“በህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርቡባቸውን አብዛኛዎቹን ችግሮች መፍታት የተቻለበት አመት ነበር” – አቶ ሳሙኤል ዳርጌ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ይባላሉ፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ በቆይታችን በጤና ዘርፍ በበጀት አመቱ የተሰሩ ስራዎችንና የተመዘገቡ ውጤቶችን ጨምሮ ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በመለሠች ዘለቀ
ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሳሙኤል፡- ስለተሰጠኝ እድል እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- በበጀት አመቱ በጤና ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትና የተመዘገቡ ውጤቶች እንዴት ይገለጻሉ?
አቶ ሳሙኤል፡- የ2017 በጀት አመት ስራ ስንጀምር የ2016 እቅድ አፈጻጸምን በመገምገም ነበር ወደ ተግባር የገባነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የድጋፍና ክትትል ስምሪት ወስደን ያሉ ችግሮች፣ ጥንካሬዎችና ቀጣይ መሰራት አለበት የሚለውን ግምገማ ካደረግን በኋላ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብ ስምምነት በማድረግ ነው የጀመርነው። ከዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋርም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ስምምነት በመፍጠር ነው ወደ ተግባር ነው የገባነው፡፡
በዚህም የክልሉን የጤና ዘርፍ ውጤታማነት ለማሳደግ እና የዜጎችን ጤና ማሻሻል የሚያስችል እቅድ በማዘጋጀት ጤናን የማበልጸግ፣ በሽታዎችን የመከላከል እና የፈውስ ህክምና ላይ በማተኮር በርካታ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል።
የበጀት ዓመቱ እቅድ ከመዘጋጀቱ አስቀድሞ በ2016 በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ የነበሩ ችግሮችን በዝርዝር በመለየት የዋና ዋና ችግሮች ትንተና በማከናወን እና የተለዩ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያችሉ ስልቶችና ቁልፍ ተግባራት ለይቶ በማስቀመጥ፣ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እቅድ በማዘጋጀት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና መዋቅሮች ጋር መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ተግባር ምዕራፍ ተገብቷል፡፡
በሂደቱም የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት ጉልህ ሚና ያላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ንቅናቄዎች እና የውይይት መድረኮች እስከ ጤና ተቋማትና ቀበሌዎች ድረስ የተካሄዱ ሲሆኑ ለዓመታት የዘለቁ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተንቀሳቅሰናል፡፡
የጤና ስርዓት ግንባታና ተቋማትን ማጠናከር ላይ በማተኮር ተከታታይና ችግር ፈቺ የሆኑ ድጋፋዊ ክትትሎች በሁሉም መዋቅሮች እስከ ቤት ለቤት ድረስ የማካሄድ፣ ችግሮችን በየአካባቢው በመፍታትና ግብረ መልስ በመስጠት እንዲሁም የተግባራት አፈጻጸሞችን በየወቅቱና በየደረጃው በመገምገምና ምላሽ በመስጠት በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመሩ ተደርጓል፡፡
ንጋት፡- የጤና ኤክስቴንሽን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለጻሉ?
አቶ ሳሙኤል፡- በበጀት ዓመቱ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ፍኖተ ካርታ ትግበራ ለማጠናከር በክልሉ ውስጥ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እስከ ቀበሌ ድረስ በተፈጠሩ የንቅናቄ መድረኮች ለሚመለከታቸው አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ግንዛቤ የማስጨበጫ መድረክ በማዘጋጀት ሰፊ ሥራ መስራት ተችሏል። በዚህም ከ50 በላይ ወረዳዎች በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ላይ ትግበራ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል። በቀጣይም ወደ ሌሎች ወረዳዎች ለማስፋት ይሰራል፡፡ ከጤና ኬላዎች አገልግሎት አሠጣጥ አንፃር በበጀት ዓመቱ ሁለት ተጨማሪ አጠቃላይ ጤና ኬላዎች ስራ በማስጀመር በአጠቃላይ 8 አጠቃላይ ጤና ኬላዎች እና 27 መሠረታዊ ጤና ኬላዎች ከጤና ኤክስቴንሽኖች በተጨማሪ ሌሎች የጤና ባለሙያ ተመድቦ በጥራቱና በደረጃ ከፍ ያለ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
ንጋት፡- የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ሳሙኤል፡- የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስና ጤናን ለማጎልበት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነፍሰ ጡር እናቶች ክትትል 4 ጊዜ ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ ስምንት ጊዜ ክትትል የሚያደርጉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ የጤና ኬላዎችን ስታንዳርድ በመቀየር የባለሙያዎች ስብጥር በማድረግ የነፍሰ ጡር እናቶች ክትትል አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
በበጀት ዓመቱ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የተጠቀሙ ሴቶች ሽፋን ከ81 ከመቶ ወደ 86 ነጥብ 4 ከመቶ በማሳደግ ከባለፈው ዓመት አፈጻጸም በ6 ነጥብ 4 ከመቶ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
የተወሳሰበ የእርግዝና ችግር ያለባቸው እና መስፈርቱን ለሚያሟሉ እናቶች የማረፊያ ቤት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እና ግብአት የማሟላት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም 260 ማቆያ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ 218 የማቆያ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በሁሉም የጤና ተቋማት ያሉ የእናቶች ማቆያ 85 ከመቶ የደረሰ ሲሆን በቀሩት ተቋማት ላይ ከክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ጋር አቀናጅተን እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ የማዳረስ ስራ ይሰራል፡፡
ንጋት፡- በሰለጠኑ ባለሙያዎች አገልግሎቱን ከማዳረስ አንፃር የተሰራው ሥራስ ምን ይመስላል?
አቶ ሳሙኤል፡- በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች 200 ሺህ 786 (87.9 ከመቶ) እናቶች የወሊድ አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ለበጀት ዓመቱ ከታቀደው 205 ሺህ 491 (90 ከመቶ) አንጻር ወደ 97 ነጥብ 7 ከመቶ መፈጸም ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል 184 ሺህ 941 እናቶች የድህረ ወሊድ አገልግሎትን በወለዱ በመጀመሪያ 48 ሰዓት ውስጥ እንዲያገኙ በማድረግ ሽፋኑን ከ67 ከመቶ ወደ 85 ነጥብ 2 ከመቶ በማሳደግ ከታቀደው አንፃር አፈጻጸሙ 105.2 ከመቶ ደርሷል፡፡
ከዚህም ባሻገር 11 ሺህ 895 ጨቅላ ህፃናት የጽኑ ህመም ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ ሽፋኑን ከ65 ከመቶ ወደ 70.4 ከመቶ በማሳደግ ከታቀደው አንጻር ደግሞ 88 ከ መቶ መፈጸም ተችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ውስጥ የክትባት አገልግሎት ማግኘት ከሚገባቸው እድሜያቸው ከ1 ዓመት በታች ከሆኑ 210 ሺህ 514 ህፃናት መካከል የፔንታቫለንት ሦስት ክትባት የተከተቡ ሽፋን 225 ሺህ 231 (107.4 ከመቶ)፣ የኩፍኝ ክትባት 2ኛ ዶዝ የተከተቡ ህፃናት ሽፋን 210 ሺህ 293 (99.9 ከመቶ) ሲሆን ለበጀት ዓመት ከታቀደው198 ሺህ 514 (94.3 ከመቶ) አንጻር 105.9 ከመቶ መፈጸም ተችሏል፡፡
ከክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን በተፈጥሮ እግረ ቆልማማ ሆነው የተወለዱ ከ400 በላይ ህጻናት እንዲሁም የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ያለባቸውን ከሌሎች ክልሎችም ጭምር መጥተው ከትራንስፖርት ጀምሮ ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
በዚህም እቅድ ማስፈጸም ብቻ ሳይሆን የወላጆች ምርቃትንና እርካታን ያገኘንበት አመት ነው፡፡ በክትባት ዘርፍ በጥራትም በተደራሽነትም ውጤታማ ስራ መስራት ችለናል፡፡ በዚህም ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስተር የእውቅና ሽልማት ተበርክቶልናል፡፡
በሌላ በኩል በአማካይ 181 ሺህ 800 እናቶች በየወሩ የስርዓተ-ምግብ ደረጃ ልየታ የተደረገላቸው ሲሆን በዚህም ሽፋኑን ከ66 ከመቶ ወደ 79.6 ከመቶ ማሳደግ ተችሏል። የስርዓተ-ምግብ ልየታ ስራ ከተሰራላቸው እናቶች ውስጥ በአማካይ 18 ሺህ 698 (10.3ከመቶ) በመካከለኛ ደረጃ የምግብ አለመመጣጠን የተጎዱ ተለይተው ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ በኩል ድጋፍ እንዲያገኙ የማቆራኘት እና በአንድ ሺህ ቀናት ዙሪያ የአመጋገብ ምክር እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡
ንጋት፡- የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ሳሙኤል፡- በበጀት ዓመቱ የኤች አይ ቪ ኤድስን ሥርጭት መከላከል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለአብነትም በዓመቱ ለ320 ሺህ 907 ያህል ሰዎች የኤች አይ ቪ ምርመራ ለማድረግ ታቅዶ 344 ሺህ 328 በማከናወን የዕቅዱን 107 ነጥ 3 ከመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 225 ሺህ 505 እናቶች የኤች አይ ቪ የምርመራ አገልግሎት ያገኙ ሲሆን አገልግሎት ማግኘት ከሚገባቸው አንጻር ሽፋኑን ከ90 ከመቶ ወደ 98.8 ከመቶ ለማድረስ ከታቀደው አንጻር ከመቶ ፐርሰንት በላይ በማከናወን መሻሻል ታይቷል፡፡
ንጋት፡- የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ሥራዎች ምን ይመስላል?
አቶ ሳሙኤል፡- የወባ ስርጭት እንደ ሀገር የጨመረበት አመት ቢሆንም በክልሉ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለ1 ሚሊዮን 884 ሺህ 171 ያህል ሰዎች በወባ በሽታ ስሜት የላቦራቶሪ እና የአር.ዲ.ቲ የደም ምርመራ የተከናወነ ሲሆን ከዚህም መካከል 574 ሺህ 523 (31.2%) የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል፡፡
ጫናውን ለመቀልበስ የመከላከል እና የህክምና ስራዎች በስፋት እስከ ቤት ለቤት መሄድ የተከናወኑ ሲሆን በተለይም የማህበረሰቡን ተሳትፎ የማሳደግ ስራዎች በንቅናቄ መልክ በሁሉም ደረጃ ተከናውነዋል፡፡ በዚህም የሞት መጠኑን ወደ ዜሮ ማድረስ ተችሏል፡፡
ንጋት፡- እንደ ሀገር የተጀመረውን የጽዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭን ተግባራዊ ከማድረግ ረገድ የተሰሩ ስራዎች ካሉ?
አቶ ሳሙኤል፡- በክልሉ ሞዴል ወረዳዎችንና ቀበሌያትን ለመፍጠር የጽዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭን በወረዳዎች መተግበር የተጀመረ ሲሆን በበጀት አመቱ በሙከራ ደረጃ በተመረጡ 5 ወረዳዎች (ሶዶ፣ ምዕራብ አዘርነት፣ ደምቦያ፣ ምስራቅ ባዳዋቾ፣ ጌታ) ላይ መተግበር የተቻለ ሲሆን ሌሎችም 3 ወረዳዎች (እዣ፣ ሚሻ፣ አቶቴ ኡሉ) በዝግጅት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
በዚህም በክልሉ 695 ቀበሌዎችን ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነጻ በማድረግ ሽፋኑን ከ53 ከመቶ ወደ 55 ከመቶ ለማድረስ ታቅዶ 684 (54.2 ከመቶ) የደረሰ ሲሆን ከታቀደው አንጻር 98 ነጥብ 5 ከመቶ መፈጸም ተችሏል፡፡
ንጋት፡- በጤና ተቋማት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመተግበር ረገድ ምን ስራዎች ተሰርተዋል?
አቶ ሳሙኤል፡- የጤና ተቋማት ከወረቀት ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተጀምሯል፡፡ ከወረቀት ነፃ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎችን ቁጥር ከ2 ወደ 5 ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በዚህም የቡታጅራ፣ የንግስት ኢሌኒ መሀመድ መታሰቢያ፣ የወራቤ፣ የበሸኖ እና ዶክተር ቦጋለች ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነፃ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ የጤና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የሀላባ ቁሊቶ ሆስፒታል በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
በበጀት ዓመቱ አንድ የኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት በሆሳዕና ከተማ በንግስት ኢሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ተቋቁሞ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ አንድ አዲስ ክልላዊ የህብረተሰብ ጤና ላበራቶሪ በወራቤ ከተማ በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በማቋቋም ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል 10 አዲስ ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት በማቋቋም ስራ ለማስጀመር ታቅዶ 11 ማስጀመር የተቻለ ሲሆን በዚህም በክልሉ ስራ የጀመሩ ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ቁጥር 7 ከነበረበት ወደ 18 በማሳደግ ጉልህ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዘጠኝ ከተሞች ውስጥ (ሆሣዕና፣ ወልቂጤ፣ ዱራሜ፣ ቡታጅራ፣ ኬላ፣ ዓለምገበያ፣ ቀቤና፣ ዳርጌ፣ ሀላባ ቁሊቶ) ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች በኮሪደር ልማት ፕሮጄክት ውስጥ ተካተው እየተሰሩ ሲሆን በሁለት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ይገኛል፡፡
ንጋት፡- ድንገተኛ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ሳሙኤል፡- በበጀት ዓመቱ የተከሰቱትን የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ ቆይቷል፡፡ ከተከሰቱ ወረርሽኞች መካከል ወባ፣ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ኤምፖክስ እና የምግብ አለመመጣጠን ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ከተፈጥሮ አደጋዎች መካከል የጎርፍ አደጋ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንደ ክልል 3 የኮሌራ ታማሚዎች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን በባለፈው በጀት ዓመት 876 ታማሚዎች እና 21 ሞት ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ የታማሚ ቁጥር የተመዘገበበት እና ምንም ሞት ያልተመዘገበበት ዓመት ነበር፡፡ ሌላዉ 609 የኩፍኝ ታማሚዎች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ምንም የሞት ክስተት ያልነበረበት ዓመት ነበር፡፡
ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 1 ሺህ 952 የኩፍኝ ኬዝ እና 20 ሞት አንፃር ከፍተኛ ለውጥ የመጣበት ነው፡፡ በጥቅሉ በበጀት አመቱ ከስታንዳርዱ በላይ ሞት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር የዋለ ወረርሽኝ ሽፋን 100 ከመቶ በላይ ለማቆየት በታቀደው መሰረት 100 ከመቶ ማከናወን ተችሏል፡፡
ንጋት፦ የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታትና ህገ ወጥ የመድሃኒት ቁጥጥር ከማድረግ አንጻር ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል?
አቶ ሳሙኤል፡- በበጀት ዓመቱ በ2 ሺህ 699 የመንግስትና የግል የጤና አገልግለት ሰጪ እና 534 መድሃኒት ቸርቻሪ ተቋማት ላይ ቁጥጥር ለማካሄድ ታቅዶ በ2 ሺህ 424 (89.8%) ላይ ለማከናወን ተችሏል፡፡ በቁጥጥር ወቅት በተገኘ ግኝት መሰረት ጥፋት በፈጸሙ 263 ተቋማት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዷል፡፡
በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት በህገ ወጥ ምግብና መድሃኒት ላይ በተለያዩ ጤናና ጤና ነክ ተቋማት ላይ በተደረገ ቁጥጥር ብር 20 ሚሊዮን 181 ሺህ 901 ነጥብ 15 የሚገመት ህገ ወጥና ጊዜ ያለፈበት የምግብና የመድሃኒት ምርት ከህብረተሰቡና ከጸጥታ አስከባሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ውለው ሊወገዱ ችለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የማህበረሰብ ጤና መድህን የአባልነት ሽፋን ከ78 ከመቶ ወደ 90 ከመቶ ለማድረስ ታቅዶ 80 ከመቶ ማድረስ የታቸለ ሲሆን የእድሳት ምጣኔ ከ86 ከመቶ ወደ 95 ከመቶ ለማድረስ ታቅዶ 86 ከመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ ሀብትን ከማሰብሰብ አንጻር በ2017 በበጀት ዓመት በጠቅላላ ከ651 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሀብት ማሰብሰብ የተቻለ ሲሆን የተሰበሰበውን 623 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ብር ወደ ባንክ በማስገበት አፈጻጸሙ 95 ነጥብ 78 ከመቶ ነው፡፡ ይህም አፈጻጸም በ2016 ከነበረው ከአባላት ቁጥርም በሀብት አሰባሰብም መሻሻል ያሳየ ነው፡፡
ንጋት፡- የሎጅስቲክና የፕሮጅክቶች አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሳሙኤል፡- በበጀት ዓመቱ ቢሮው ያለበትን የተሸከርካሪ፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ እና ኤሌክትሮኒክስ ችግሮችን ድጋፍ እንዲደረግ ፕሮፖዛል በመቅረፅና በተደጋጋሚ በአካል በመንቀሳቀስ ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋሮች የተገኙ አምስት አዳዲስ ሀርድቶፕ ተሸከርካሪዎች፣ ሁለት ያገለገሉ ተሸከርካሪዎች፣ 16 አምቡላንሶች፣ 76 ሞተር ሳይክሎች፣ 262 ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች፣ 297 ታብሌቶች በክልሉ ዉስጥ ላሉ ጤና ተቋማት እና ከክልል እስከ ወረዳ ላሉ መዋቅሮች ተሰራጭቷል፡፡
ለነባርና ለአዳስ ፕሮጀክቶችና ለጤና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ የሚሆን በአጠቃላይ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ከክልል መንግስት በኩል የተመደበ ሲሆን የሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ ግንባታ በዞን/በልዩ ወረዳ ደረጃ በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ በጀት ይዘው ግንባታውን ለጀመሩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በድጋፍ መልክ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡
በ2017 ዓ/ም ነባር ፕሮጀክቶች 34 ሲሆኑ 5 የፋርማሲ ብሎክ፣ 3 የቀዶ ጥገና ብሎክ፣ 6 የባለሙያ ማደሪያ ግንባታ፣ 11 የጤና አጠባበቅ ማስፋፊያ፣ ሁለት 2ኛ ትውልድ ጤና ኬላ፣ 4 የመጀመሪያ ጀረጃ ሆስፒታሎች እና 3 አጠቃላይ ሆስፒታሎች ይገኛሉ፡፡ ከሶስቱ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ወልቂጤ አጠቃላይ ሆስፒታል አዲስ ሙሉ ግንባታ ሲሆን ዶ/ር ቦጋለች መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ የሚካሄድባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጄክቶች ላለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ስራ ያቆሙና ባለቤት አልባ የነበሩ ሲሆን በበጀት አመቱ ወደ ትግበራ አስገብተናል፡፡ በእርግጠኝነት በቀጣይ እስከ 2018 ግማሽ አመት ድረስ ሁሉም ፕሮጅክቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን፡፡
በበጀት ዓመቱ ለጤና ኬላዎች ግንባታ በመንግስት ከተመድበው 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በተጨማሪ ከህብረተሰቡ ለግንባታ የሚሆን ሀብት ከ153 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰበሰብ የተቻለ ሲሆን 7 አዲስ አጠቃላይ/ኮምፕርሄንሲቭ ጤና ኬላዎችን ግንባታ ለማስጀመር ታቅዶ በህብረተሰቡ ንቅናቄ 17 የተጀመረ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ከታቀደው ከ200 በመቶ በላይ ማከናወን ተችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ የ25 አዲስ መሰረታዊ ጤና ኬላዎችን ግንባታ በዞኖች እና በወረዳዎች ለማስጀመር ታቅዶ በህብረተሰቡ ንቅናቄ የሃያ አምስቱን ግንባታና እድሳት ማስጀመር ተችሏል፡፡
ከመንግስት በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ በህብረተሰብ፣ በአጋር ድርጅቶችና በባለሀብቶች በተገኘ ከ344 ሚሊዮን 122 ሺህ 992 ብር በላይ ድጋፍ ከ97 በላይ የተለያዩ የጤና ፕሮጀክቶች ግንባታ በበጀት በማስደገፍ የተጀመሩ ሲሆን የአብዛኛዎቹ ግንባታ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በርካታ ስራዎች በየደረጃው በመስራት በርካታ አዎንታዊ ለውጦች ማምጣት የተቻለ ሲሆን ለረጅም ዓመታት የዘለቁ ችግሮች በአብዛኛው መፍታት የተቻለበት፣ ዝቅተኛ አፈጻጸም ይዘው ለረጅም ጊዜ የቆዩ አፈጻጸሞችን ማሻሻል የተቻለበት እና የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው በህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች የሚቀርቡባቸውን አብዛኛዎቹን ችግሮች መፍታት የተቻለበት አመት ነበር፡፡
ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሳሙኤል፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
በርካታ የቀለም ልጆችን ያፈሩ መምህርት
“አካል ጉዳተኛ ተቀባይ ብቻ አይደለም ሰጪም ነው” – አቶ ልብአገኘሁ ገ/ማሪያም
“ወርቃማ የሚባለውን ዘመን በመምህርነት በማሳለፌ ደስተኛ ነኝ” – መምህር መንግስቴ አየለ