ሆሳዕና በአርያም

ሆሳዕና በአርያም

በአለምሸት ግርማ

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን የኃጢአት ዕዳ በመክፈል ከዘላለም ሞት ለማዳን በመስቀል ላይ ተሰቅሏል። “እግዚአብሐር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” ተብሎ እንደተፃፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መስዋዕት ሆነ።

ኢየሱስ ክርስቶስ በበረሃ ያለ ምግብና ውሃ ለ40 ቀናት ቆይቷል። የስቅለቱ ጊዜ ሲቃረብ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት ነበረበት። በዚያም ወቅት ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ነበር። የተቀመጠባት ውርንጭላም ሰው ያልተቀመጠባት፤ በእርሱ የተመረጠች ነበረች።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ከተማዋ በገባ ጊዜ “ሆሳዕና በአርያም፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን፤” እያሉ ዘምረውለታል። የዘንባባና የወይራ ዝንጣፊ እንዲሁም የለበሱትን ልብስ በመንገዱ ግራና ቀኝ እያነጠፉለትም አጅበው ተቀብለውታል። ዕለቱም ሆሳዕና በመባል እየተከበረ ይገኛል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ጌታ ሊፈፅመው ያለው ትልቅ ዓላማ ነበረው። የሰውን ልጅ ኃጢያት በጫንቃው መሸከም። እስከሞት ድረስ በመሰዋት ፍቅሩን መግለፅ።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰዋው የሰውን ልጅ ከተፈረደበት የዘላለም ሞት ወደ ዘላለም ህይወት ወይም ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር ነው። ለዚህ ዓላማ ስኬትም ብዙ መከራን ተቀብሏል። ተንገላቷል።

ይሁን እንጂ ዝቅ ብሎ ወደ ምድር በመምጣቱ ብቻ ማንነቱን(አምላክነቱን) መቀበል ያቃታቸው ብዙዎች ነበሩ። አምላክ የሰው ልጅን ለማክበር ስጋ ለብሶ ወደ ምድር መምጣቱ ሳያንስ ለክብሩ የሚገቡ መጓጓዣዎችን መጠቀም እየቻለ የአህያ ውርንጭላን መምረጡ ትሁትነቱን የሚያመለክት ነው።

ሆሳዕና በአቢይ ፆም የመጨረሻው እሁድ የሰሞነ ህማማት መቀበያ ዕለት እንደመሆኑ የጌታችንና የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ህማማተ መስቀል በማሰብ የበደሉንን ይቅር እንድንል ለንስሃ የምንዘጋጅበት ወቅት ነው። በክርስትና እምነት አስተምህሮት “ሰውን ሁሉ እንደራስህ አድርገህ ውደድ” የሚለው መርህ አብዛኛውን ህግ ጠቅልሎ የሚይዝ በመሆኑ ክርስቶስ በመስቀል የከፈለውን ዋጋ በማሰብ እርስ በእርስ መዋደድ ይገባል።

ሰሞነ ህማማት ከዕለተ ሆሳዕና እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ የሚያጠቃልል ነው። የህማማት ሰሞን ክርስቶስ የተሰቃየበትና መከራን የተቀበለበት ሰሞን ነው። ወቅቱ የሰውን ልጅ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለማውጣት በፈቃዱ የተቀበላቸውን መከራዎች እንድናስብ ያደርገናል። ስቃዩ፣ መዋረዱ፣ መገፋቱ ሁሉ በሰራው በደል ሳይሆን ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር መግለጫ ነው።

የሰሞነ ህማማት ዕለታት የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚሰግዱበት፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ በፆም፣ በፀሎትና በንስሃ ከአምላካቸው ጋር የሚቀራረቡበት ወቅት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ከመሰቀሉ በፊት የሰው ልጅ በኃጢያቱ ከአምላክ ርቆ የዘላለም ሞት ተፈርዶበት ነበር። ነገር ግን አምላክ በገባው ኪዳን መሰረት የሰውን ልጅ እንደገና በምህረት ጎበኘ። የጥሉን ግድግዳ ሊያፈርስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቀለ።

“ሀመ” – ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያቢሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን የመከራዎች ብዛት የሚያሳስብ ነው፡፡

በሰሞነ ህማማት መጨባበጥ፣ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጥ አይፈቀድም። ምክንያቱም አይሁድ ጌታን ለመስቀል ያደረጉት ምክራቸው የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት አይሁድ እያንሾካሾኩ ኢየሱስ ክርስቶስን “እንስቀለው… እንግደለው” ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ይህንን ለማስታወስ ሰላምታም ሆነ መስቀልን መሳለም አይፈቀድም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት በመሆኑም ክርስቲያኖች ህመሙን በማሰብ ራሳቸውን ከደስታ በመቆጠብ የሚያሳልፉት ሳምንት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ምድር ለመጣበት ዓላማ ይረዱት ዘንድ 12 ሐዋሪያትን መርጦ ነበር። ዓላማውን ለማስፈፀም አብረው ይውላሉ፣ ያድራሉ። እርስ በእርስ የጠነከረ ወዳጅነትም ነበራቸው። ከስሩ ቁጭ ብለው ከእርሱ መልካምነትን በተግባር ጭምር ተምረዋል።

ይሁዳም ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉት 12ቱ ሐዋሪያቶች ለአንድ ዓላማ ህብረትና አንድነት ያላቸው የክርስቶስ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ። እርሱም ከእነርሱ አንዱ ነበረ። በፀሎተ ሐሙስ የመጨረሻው ማዕድ ላይ ክርስቶስ “ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ተናገራቸው። እነሱም እርሰ በራስ “ማን ሊሆን ይችላል?” የሚለውን ተነጋገሩ፤ ሆኖም ግን ሁሉም “ከአንተ ጋር እንሞታለን እንጂ አንክድህም” ሲሉ ደጋግመው ነግረውት ነበር።

ይሁን እንጂ ከ12ቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ወዳጅነቱንና ታማኝነቱን በማጉደል ከዕለታት በአንዱ ቀን ጌታውን በገንዘብ አሳልፎ ለመሸጥ አሰበ። ጌታን ፈላጊዎችም አጋጣሚውን ተጠቀሙበት። ጌታውን አሳልፎ ከሰጣቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚሰጡት በመንገር አስማሙት።

በጊዜው ለጌታው ከመታመን ይልቅ የሚያገኘው ገንዘብ ደስታን የሚሰጠው መሰለው። ጌታውን ሽጦ በገንዘቡ የተሻለ ደስታን ለማግኘት ብዙ አቀደ። በልቡም ይሔን አጋጣሚ መጠቀም እንዳለበት ወሰነ። በውሳኔውም መሰረት ከገዢዎች ጋር ተስማማ። ጌታውን ለመሸጥ ባሰበበት ወቅት ጌታውን ከሌላው ጊዜ በተለየ ሳመው። ሰላምታው ከገዢዎቹ ጋር የሚግባቡበት መንገድ ነበር። ሰላምታ የፍቅር መግለጫ ቢሆንም እሱ ግን ጌታውንና የቅርብ ወዳጁን ለሞት አሳልፎ የሰጠበት መንገዱ ነበር።

ይሁዳ ኢየሱስን ሲስመው ወታደሮቹ በፍጥነት መጥተው ያዙት፤ እንደ ወንጀለኛ ለፍርድ አቀረቡት። ይሁዳም የጓጓለትን ገንዘቡን ተቀበለ።

ይሁዳ ጌታውን ለጠላቶቹ አሳልፎ ለመስጠት “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው። ሰላምታው የፍቅር ሳይሆን ተንኮል የተሞላበት ነበር፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ መለዋወጥ አይቻልም፡፡

ይህ ሳምንት የሰው ልጆች ከሞት ወደ ህይወት የተሸጋገሩበት ከጨለማ ወደ ብርሀን የወጡበት የመሸጋገሪያ ወራት ምሳሌ በመሆኑ በሳምንቱ ስርአተ ፍትሀት አይደረግም፡፡

ክርስቲያኖች ሳምንቱን በፆም፣ በፀሎት፣ በስግደት ያሳልፉታል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርባ ቀናት በምድረ በዳ በነበረበት ወቅት በዲያብሎስ ተፈትኖ ነበር።

ፈታኙ ዲያብሎስ ወደ እርሱ ቀርቦ የመጣለት ዓላማ እንዳይፈፀም ለማድረግ ጥረት አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣበትን ዓላማ ለመፈፀም ገስፆታል። ዲያብሎስም ሃሳቡ እንዳልተሳካ በተረዳ ጊዜ ከእርሱ ርቋል።

በአይሁድ በዓል በየዓመቱ ለፋሲካ አንድ እስረኛ ይለቀቅ ነበር። ክርስቶስ እና በርባን የሚባል እስረኛ በህዝቡ ፊት ቀረቡ። ህዝቡም በቄሳር “በርባን ይፈታ ወይስ ክርስቶስ?” ተብለው ምርጫ ሲሰጣቸው “ባርባንን ፍታልን” አሉ። “ኢየሱስ ምን ይደረግ?” ሲባሉ ዘምረው የተቀበሉት “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ። የህዝቡ ድምፅ ይሁንታን በማግኘቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ ተላልፎ ተሰጠ። እስከመጨረሻው መከራና ስቃይንም ተቀበለ።

ይህም ለቆምንለት ዓላማ እስከ መጨረሻው ድረስ ዋጋ መክፈል እንደሚጠበቅብን ያስተምረናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሞት ድረስ የሰው ልጆችን ወዷል። ክርስቶስ ባስተማረው ፍቅር መሰረት የሰው ልጆች እርስ በእርስ ሊዋደዱ እና ሊደጋገፉ ይገባል!