“በክልሉ ባለፉት አመታት የተተከሉ ችግኞች ለኢኮኖሚ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ ሆነዋል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

“በክልሉ ባለፉት አመታት የተተከሉ ችግኞች ለኢኮኖሚ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ ሆነዋል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡

በክልሉ በአንድ ጀምበር የ60 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልላዊ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲ በእጃችን ታሪክን በደማቅ ቀለም የምንፅፍበት መርሃ ግብር ነው ብለዋል።

በመትከል ማንሰራራት ለልጆቻችን የተሻለ አከባቢን ለማውረስ የሚያስችል በመሆኑ መላው የክልሉ ነዋሪ ችግኝ በመትከል የድርሻው እንዲወጣም አሳስበዋል።

በክልሉ ባለፉት አመታት የተተከሉ ችግኞች ለኢኮኖሚ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ ሆነዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ችግኝ የሚተከልባቸው ስፍራዎችን ከሰውና እንስሳት ንኪኪ ነፃ ማድረግ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የክልሉ አብዛኛው አከባቢ ተራራማ መሆኑ ለጎርፍ ተጋላጭ አድርጎታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ተራሮች የስጋት ሳይሆኑ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ለማስቻል ኢንሼቲቭ ተቀርፆ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በሶልኮዋ ተራራ እየተተከለ ሚገኘው የአፕል ችግኝ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የአከባቢው ማህበረሰብ ሊጠብቀውና ሊንከባከበው እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አሳስበዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊና የዲላ ክላስተር አስተባባሪ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ብዝኃ ህይወት ከመጥፋት የመታደገ በአየር መዛባት ምክንያት የሚከሰት ድርቅን የመከላከል እና የተፈጥሮን ሚዛንን የመጠበቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲያችን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።

በክልሉ ባለፉት 6 አመታት 1 ቢሊዮን 422 ሚሊዮን 936 ሺህ 13 እንዲሁም በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 231 ሚሊዮን 869 ሺህ 283 የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ዶክተር መሪሁን ተናግረዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት በበልግ እና በክረምት የተከላ መርሃ-ግብሮች በ170 ሺህ 272 ሔክታር መሬት ላይ ከ500 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የመትከል ስራ አፅንኦት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱንም ዶክተር መሪሁን አብራርተዋል።

በዛሬው ዕለት በክልሉ በአንድ ጀምበር 60 ሚሊዮን ችግኞች በተመረጡ 973 ቦታዎችና ተፋሰሶች በ9 ሺህ 421 ሄክታር መሬት እንደሚተከልም የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል።

የሶልኮዋ ተራራን ማልማት በአከባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችንን ደህንነት መጠበቅ ነው ያሉት የቢሮው ኃላፊ መትከል ብቻውን ግብ ባለመሆኑ የተተከሉ ችግኞች እስኪፀድቁ ድረስ መንከባከብ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደገለፁት በዞኑ በአንድ ጀምበር 17 ሚሊዮን 403 ሺህ 480 ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የወላይታ ዞን አመራሮችና የቀበሌው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ምንጭ፡- የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ