“አካል ጉዳተኛ ተቀባይ ብቻ አይደለም ሰጪም ነው” – አቶ ልብአገኘሁ ገ/ማሪያም
በሙናጃ ጃቢር
በጎነት መንፈሳዊነት ነው፤ ከፈጣሪ በረከት የሚገኝበት፤ ከዚህ የተነሳ በርካታ ሰዎች መልካም ሥራዎችን ሲሠሩ ይስተዋላሉ፡፡ የትኛውም ዓለም ላይ ችግሮች አይጠፉም፡፡ ብዙ ሰዎች ይቸገራሉ፤ ሀዘናቸው ይበረታል፣ ግን እኔን ባይ ሰዎችን ደግሞ ፈጣሪ ያዘጋጃል፡፡
“ለድሃ የሰጠ ለፈጣሪ እንዳበደረ ይቆጠራል” እንደሚለው የፈጣሪ ቃል ለሠራነው መልካም ሥራ ፈጣሪ እጥፍ አርጎ ይከፍለናል፡፡ በጎነት ዘር፣ ሀይማኖት፣ ቀለምና ጾታ አይገድበውም” ሲሉ ነው ሀሳባቸውን ማጋራት የጀመሩት፡፡
በደረሰባቸው አካል ጉዳት ምክንያት ከትምህርት ዓለም ርቀው ነበር፡፡ ደጋግ ሰዎች አይጠፉም እና ዛሬ ላይ የደረሱበት ደረጃ እንዲደርሱ የረዷቸው በጎነት ለራስ ነው የሚል እምነት ያላቸው አቶ ሙሉ ተገኝ የተባሉ ሰው ናቸው ሲሉም ምስጋናዬ ይድረሳቸው ብለዋል የዛሬ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን አቶ ልብአገኘሁ ገ/ማሪያም፡፡
አቶ ልብአገኘሁ ገ/ማሪያም ተወለደው ያደጉት በሀድያ ዞን በቀድሞ ስሙ ሚሻ ወረዳ በአሁን ደግሞ አመካ ወረዳ ፍገጃ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዱና በሚባል መንደር ነው፡፡ ልበ-ብርሃን የሆኑት ባለታሪካችን በሀድያ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ መምሪያ ውስጥ ባለሙያ ሲሆኑ ባለትዳር እና የ4 ልጆች አባት ናቸው፡፡
የአይን ብርሃናቸውን ያጡት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ባልታወቀ ምክንያት ነበር፡፡ ለቤተሰቦቻቸው የመጀመሪያ ልጅ ስለሆኑ ይንከባከቧቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አይነ ስውር ነው በቃ ምንም መሥራት አይችልም በሚል እምነት ወደ ህክምና ተቋም አልወሰዷቸውም ነበር፡፡
ከፍ ካሉ በኋላ ግን ከውጭ በመጡ የህክምና ባለሙያዎች ባገኙት ህክምና በፊት ሙሉ በሙሉ ጭልም ያለው እይታቸው በተወሰነ ደረጃ ቀለም መለየት መቻላቸውን ገልፀውልናል፡፡
ልጅ እያሉ ለወላጆቻቸው ውሃ እየቀዱ፣ ሣር እያጨዱ፣ ከገደል ገደል እየዘለሉ እና እየተላላኩ ከሰፈር እኩዮቻቸው ጋር ምንም ሳይገድባቸው እየተጫወቱ ነበር ያሳለፉት፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን እኩዮቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እሳቸው ሰፈር ሲጠብቁ መዋላቸው ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ያወሳሉ፡፡ “አይነ ስውር በመሆኔ ምንም መሥራት አልችልም ብዬ ነበር በወቅቱ የማስበው፡፡ ይህም ውሎ ሲያድር የብቸኝነት ስሜት በርትቶብኝ ልቤ በሀዘን እንዲሰበር አድርጓል” ሲሉ ያለፉትን ከባድ ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡
“ከእለታት በአንዱ ቀን ግን የልብ ስብራቴን የሚጠግን ዕድል ተፈጠረ፡፡ የአንድ ጎረቤታችን ወንድም ከሌላ ሀገር ሊጠይቃት መጥቶ ነበር፡፡ እናቴም ልትጠይቃት ስትሄድ አብሬያት የመሄድ እድል ተፈጠረ፡፡
“ወንድሟ አቶ ሙሉ ተገኝ የሚባሉ ሲሆን አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ ልክ እንዳዩኝ ነበር ልባቸው ያዘነው፡፡ አዝነው ግን ዝም አላሉም፤ ወድያው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማሰብ ጀመሩ፡፡” ሲሉ ስለሂደቱ ዛሬ የሆነ ያህል እያስታወሱ ይናገራሉ፡፡
እኝህ በጎ ሰው አቶ ልብአገኘሁን ለመርዳት ብዙ ርቀት ተጓዙ፡፡ ከብዙ ውጣውረድ በኋላ አዲስ አበባ አይነ ስውራን ትምህርት ቤት እድሉን እንዲያገኙ አደረጉ፤ ነገር ግን “ኮታ ሞልቷል” በሚል ወደ ወላይታ ሶዶ ኦቶና አይነ ስውራን ትምህርት ቤት አዘዋወሯቸው፡፡
አቶ ልብአገኘሁም በብዙ መሰናክል የተሳካውን ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ መከታተል ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ደብል የመውጣት እድል ነበረ እና እሳቸውም ደብል እየመቱ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተምረው አጠናቀቁ፡፡ ከዚያም ድርጅቱ ከ6ኛ ክፍል በኋላ የማስቀጠል አቅም ስላልነበረው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ፡፡
“በዚያን ጊዜ የማህበረሰቡ አመለካከት ጥሩ ስላልነበር አይናማ ተማሪዎች የሚማሩበት ት/ቤት ገብተን መማር አንችልም ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ ሁኔታ ግን ተለውጧል፡፡ በሰዓቱ ግን የትኛውም ትምህርት ቤት ሊቀበለኝ ዝግጁ አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ለአንድ ዓመት ለማቋረጥ ተገደድኩ፡፡ በሰዓቱ በጣም ነበር የተሰማኝ” ሲሉ አጫውተውናል፡፡
ለአንድ ዓመት ያህል ካቋረጡ በኋላ አዲስ አበባ አካቶ ትምህርት ይሰጥ ስለነበር ወላይታ አብረዋቸው የተማሩ ጓደኞቻቸው አዲስ አበባ ይማሩ ስለነበር እንዲመጡ ይገፏፏቸው ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ “ቁጭ ብዬ ምን እሰራለሁ መሄድ አለብኝ በሚል ወሰንኩ” ሲሉ አዲስ አበባ የሄዱበትን አጋጣሚ አውስተውናል፡፡
አቶ ልብአገኘሁ በባህሪያቸው ደፋር ስለነበሩ ምንም ዘመድ ወደሌለበት አዲስ አበባ ኪሳቸው ውስጥ ያላቸውን 500 ብር ብቻ ይዘው አቀኑ፡፡
ጓደኞቻቸው የሚማሩበት 4 ኪሎ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ገብተው መከታተል ጀመሩ፡፡ የሚረዳቸው አካል ስላልነበረ ሎተሪ እያዞሩ ነበር የሚማሩት፡፡ በሚያገኙት ሳንቲም አፍንጮ በር አካባቢ በጋራ የሚታደርበት ቤት ለማደሪያ እየከፈሉ ያድሩ ነበር፡፡ ሲያገኙ በልተው ሲያጡ ደግሞ ጾማቸውን እያደሩ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ተምረው አጠናቀቁ፡፡
በ1994 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና 3 ነጥብ 6 አምጥተው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሶሺዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተከታትለው በ1998 ዓ.ም መመረቅ ችለዋል፡፡
አቶ ልብአገኘሁ በባህሪያቸው ከሰው ጋር ተግባቢ ሲሆኑ የትኛውንም ማህበራዊ መስተጋብር ለመፈፀም አይፈሩም፡፡ ይሁን እንጂ “እኛ እንችላለን ብለን ብናምንም አንዳንድ ጊዜ ከማህበረሰቡ የሚመጡ አመለካከቶች እምነቶቻችን እንዲሸረሸሩ ያደርጋሉ፡፡ ለቅሶ፣ ሠርግ፣ መጋበዝ፣ አብሮ መብላት እና አብሮ መጠጣት እንችላለን፡፡ ሰዎች የረሱት አካል ጉዳተኛ ሁሌ ተቀባይ ብቻ ሳይን ሰጪም ጭምር መሆኑን ነው” ሲሉ የህብረተሰቡ ግንዛቤ መሻሻል እንዳለበት ያነሳሉ፡፡
“አካል ጉዳተኛ ማለት ሁሌ ተመፅዋች ሳይሆን የልማት ተቋዳሽ፤ በሀገሪቱ በሚደረጉ የትኛውም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ላይ ተሳታፊ ነው እንጂ ሁሌ ጥገኛና ተቀባይ ተብሎ መወሰድ የለበትም፡፡ በመሆኑም ማህበረሰቡ ይሄን አመለካከት መቅረፍ አለበት” ሲሉ አቶ ልብአገኘሁ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርስቲ እያሉ የገጠማቸውን ሲያወሱ፡- “አካል ጉዳተኛ መዝናናት የሚችል የማይመስላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ሻይ ቡና ለማለት ካፌ ገብቼ በተቀመጥኩበት አስተናጋጁ መጣና ጋሼ ፈጣሪ ይስጥልን ይሄ ካፌ ነው ብሎ ሊያስወጣኝ ሞከረ፤ እኔ ግን በሁኔታው ከመናደድ ይልቅ ሞራሌ ተነክቶ አዘንኩ፡፡
“ሥራ ከጀመርኩ በኋላ ደግሞ ለቅሶ ቤት ስሄድ ለምን ለፋ፣ እሱን ለምን ታስለፋላችሁ? የሚሉ ቃላቶች አግባብ አልነበሩም” ሲሉ ማህበረሰቡ ባለማወቅ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ አውግዘዋል፡፡
ለዚህ ግን “አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም ብለን የምናወራ ብቻ ሳይሆን አለመቻል አለመሆኑን በግልፅ ማሳየት አለብን፡፡ ሰዎች ወደእኛ እንዲመጡ መጠበቅ የለብንም፤ እኛ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ አለብን፡፡ ማንኛውም ሰው ሲሳሳት መንገድ ይጠይቃል፤ ልክ እንደዚሁ አካል ጉዳተኛ ጉዳቱን ይዞ መቀመጥ የለበትም የቸገረውን ነገር መጠየቅ አለበት፡፡
“ለምሳሌ ብዙ ታሪክ የሠሩ አካል ጉዳተኞች አሉ፤ አካል ጉዳተኛ መሆን አለመቻል አይደለም ስንል ዝም ብለን አይደለም፤ በሥራ ማሳየት ነው፡፡ ለምሳሌ ዓይን ባጣ እጅ እና እግር አለኝ፤ ስለዚህ ያለኝን የስሜት ህዋሳት ተጠቅሜ መሥራት መቻል አለብኝ፡፡ ተስፋ መቁረጥ የለብኝም፡፡
“መሰናክሎች እንዲወገዱ መሞገት አለብን፤ እንዴት ነው የምንሞግተው ካልን ማህበራትን በማደራጀት ከመሠል አካላት ጋር አንድ ላይ በመሆን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ የማህበረሰቡ አመለካከት እንዲቀየር በጋራ መጮህ አለብን” ይላሉ፡፡
“አካል ጉዳተኛ ስለሆንን ብቻ ዝም ብለን ተመጽዋች መሆን የለብንም፡፡ ሰዎች ‹ዓሣ ሁል ጊዜ ከሚያጎርሱን ይልቅ የዓሣ አጠማመድ ቢያሳዩ መልካም ነው› የሚል አባባል አለ፡፡ ሰዎችም ሁል ጊዜ ከንፈር እየመጠጡ ሳንቲም ከመስጠት ይልቅ በዘላቂነት ከችግር የሚላቀቁበት ነገር ማድረግ ነው እንጂ አልባሳትና ሳንቲም እየሰጠን የምንቆይ ከሆነ ሁሌም ተመጸዋች ነው የምንሆነው፡፡
“ስለዚህ አካል ጉዳተኛ በራሱ እንዲቆም ማድረግ እና ራሱን በራሱ እንዲችል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ቤት ውስጥ ሰባት ሰው እያስተዳደርኩ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ለመሰረተ ልማት ሲባል መዋጮ አዋጣለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ከራሴ አልፌ ለሌላው እየተረፍኩ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ይበልጥ እንድናደርግ መሰረተ ልማት መመቻቸት አለበት፡፡
“ማህበራችን በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በስፋት የሚሠራ ሲሆን የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ይጠሩናል፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስለ አካል ጉዳተኞች እንሟገታለን” ሲሉ ስለማህበራቸው የሥራ እንቅስቃሴ አጋርተውናል፡፡
“የአካል ጉደተኞችን ጉዳይ በማስተጋባት ጠንካራ ሥራ ከሚሰሩ ባለደርሻ አካላት አንዱ የአካል ጉደተኞች ማህበር ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ፌደሬሽን አለ፤ በክልል እና በዞን ደረጃ ማህበራት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሥራዎችን ለመሥራት ብዙ ጊዜ በጣም እንቸገራለን፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የምናገኘው የበጀት ምንጭ አለመኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ሴቶች ሊግ እና ወጣቶች ሊግ ከመንግስት የሆነች ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል፤ የኛ ማህበር ግን ምንም አይነት ድጋፍ እያገኘ አይደለም” ሲሉ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
“የአካል ጉዳተኛ ማህበር ማለት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማስጠበቅ የቆመ ተቋም ነው፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ ቁስል እስካለበት ድረስ ከሌሎች ማህበራት ይልቅ የበለጠ ለአካል ጉዳተኛ ማህበራት ቅድሚያ በመሥጠት መብታቸው እንዲከበር ባለቤት ሆኖ እንዲሰራ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተገቢውን ድጋፍ በመሥጠት ቢያጠናክሩን ጥሩ ነው” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“ለምሳሌ እስካሁን ሀዋሳ ላይ የሚገኘው ቸሻየር ኢትዮጵያ ባሉት ቅርንጫፍች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርግልን ነበር፡፡ እንደዚህ ያሉ ድርጅቶች ቢበዙ የአካል ጉዳተኞች ማህበርን ያጠናክሩ ነበር” ብለዋል፡፡
“በሌላ በኩል ማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ሊቀረፍ ይገባል፤ አሁንም ቢሆን አካል ጉዳተኞች ይችላሉ፡፡ አካል ጉዳተኝነት በፆታ፣ በዕድሜ እና በቀለም የሚገደብ አይደለም፡፡ አካል ጉዳት በደቂቃ ውስጥ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነገ በኔ በሚል እሳቤ እኔ በነሱ ቦታ ብሆን ምን እሆን ነበር ብሎ ማህበረሰቡ ማሰብ አለበት፡፡ ለዚህም የወላጅ አስተሳሰብም መቀየር አለበት፡፡
“አካል ጉዳተኛ ልጆች ስለወለድን ብቻ እንደ መርገም ቆጥረን ልጆቻችንን ቤት ውስጥ ማስቀመጥ የለብንም፡፡ ከዛ ይልቅ የትምህርት እና የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማገዝና ማበረታታት አለብን፡፡ ወላጅ ልጁ አካል ጉዳት ስለገጠመው ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ ልጁን ለቁም ነገር ለማድረስ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ቆራጥ በመሆን አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለበት ሲሉም” ወላጆችን መክረዋል፡፡
“በተለያዩ ጊዜያት የሚዲያ አካላት ይጠይቁናል፤ ይህም በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም፤ ምክንያቱም ከ 20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ጋር ይደርሳል፡፡ መድረሱ ደግሞ አመለካከትን ይቀይራል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ሙሉ ተገኝን ጨምሮ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ በጎ ነገር በማድረግ ላገዙኝ አካለት ምስጋናዬ ይድረስ ብለዋል፡፡
More Stories
በርካታ የቀለም ልጆችን ያፈሩ መምህርት
“በህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርቡባቸውን አብዛኛዎቹን ችግሮች መፍታት የተቻለበት አመት ነበር” – አቶ ሳሙኤል ዳርጌ
“ወርቃማ የሚባለውን ዘመን በመምህርነት በማሳለፌ ደስተኛ ነኝ” – መምህር መንግስቴ አየለ