ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልላዊ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ አስጀመሩ

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልላዊ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ አስጀመሩ

በክልሉ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዳዉሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ፣ ጎርቃ በርሳ አስጀምረዋል።

በማብሰሪያ መርሀግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢንሼቲቭ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የምርትና ምርታማነት ጭማሪ እንዲኖር አቅም እንዲጨምር እያገዘ ይገኛል ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥ ከመቋቋም ባሻገር የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ችግኝ ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ምግብ እና የእንስሳት መኖ በመኾኑ መትከልና በልዩ ትኩረት መንከባከብ ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

አለም እያስደመመ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢንሼቲቭ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የከርሰ ምድር እርጥበት እንዲኖር በማስቻልና የአፈር መከላትን በመከላከል የምርትና ምርታማነት ጭማሪ እንዲኖር አቅም እንዲጨምር እያገዘ እንደሆነም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል።

ችግኝ መትከል ሀብት እንደ መትከል ተቆጥሮ ተግባሩ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደገለጹት የ2017 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ ‘‘በመትከል ማንሰራራት’’ በሚል መሪ ቃል እንደ ክልል 21 ሚሊየን የደን፣ ጥምር ደንና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸዉ ችግኞች ይተከላሉ።

ለተከላው 6 መቶ 54 የተከላ ሳይቶች 7 ሺህ 9 መቶ 24.90 ሄክታር መሬት የሚሸፈን መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች ለተከላ የሚሆኑ ችግኞችን የማዘጋጀትና የተከላ ቦታ ጉድጓድ ዝግጅት የተከናወነ ሲሆን በአንድ ጀንበር ተከላዉም ከ1 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

በበጋ ወራት በተካሄዱ የአፈርና ውኃ ጥበቃዎች ሥራዎች በክረምት ወራት ሥነ ሕይወታዊ ሥራዎች እየተካሄደ ይገኛሉ።

የዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ ልማት የመንግሥትና የፓርቲ ኢንሼቲቭ የሆነው አሁን ላይ ሕዝባዊ ቅቡልነትን እያገኘ በመምጣቱ በውጤት የታጀበ ሂደት እየፈጠረ ነው።

በመሆኑም በዞኑ በአንድ ጀምበር 7.5 ሚሊዮን ችግኞቾ የሚተከሉ ሲሆን ከ3 ሺህ 23 ሄክታር የሚበልጥ ማሣ በችግኞች እንደሚለማም ይጠበቃል።
በዞኑ የታርጫ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበሻው ጉተማ በዕለቱ በ10 ሄክታር ማሣ በሚሸፍን ከ26 ሺህ በላይ የተለያዩ ዘረፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን የተተከሉ ሲሆን የጥበቃና ክብካቤ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኙ ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ከምርቱ ተጠቃሚ መሆን እየቻሉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡-መሣይ መሠለ