በርካታ የቀለም ልጆችን ያፈሩ መምህርት
በሐና በቀለ
ሰኔ 30 በትምህርት ዓለም ላለፍን አብዛኞቻችን የተለያዩ ትዝታዎችን ያስተናገድንባት ቀን ናት፡፡ ዓመቱን ሙሉ ተምረን ካርድ የምንቀበልበት በመሆኗ በትምህርታችን ወደሚቀጥለው ክፍል ከማለፍ እና መውደቅ ባልተናነስ ከምንወዳቸው መምህራንና ጓደኞቻችን ጭምር ለመለያየት የምንገደድበት በመሆኑ ስሜታችን መረበሹ አይቀርም፡፡
በዛሬው የእቱ መለኛ አምዳችን በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ስለነበሩ መምህርት በማንሳት ያለፉበትን የሕይወት መንገዳቸውን በጥቂቱ ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡
ባለታሪካችን መምህርት አልማዝ ደነቀ ይባላሉ፡፡ በሲዳማ ክልል አሮሬሳ አካባቢ የተወለዱ ሲሆን አባታቸውን በልጅነታቸው በሞት ስላጡ አጎታቸው አቶ መኮንን ልዑል ጋር ማደጋቸውን ይናገራሉ፡፡ አጎታቸው በቀድሞው አርሲ ክፍለ ሃገር ይኖሩ ስለነበር ትምህርታቸውን የጀመሩትም አርሲ አካባቢ ነው፡፡
የአጎታቸው የሥራ ባሕሪ ከቦታ ወደ ቦታ የሚያዘዋውራቸው በመሆኑ የተለያዩ ከተሞች ተምረዋል፡፡ በአብዛኛው በቀድሞው አርሲ ክፍለ ሃገር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቢሆንም የተማሩት የ1ኛ እንዲሁም የ9 እና 10ኛ ክፍልን በይርጋዓለም ከተማ ነው የተማሩት፡፡
በ1964 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ በመመረቅ የሥራ ዓለምን ተቀላቀሉ፡፡ ከዚያም ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ክብረመንግስት ራስ ብሩ እና መጋዶ ትምህርት ቤት ካስተማሩ በኋላ ወደ ወላይታ በማቅናት በሙያቸው አገልግለዋል፡፡
ወላይታ ሶዶ በነበራቸው ቆይታ በወቅቱ ኪዳነ ምህረት እና ወላይታ ሶዶ ጊዮርጊስ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ሙዚቃን ጨምሮ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች ለበርካታ ዓመታት አስተምረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በወላይታ ሶዶ በነበሩበት የመጨረሻ ዓመታት የ6ኛ ክፍል የአማርኛ እና ሒሳብ መምህር በመሆን እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ ማገልገላቸውን የሥራ ማስረጃቸው ያሳያል፡፡ ከዚያም በ1971 ዓ.ም ወደ ሀዋሳ በመዛወር ጡረታ እስከወጡበት እስከ ታሕሥሣ 2001 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
መምህርት አልማዝ በ1974 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ገበያ ዳር ትምህርት ቤት ሲመሰረት ከነበሩ መምህራን አንዷ እንደሆኑ በቆይታችን ወቅት ነግረውናል፡፡
በወቅቱ ታቦር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው ለ2 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ የ2ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች ብዛት ስለነበራቸው የተወሰኑ ተማሪዎች እና 20 መምህራን ወደ ገበያ ዳር በመሄድ ትምህርት ቤት እንዲከፈት ምክንያት እንደሆነ ነው የገለፁልን፡፡
ከዚያም በሂደት ትምህርት ቤቱ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሆነ ያስታውሳሉ።
ወደ ሀዋሳ መዘዋወራቸውን ተከትሎ ካሳኩት ነገር መካከል አንዱ በእፅዋት ሳይንስ (Plant Science and Technology) በዲፕሎማ መመረቃቸው መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ በቋሚነት የሳይንስ መምህር ሆነው ቢመደቡም የሳይንስ እና የሙዚቃ ትምህርትን በጣም ስለሚወዱ ሙዚቃን ደርበው ያስተምሩ ነበር፡፡
ብዙ ተማሪዎቻቸውን ስለ ኖታና ሪትም አጠባበቅ እንዲሁም የአርቲስት ጥላሁን ዘፈኖችን ማሳያ በማድረግ ሙዚቃ ያስተምሩ እንደነበር ነግረውናል፡፡
በመምህርነት በቆዩባቸው ዓመታት እንደገጠመኝ የሚያነሱት አልያም ያስገረማቸው ነገር ካለ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-
“ገበያ ዳር ትምህርት ቤት በማስተምርበት ወቅት የገበያ ዳር ሰፈር ልጆች ሰኞ እና ሃሙስ ትምህርት ይቀሩ ነበር፡፡ በዚያ እቸገር ነበር፤ በተለይ አንድ ልጅ እኔ ሙዚቃ በማስተምርበት ወቅት ሁሌ አይገኝም ነበር፡፡
“እንደ አጋጣሚ ሆኖ ክፍለ ጊዜ የነበረኝ ሰኞ እና ሃሙስ ስለነበር እሱ ደግሞ ስለማይመጣ ሳይማር ትምህርቱ አለፈው። ከነበረው ችሎታ አንፃር ቢማር ብዬ ሁሌ እቆጫለሁ፤ ነገር ግን በኋላ ስሰማ የግድ ገበያ መነገድ ስለነበረበት ነው ክፍለ ጊዜው የሚያመልጠው፡፡” ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡
ሌላኛው የማይረሱት ገጠመኛቸውንም ሲያስታውሱ፡-
“ክብረመንግስት በማስተምርበት ወቅት የመምህራን እጥረት ስለነበር፤ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ 1ኛ ክፍል ጠዋት አስተምሬ ከሰዓት ደግሞ 2ኛ እና 3ኛ ክፍልን ለማስተማር እመለስ ነበር፡፡ ተማሪዎቼን እወዳቸው ስለነበር ነው እንጂ ያ ወቅት ለእኔ ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቼ ተምረው እንዲያልፉ ስለምፈልግ ዋጋ በመክፈል አስተምሬያቸዋለሁ፡፡
“ከዚያም በተጨማሪ አማርኛ የማይችሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በሚመጡበት ወቅት ትምህርቱ በአማርኛ ስለሆነ አይረዱም። ስለዚህ እነሱን ደግሞ ለብቻ ኦሮምኛ ባልችልም በሚረዱት መልክ ጊዜ ሰጥቼ አስተምራቸዋለሁ፡፡
“ከዚያም በተጨማሪ ከተማሪዎች ጋር እንዲግባቡ ስለምፈልግ ሆን ብዬ የክፍል አለቃ አደርጋቸው ነበር፡፡ ከነዚያም ተማሪዎቼ መካከል በሆነ ወቅት አንደኛው ተማሪዬ የክብረመንግስት ጤና ጣቢያ ኃላፊ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
“በወቅቱ የነበሩ ርዕሰ መምህሩን እስከ 6ኛ ክፍል ተማሪዎቼን አስተምሬ ሚኒስትሪ እንዲፈተኑ ላብቃቸው ብዬ አማክሬው ነበር። ነገር ግን ሃሳቤ ጥሩ እንደሆነ ነግሮኝ በዚህ መልኩ ማስቀጠል እንደማልችል ስለተነገረኝ መቀጠል አልቻልኩም፡፡” ሲሉ ያሳለፉትን ጊዜ አውግተውናል፡፡
ዛሬ መምህርት አልማዝ ያስተማሯቸው ተማሪዎች ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮች፣ መምህራን፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የቢሮ ሃላፊዎች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም በተለያዩ መስክ የተሰማሩ ዜጎች ሆነዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያገኝዋቸው አክብሮታቸውንና ፍቅራቸውን ይገልፁላቸዋል፡፡
እኛም ለመገናኘት እና ይህን ቃለመጠይቅ ለማድረግ ምክንያት የሆነው ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገ የቀድሞ ተማሪያቸው ሰኔ 30ን ምክንያት በማድረግ የላከላቸውን መልዕክት ለማድረስ በተዘጋጀው የምስጋና ፕሮግራም ነው፡፡
መምህርት አልማዝ ያስታወሳቸውን የቀድሞ ተማሪያቸው አመስግነው እዚህ ለመድረሳቸው ዋነኛ ተዋናይ በመሆን እንደ አባት አሳድገው ትልቅ ደረጃ ያደረሷቸውን አጎታቸው በሕይወት ባይኖሩም አቶ መኮንን ልዑልን አመስግነዋል፡፡
የአብራካቸው ክፋይ የሆኑ ልጆቻቸውን አስተምረው ለቁም ነገር ማብቃታቸውን የገለፁት መምህርት አልማዝ ሁሉም ራሳቸውን ችለው ኑሯቸውን እየመሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ዛሬ እነሱ በተራቸው እየጦሯቸው ደህና የሚባል ኑሮ እየኖሩ መሆኑን ገልፀው እናንተም በልጆቻችሁ አግኙ ሲሉ መርቀዋቸዋል፡፡
የቀለም ልጆቼም በወቅቱ የቀጣኋችሁ ጥሩ ደረጃ እንድትደርሱ በማሰብ መሆኑን ዛሬ መረዳታችሁ አይቀርምና ይቅር በሉኝ ሲሉ እንደሚወዷቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል”
የአዲስ ዓመት ተስፋ
“ግድቡም አለቀ ÷ መስከረምም ጠባ…”