‎የእንስሳትን ጤና መጠበቅ የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ መሆኑን በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ

‎የእንስሳትን ጤና መጠበቅ የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ መሆኑን በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ

‎‎ሀዋሳ፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የእንስሳትን ጤና መጠበቅ የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ነው ሲል በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳት ጤና ቁጥጥርና በሽታ መከላከል አስታወቀ፡፡

የኮሬ ዞን አርሶ አደሮች እንስሳትን በማስከተብ በሽታን መከላከል መቻላቸውን ገልፀዋል።

‎የእንስሳት ጤና ከሚጠበቅበት መንገድ አንዱ ተከታታይ ክትባት ሲሆን ሰዎች የእንስሳትን ተዋጽኦ ተጠቃሚ በመሆናቸው ጤናቸውን መጠበቅ የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ እንደ ሆነ ነው በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳት ጤና ቁጥጥርና በሽታ መከላከል ቡድን መሪ ዶክተር ዓለሙ ጥላሁን የተናገሩት።

‎በዓለም አቀፍ ደረጃ 71 በመቶ በኢትዮጵያ 51 በመቶ በላይ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ጥናቶች ያረጋግጣሉ ያሉት ዶክተር ዓለሙ፥ ከበሽታ ነፃ የሆነ እንስሳትን በመፍጠር የሰው ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ወቅቱን ጠብቆ የሚቀሰቀሱ በሽታዎችን ለመከላከል በጊዜ ሰሌዳ ክትባት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የእንስሳትን ሙሉ ጤና ለመጠበቅ ንጽህናውን መጠበቅ፣ በቂ መኖ ማቅረብና እንስሳቱ ሲታመሙ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ብቻ ማሳከም እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።

‎አርሶአደር ተስፋዬ ሞቻ እና በዛብህ ቶሬ ከዚህ ቀደም ከብቶቻቸው በወረርሽኝ በሽታ ሲጠቁ እንደነበር ገልጸው ተከታታይ ክትባት መሰጠት ከጀመረ ወዲህ የእንስሳት ጤና መጠበቁን ተናግረዋል።

‎አክለውም አርሶአደሮቹ ከልምድ ህክምና ወጥተው በሰለጠነ ባለሙያ በማሳከምና በቂ መኖ በማቅረብ የእንስሳቱን ተዋጽኦ ማሳደጋቸውን ነው የገለጹት።

‎ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን