በ58 ዓመቱ ወደ ጨዋታ ተመልሷል
በኢያሱ ታዴዎስ
በእግር ኳሱ ጉድ ተሰምቶ ማያልቅባት ብራዚል፣ አሁንም እንግዳ ነገር ማብሰሯን ቀጥላለች። እግር ኳስ በተጫወተባቸው 24 ዓመታት እንደ ተናፈቀ የጨረሰው ሮማሪዮ፣ ጫማ ከሰቀለ ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ጨዋታ እንደተመለሰ አየተነገረ ይገኛል።
የእንግሊዙ “ዘሰን” ከሰሞኑ ይዞት በወጣው መረጃ ከብራዚል የምን ጊዜም ጀግኖች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚጠቀሰው ሮማሪዮ፣ በ58 ዓመቱ የሰቀለውን ጫማ አውርዶ ዳግም ሊጫወት እንደተሰናዳ አስነብቧል።
ሮማሪዮ የመጨረሻ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወት ጨዋታውን ያካሄደው በአውሮፓዊያኑ 2009 ሪዮ ደዠኔሮ ላይ ለከተመው “አሜሪካ” ለተሰኘው ክለብ ነው። ጫማውን ከሰቀለ በኋላ በዚሁ ክለብ በፕሬዝደንትነት ሲያገለግል ቆይቷል።
አሁንም በፕሬዝደንትነቱ የቀጠለ ቢሆንም ከብዙ ጉትጎታ በኋላ የተጫዋችነት ውል ፊርማውን አኑሯል። የተፈራረመበትን ውልም በእጁ ይዞ የተነሳው ፎቶ ይፋ ተደርጓል። ዘሰን እንዳስታወቀው ሮማሪዮ ለውሉ ምንም ዓይነት ክፍያ አይፈጸምለትም። ክለቡን በነጻ ለማገልገል ነው የወሰነው። ሕልሙም በዚያው በክለቡ ከሚጫወተው ከ30 ዓመት ልጁ ሮማሪንሆ ጋር አብሮ መጫወት እንደሆነ ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰሙ ናቸው። የበርካቶቹ ግን “ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?” የሚለው አግራሞት ነው። ዜናውን በበጎ ጎኑ የተቀበሉት ደግሞ በሜዳ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በጉጉት ይጠባበቃሉ። የሮማሪዮ ክለብ አሜሪካ፣ በሪዮ ደዠኔሮ እግር ኳስ ሊግ በሁለተኛ ዲቪዚዮን እየተጫወተ ይገኛል።
ምን አልባትም ክለቡ ከሮማሪዮ ጋር ተያይዞ መነሳቱ በራሱ ሲሳይ ይዞ ሳይመጣ እንዳልቀረም ተሰምቷል። የማስታወቂያ ገቢን እና የአክስዮን ድርሻውን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ታምኗል።
በሙሉ ስሙ ሮማሪዮ ደሱዛ ፋሪያ በመባል የሚታወቀው የቀድሞ የግብ ቀበኛ፣ ከእግር ኳስ አፍቃሪያን ሕሊና ፈጽሞ የማይፋቅ ታሪክ ሰርቶ ነው ያሳለፈው። በ1985 በብራዚሉ ቫስኮ ደጋማ ጅማሮውን አድርጎ፣ ከዚያም በሆላንዱ ፒኤስቪ አይንድኦቭን ብቃቱን ካስመሰከረ በኋላ ወደ ታላቅነት ወደ አሸጋገረው ባርሴሎና ተጉዟል።
በካታላኑ ክለብ በ46 ጨዋታዎች 34 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ከስፔኑ ክለብ ቆይታ በኋላ የእግር ኳሱ ማጂላን ሆኖ ነው የሰነበተው አንዴ በሀገሩ፣ ሌላ ጊዜ በአውሮፓ፣ ሲያሻው ደግሞ በእስያ፣ በአውስትራሊያ እና በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ ክለቦች እየተዘዋወረ ተጫውቷል። ከመዳረሻዎቹም የኳታሩ አልሳድ፣ የስፔኑ ቫለንሲያ፣ የአሜሪካው ማያሚ፣ የአውስትራሊያው አሊዴይድ እና የብራዚሉ ቫስኮ ዳጋማ ክለቦች ይገኙበታል።
በአጠቃላይ የክለብ ቆይታውም በ698 ጨዋታዎች 542 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ ምህረት የለሽ አጥቂ ነው። በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን በተሰለፈባቸው 70 ጨዋታዎች 55 ግቦችን አስቆጥሯል። በ1994 የአሜሪካው ዓለም ዋንጫ ከቡድን አጋሮቹ ዱንጋ እና ቤቤቶ ጋር የነበረው አስደናቂ የሜዳ ውስጥ ጥምረት ብራዚል ዋንጫ እንድታነሳ ትልቅ ሚና ነበረው። የኮፓ አሜሪካ ዋንጫንም ሁለት ጊዜ ከቡድኑ ጋር አሳክቷል።
በአጠቃላይ በእግር ኳስ ሕይወቱ 1 ሺህ 2 (1002) ጨዋታዎችን አድርጎ 784 ይፋዊ ግቦችን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ ያስቆጠራቸው ግቦች ቁጥር እስካሁን ድረስ አጨቃጫቂ ናቸው። እንደ አር.ኤስ.ኤስ.ኤስ.ኤፍ መረጃ፣ ሮማሪዮ በ1 ሺህ 188 ጨዋታዎች 968 ግቦች አሉት።
በ2008 ሮማሪዮ ራሱ በለቀቀው ዲቪዲ ደግሞ 900 ግቦችን ሲያስቆጥር አስመልክቷል። ፊፋ በበኩሉ በይፋዊነት ከተጠቀሱት 784 ግቦች ውጪ ሌሎቹ የነጥብ ግቦች ወይም እውቅና ባላቸው ጨዋታዎች የተገኙ አለመሆናቸውን ይሟገታል።
ያም ሆነ ይህ ከኳስ ጋር እንደ አቦሸማኔ የሚምዘገዘገው እና ለተከላካዮች ፈተና ሆኖ በቀላሉ ግብ ማስቆጠር የሚቀናው ሮማሪዮ፣ በእግር ኳስ ታሪክ ከሚጠቀሱ የምን ጊዜም ምርጦች አንዱ ነው። እርሱን ለመሆን በመመኘት ስፖርቱን ተቀላቅለው ሕልማቸውን ያሳኩ ተጫዋቾች ቁጥርም የትየለሌ ነው።
አሁን ታዲያ ወደ አሰልጣኝነት ለመመለስ እንኳን በረፈደ ዕድሜው ወደ ተጫዋችነት መመለሱን ምን ይሉታል?
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
ሮድሪጎ ቤንታንኩር ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ታገደ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው