በኢያሱ ታዴዎስ
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 19/1996 ዕለተ አርብ ምሽት፣ በስፖርቱ መድረክ አንድ ድንቅ ትዕይንት እየተካሄደ ነው። ስፍራው በአሜሪካዋ አትላንታ ከተማ የሚገኘው ግዙፉ ሴንቴኒያል ስቴዲየም። አሜሪካ በትልቁ የኦለምፒክ መድረክ መላውን ዓለም ለማስደመም በወቅቱ ውድ የተባለውን 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ አድርጋለች።
ለዚሁ ዝግጅት አምሮና ተውቦ የተሰናዳው ሴንቴኒያል ስቴዲየም ታዳሚው እጁን በአፉ ጭኖ በተገረመበት በምሽቱ የመክፈቻ ስነስርዓት በአስገራሚ ድባብ ተሞልቶ ነበር። ይህንን ድንቅ ዝግጅት በአካል ተገኝተው ለመከታተል የታደሉት 85 ሺህ 600 ታዳሚያን ነበሩ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴሌቪዥን መስኮቶች ደግሞ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ተመልካቾች በቀጥታ ተመልክተውታል። በሴንቴኒያል ስቴዲየም በደማቅ ትዕይንት ታጅቦ በተካሄደው በመክፈቻ ዝግጅት፣ የኦሎምፒክ ችቦውን ያቀጣጠለው የቡጢው ስፖርት የምን ጊዜም ጀግና መሐመድ አሊ ነበር።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ደግሞ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ነበሩ። በኦሎምፒክ ወግ መሰረትም ቀልብን የሚስቡ ማራኪ ትዕይንቶች ከቀረቡ በኋላ፣ ተሳታፊ ስፖርተኞች እንደ አሜሪካ ባህል በአልባሳት አሸብርቀው የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ስቴዲየሙን ዞረዋል።
በዚህ መልኩ ጅማሮውን ባደረገው የ1996 የአትላንታው ኦለምፒክ፣ ከ197 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 339 ስፖርተኞች በ37 የውድድር ዓይነቶች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 4 ድረስ ውድድራቸውን አካሂደዋል።
ታዲያ ተሳታፊ ከነበሩት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች። ይሄ የኦሎምፒክ መድረክም ለሀገሪቱ ልዩ ትርጉም ነበረው። ከዚሁ ከአትላንታው ውድድር አስቀድሞ ተካሂዶ በነበረው የ1992 የባርሴሎናው ኦለምፒክ፣ ኢትዮጵያ ለ12 ዓመታት ከመድረኩ ርቃ ዳግመኛ በመመለሷ ክብሯን ለማስጠበቅ በአትሌቶቿ ብርቱ ትግል አድርጋ ነበር።
በወቅቱም በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የተሳተፈችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ ቀዳሚ ሆና በመጨረስ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሴት አትሌት ከመሆኗም በላይ ለሀገሯ ወርቅ ማስገኘት ቻለች። አትሌት አዲስ አበበ በ10 ሺህ ሜትር፣ እንዲሁም ፊጣ በይሳ በ5 ሺህ ሜትር ባስገኙት 2 የነሃስ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያ በጥቅሉ 3 ሜዳሊያዎችን አግኝታ ነበር የባርሴሎናውን ኦለምፒክ ያጠናቀቀችው።
የ1996 የአትላንታም ኦሎምፒክ ከውጤታማነት አኳያ ስሟ በጉልህ ባይጠቀስም ክብሯን ማስጠበቂያ መድረክ ተደርጎ ተወስዶ ነበር። ለዚህም በአትሌቲክስ 16 አትሌቶችን፣ በቦክስ ስፖርት ደግሞ 2 ቦክሰኞችን፣ በአጠቃላይ 18 ስፖርተኞችን አሳትፋለች።
ኢትዮጵያ ልታሸንፍ እንደምትችል የተገመተው በሴቶች 10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ነበር። የባርሴሎናዋ አሸናፊ ደራርቱ ቱሉ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷት ነበር። ከደራርቱ ጋር ጌጤ ዋሚ እና ብርሃኔ አደሬ በርቀቱ ተዓምር ሊፈጥሩ ይችላሉ የተባሉ ተጠባቂ አትሌቶች ነበሩ።
ውድድሩ ግን እንደታሰበው ቀላል አልነበረም። ኢትዮጵያ በጠንካራ አትሌቶቿ ታግዛ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ብታደርግም ሜዳሊያ ውስጥ መግባት የቻለችው ጌጤ ዋሚ ባሳካችው የነሃስ ሜዳሊያ ነበር። በውድድሩ የተጠበቀችው ደራርቱ ቱሉ 4ኛ ደረጃን ስትይዝ፣ ብርሃኔ አደሬ በበኩሏ 18ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ብዙም ተስፋ ባልጣለችባቸው ሁለት ውድድሮች አንጸባራቂ ድሎች ማስመዝገብ ቻለች። በወንዶች 10 ሺህ ሜትር እና በሴቶች የማራቶን ውድድሮች።
በወንዶች 10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያን የወከሉት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ አብርሃም አሰፋ እና ወርቁ ቢቂላ ነበሩ። በውድድሩ ከኬኒያዊው ፖል ቴርጋት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ሲሮጥ የነበረው ወጣቱ ሃይሌ፣ ድንገት ሳይጠበቅ አፈትልኮ በመውጣት ኬኒያዊው ላይ አስደናቂ ድል ተቀዳጀ። ሃይሌ ርቀቱን ለመጨረስ የፈጀበት 27:07.34 ነበር።
ሌላው በመድረኩ ኢትዮጵያን ያስጠራ ገድል የተፈጸመው በሴቶች ማራቶን ነበር። በማራቶን ብዙም ልምድ የሌላት አትሌት ፋጡማ ሮባ በብቸኝነት ኢትዮጵያን ወክላለች። ለውድድሩ አዲስ ብትሆንም በምቾት ነበር ስትሮጥ የነበረው።
አትሌቷ ኋላ ላይ በሰጠችው አስተያየት፣ ውድድሩ 18ኛው ኪሎ ሜትር ላይ እንዳለ፣ በአንደኝነት እንደምትጨርስ እርግጠኛ ነበረች። እርሷ ምቾት በተሰማት በዚያ ቅጽበት፣ ተፎካካሪ አትሌቶች እጅግ ተዳክመው ተመልክታ ነበርና።
እንዳሰበችውም ርቀቱን በ2:26:05 በመግባት በበላይነት አጠናቀቀች። ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን ወርቅ ስታስገኝ፣ በኦለምፒክ መድረክ በሴቶች ማራቶንን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አትሌት በመሆን በታሪክ መዝገብ ለመስፈር በቃች።
ኢትዮጵያም በፋጡማ ሮባ እና ሃይሌ ገብረስላሴ ሁለት ወርቆች፣ እንዲሁም በጌጤ ዋሚ አንድ የነሃስ ሜዳሊያዎች ታግዛ በጥቅሉ 3 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የአትላንታ ኦለምፒክን ተሰናብታለች።
በእርግጥ በዚሁ መድረክ ኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን ሜዳሊያ የማግኘት ተስፋ ሰንቃ ነበር። በወንዶች ማራቶን ልምድ ያካበቱት በላይነህ ዲንሳሞ፣ አበበ መኮንን እና ቱርቦ ቱሞ ተሳታፊዎች ነበሩ። በላይነህ ዲንሳሞ እና ቱርቦ ቱሞ ውድድሩን ሳይጨርሱ አቋርጠው ሲወጡ፣ አበበ መኮንን 81ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል።
በተመሳሳይ ፊጣ በይሳ እና አሰፋ መዝገቡ በተሳተፉበት የወንዶች 5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ሜዳሊያ ሊገኝ እንደሚችል ቢጠበቅም ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል።
በአጠቃላይ የ1996 የአትላንታ ኦለምፒክ ለኢትዮጵያ የተለየ ነገር ይዞ ባይመጣም በመድረኩ በተሳትፎ ረገድ ሄድ መጣ ስትል ስለነበር ያስመዘገበችው ውጤት የሚናቅ አልነበረም። ሃይሌ ገብረስላሴ እና ፋጡማ ሮባ የመሳሰሉትን እንቁ አትሌቶችን ያስተዋወቀችበትም ነበር።
እንደ አሁኑ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ባልተስፋፉበት በዚያ ጊዜ 3 ሜዲሊያዎችን መሰብሰብ መቻሉ በራሱ ስኬት ነበር።
ታዲያ አትሌቲክሱ እና አትሌቶቹ በጎለበቱበት በዚህ ወቅት ደግሞ በተለይም ከወራት በኋላ በሚካሄደው የፓሪሱ ኦለምፒክ አንጸባራቂ ውጤት መጠበቅ የዋህነት አይመስለኝም። አሁን ለዚሁ ዓላማ በቂ ዝግጅት መደረጉና አስፈላጊው ውጤት እንዲመዘገብ ግብዓቶች መሟላታቸው ከትናንት ታሪካችን ተምረን ራሳችንን ዝግጁ ያደረግን ይመስለኛል።
ለማንኛውም ከፈረንጆቹ ሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11/2024 በሚካሄደው የፓሪሱ ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን መልካም ውጤት ይገጥመው ዘንድ ከወዲሁ ተመኘን። ሰላም!!
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ