ሥርጭቱን የመግታት እርምጃ
በደረጀ ጥላሁን
በዓለማችን ለሰው ልጆች የጤና ጠንቅ ከሆኑ ገዳይ በሽታዎች መካከል አንዱ ወባ ነው። በአገራችን ወባ በቆላማ አካባቢዎችና ከፍታቸው ከ2000 ሜትር በታች በሆኑ የወይና ደጋ አካባቢዎች ላይ ተሰራጭቶ የሚገኝ የበሽታ አይነት ነው፡፡ በአንዳንድ ወቅት ከዚህ ከፍታ በላይም ለትንኞች መራቢያ ተስማሚ ውሃ፣ ሙቀትና በቂ የአየር እርጥበት በሚፈጠርበት ጊዜና ቦታ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የወባ በሽታ በአብዛኛው ከክረምት ወራት በኋላ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት በከፍተኛ ደረጃ የሚተላለፍ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ከበልግ ዝናብ በኋላ ከሚያዝያ እስከ ግንቦት በመጠነኛ ደረጃ በወረርሽኝ መልክ ይከሰታል፡፡ ይህም በሽታው ከሚያስከትለው ሞትና ሕመም በተጨማሪ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ገቢና በአጠቃላይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርሳል፡፡
በዚህ ዝግጅት በወባ በሽታ መከላከል ዙሪያ በተከናወኑ ሥራዎች ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ያገኘነውን መረጃ እንስቃኛችኋለን÷
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ትኩረት ከሚሹ በሽታዎች መካከል የወባ በሽታ አንደኛው ነው። ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት የበሽታው ሥርጭት የቀነሰ ቢሆንም አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ይከሰታል፡፡ ቀደም ሲል በክልሉ የወባ በሽታ የሚከሰትባቸው 21 ወረዳዎች ሲኖሩ አሁን ላይ የደጋ አየር ፀባይ ያላቸው ወረዳዎች ላይም መታየት መጀመሩን ነው አቶ እንዳልካቸው ደመቀ በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የገለጹት፡፡
ባለፈው አመት የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ተከትሎ በተደረገው ርብርብ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም፡፡ ጉዳቱን መቀልበስ መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ ለዚህም በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰሩት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ውጤታማነት ምክንያት ናቸው ብለዋል፡፡
በክልሉ በሽታው በስፋት ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ሀዋሳ ከተማ ሲሆን 50 በመቶ የሚሆነው የበሽታው ሪፖርት ከዚሁ ከተማ የሚቀርብ ነው፡፡ በከተማው ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ አካባቢዎች በስፋት መታየታቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ አካባቢውን በማጽዳት፣ ኬሚካል በመርጨት፣ የመኝታ አጎበር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ በሽታውን መግታት ተችሏል፡፡
በበሽታው የሚያዙ ሰዎችም ፈጣን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል አስፈላጊው የፀረ- ወባ ፈዋሽ መድኃኒት ወደ ህክምና ተቋማት እንዲቀርብ በመደረጉም መቆጣጠር መቻሉን ማወቅ ተችሏል፡፡
ህብረተሰቡ የተሰጠውን የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር፣ የህክምና ባለሙያዎችን ምክር በመተግበርና ቤቱን በፀረ- ወባ ኬሚካል በማስረጨት÷ ራሱንና ቤተሰቡን ከወባ በሽታ መጠበቅ እንዳለበት የገለጹት ዳይሬክተሩ ባለፈው አመት 950 ሺህ አጎበር መከፋፈሉንም ተናግረዋል።
አቶ እንዳልካቸው እንዳሉት በደጋ አካባቢ ስለታየው ወባ ምርምር እየተደረገ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ ላይ በተደረገ ጥናትም ‹‹አስተፈንሳይ›› የምትባል ትንኝ መገኘቷን ተናግረዋል፡፡ ትንኟ አዲስ አይነት ብትሆንም በሽታው ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህም መከላከያ መንገዱን ሊቀይረው ስለሚችል ትንኟን ለማጥፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊዘንብ ይችላል፡፡ በዚህም ውሀ በተለያዩ ቦታዎች ተጠራቅሞ የወባ ትንኝ ይራባል፡፡ ስለዚህ ወረርሽኝ ይኖራል በማይባል ወቅት ሊከሰት ይችላል፡፡ ለማሳያነትም በጎርፍ ምክንያት ኮሌራና የመሳሰሉ በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ኮሌራ በዚህ አመት አልተከሰተም፡፡ ባለፈው አመት ግን የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ በተለያዩ መንገዶች መከላከል ተችሏል፡፡
በወባ በሽታ ታሞ ከመታከም ውጪ የተመዘገበ ሞት አለመኖሩን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ በውሀ የሚተላለፉ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የአካባቢ እና የግል ንጽህና የመጠበቅ ልምዱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
በሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዶጊሶ እንዳሉት ወባ የህብረተሰቡ የጤና ችግር እንዳይሆን በዋናነት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የመከላከል ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ባለፈው አመት የወባ በሽታው ጫና የፈጠረባቸውን አካባቢዎች በመለየት ከወዲሁ ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችን የማፋሰስ ሥራ ተሰርቷል፡፡
አጎበር አጠቃቀምን ጨምሮ የወባ መከላከያ መንገዶችን በተገቢው መልኩ በመተግበር የወረርሽኙን ሥርጭት ለመከላከል የሚያስችል ሥራ መሰራቱን የገለጹት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ÷ ህብረተሰቡ እራሱን ከበሽታው እንዲከላከል በየአካባቢው የቅስቀሳና ግንዛቤን የማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ የበሽታው ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ህክምና እንዲያገኙም ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል፡፡
የበጋ ወቅት ሲመጣ ሙቀት ስለሚኖር ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። ለዚህም ነው የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ሥራ የሚሠራው። ከዚህ አንፃር ማህበረሰቡ ራሱን በወባ በሽታ ምክንያት ሊከሰት ከሚችል ህመምና ሞት እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ፣ በተለይ የሚዲያ ተቋማት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይታመናል።
የወባ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ማኅበረሰቡን በስፋት ማስተማር ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወባ ታክሞ የሚድን በሽታ ከመሆኑ አኳያ ቢቻል የወባ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል። ለዚህም አጎበርን ሁልጊዜ በአግባቡ መጠቀም፣ በገጠር አካባቢዎች የወባ ትንኝ ማጥፊያ ኬሚካል ከተረጨ በኋላ በእበት ወይም በአመድ ግድግዳን አለመለቅለቅ፣ የወባ መራቢያ አካባቢዎችን ማድረቅና የታቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስ ይገባል። በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሳይቻል ቀርቶ በበሽታው መያዝ ቢመጣ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም በማምራት አስፈላጊውን ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋል።
በወባ በሽታ ዙሪያ ህዝቡ በራሱ የበሽታውን ምንነትና የመተላለፊያ መንገዶችን በመገንዘብ ሊወስዳቸው የሚገባቸውን የመከላከያ እርምጃዎች እንዲወስድ የማስተማርና የማብቃት ተግባራዊ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ