ ምርት በሚመለከት በኤክስቴንሽን ዘርፉ ላይ ነበር ክፍተት የነበረው፡፡ ሁሉም ሰው የስጋ ፍላጎት ስላለው በባህላዊ መንገድ በጎችንና በሬዎችን ያደልባሉ፡፡ በስጋ ልማት ላይ በስፋት መሄድ ይችላሉ ተብሎ በተመረጡ በ7 ወረዳዎች ላይ በዘመናዊ መንገድ የቁም እንስሳትን የማደለብ ስራ ጀምረናል፡፡ በ7 ወረዳዎች ላይ 14 መንደሮችን በማዘጋጀት ስራው እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ በየመዋቅሩ ያሉ የጤናና የእርባታ ባለሙያዎች በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
ንጋት፡- እንደ ሀገር የክልሉ የሌማት ትሩፋት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶ/ር አደገ፡- በሀገር ደረጃ በሌማት ትሩፋት ሲዳማ ክልል ሞዴል እንደሆነ ተመስክሯል። በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች በክልሉ ያሉ የሌማት ትሩፋቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱም ለዘርፉ ውጤታማነት እውቅና ተሰጥቷል፡፡ በዘርፉም የሚታዩ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ለአብነትም ከዚህ በፊት በሀዋሳ ከተማ አንድ እንቁላል በ16 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በተለያዩ ማዕከላት በ10 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በአቅርቦትም በዋጋም ተጨባጭ ለውጥ ታይቷል፡፡ ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻርም ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡
ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ በመሆን ስለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናሉ፡፡
ዶ/ር አደገ፡- እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ