ውበትና ጣዕምን ያጣመረ

ውበትና ጣዕምን ያጣመረ

በገነት ደጉ

አቶ መሰለ ማትዮስ ይባላሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በጋሞ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን የልማት ዘርፍ አስተባባሪ ናቸው፡፡ በአፕል ሥራ የብዙ ዓመታት ልምድ አላቸው፡፡ ከዚህ ባሻገርም በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ስለ አፕል አተካከል ግንዛቤ በመፍጠር ከሚታወቁ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ የአፕል ተክል በአካባቢው መቼ እና እንዴት ማልማት እንደተጀመረ አጫውተውናል፦

ዕድሜ ጠገቧ የ73 ዓመቷ የአፕል ተክል በጨንቻ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን “ፔር ዩ ፖም” ተብሎ ከሚጠራው የአፕል ዝርያ ውስጥ ትመደባለች። የደጋ ፍራፍሬዎች በተለይም ፖም የሚባሉት አፕል ፔር ከሚባሉት በፖም ዝርያዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ይህችን 73 ዓመት ያስቆጠረችውን የአፕል ተክል ጨምሮ በጋሞ ቃለ ህይወት ቤተ-ክርስቲያን ከ120 በላይ የአፕል ዝሪያዎች ይገኛሉ፡፡ ያም ሆኖ አሁን ላይ ለአርሶ አደሩ ምርት በተገቢው የሚሰጡት እና በማሳቸው ላይ ያሉት 24ቱ ዝርያዎች ብቻ ናቸው፡፡

በአርሶ አደሩ ማሳ የአፕልና የፔር ዝርያዎች በብዛት ምርት እየሰጡ ሲሆን እነዚህም በፖም ዝርያ የሚካተቱ ናቸው፡፡

በአርሶ አደሩ እና በቃለ ህይወት ማሳ ላይ የፔር እና የአፕል ተክሎች በብዛት እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ መለሰ ተክሎቹ ቶሎ በመድረስ ውጤት እንዲሰጡ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡

“ጆዋሳፐር”፣ “ክርስፒኒ”፣ “ትራንሰወሚስ”፣ እና “ፉጂ አታካ” ወ.ዘ.ተ የሚባሉት የአፕል ዝርያዎች በስፋት እንደሚገኙ ጠቁመው ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ የራሳቸው የሆነ ጣዕም እንዳላቸው እና በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡

አፕል ወቅቱን ጠብቆ ከተለቀመ ጣዕሙ ጥሩ እንደሚሆን የሚናገሩት አቶ መሰለ አሁን ማሳ ላይ የሚገኙ የአፕል ፍሬዎችን መሰብሰብ በማይቻልበት ወቅት ላይ አይገኙም።

አሁን ላይ አረንጓዴ ቀለም ይዘው የሚበስሉ የአፕል ዝሪያዎች ስለመኖራቸው የተናገሩት አቶ መሰለ ከዚህ ሌላ ወርቃማ፣ ወይንጠጅ፣ ቡኒ እና ዥንጉርጉር ቀለም ያላቸው የአፕል ዝርያዎችም አሉ። እንደ ዝርያቸው ሁሉ ቀለማቸውና ጣዕማቸውም የተለያዩ ስለመሆኑ ነው የሚናገሩት።

አሁን ላይ አርባ ምንጭ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ለሽያጭ የሚቀርበውና የጨንቻ አፕል እየተባለ በየመንገዱ ላይ የሚሸጠው ወቅቱን ጠብቆ ያልተለቀመ እና ጥራት የሚጎለው ምርት ስለመሆኑ ገልፀዋል፤ የጨንቻ አፕል መጀመሪያ ፈጥኖ የሚደርሰው ከመጋቢት 25 በኋላ ስለመሆኑ በመጠቆም፡፡

ይህ ሲባል ግን ሁሉም በዚያ ወቅት ይደርሳሉ ማለት ሳይሆን አንዳንዶቹ ዝርያዎች መድረስ እንደሚጀምሩ ለመጠቆም ነው ያሉት አስተባባሪው በተለይ “ቦንድ ሬድ” የተባለው የአፕል ዝርያ ፈጥኖ የሚደርስ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሌሎቹ እንደ “ጆናዶ ሬድ” እና “ክርስፒኒ” ያሉት የአፕል ዝርያዎች ደግሞ ከሚያዚያ አጋማሽ በኋላ የሚደርሱ መሆናቸውን አጫውተውናል፡፡

ከእነዚህ ለየት የሚሉ የአፕል ዝርያዎች ከዚህ ጊዜ ገፋ አድርገው የሚደርሱ እንዳሉ የሚናገሩት አቶ መሰለ እንደ “ፉጂ አታካ” እና “ሬድ ደሊሸስ” የመሳሰሉ ዝርያዎች ግንቦት ወር አካባቢ የሚደርሱ ናቸው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በየከተማው የተሰራጨው አፕል ወቅቱን እና የመብሰያ ጊዜውን ሳይጠብቅ የተሰበሰበ ሲሆን፥ የጨንቻ አፕል በሚል ስያሜ ለሽያጭ የቀረበበትና ይህም ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነት “ግራኒ” የሚባል የአፕል ዝርያ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ የሚደርስ ሲሆን አሁን ላይ በስፋት ገበያ ላይ እየተሸጠ ይገኛል። ይህ ድርጊት ብዙዎች የአፕልን ጥቅም እንዳይረዱ ያደርጋልና እያንዳንዱ አፕል የሚደርስበትን ጊዜ እና ወቅቱን አውቀውና ጠብቀው ቢለቅሙ የማይጣፍጥ የአፕል ዝርያ ይገኛል ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአፕል ጣዕሙ የሚለካው እንደ ግለሰቡ ነው የሚሉት አቶ መሰለ፥ በደፈናው ይህ ጣፋጭ ነው፥ ይህ አይጣፍጥም የምንለው ሳይሆን ወቅቱን ጠብቀን ምርቱን ከሰበሰብን ሁሉም የአፕል ዝርያዎች የየራሳቸው ውበትና ጣዕም እንዳላቸውም ነው የጠቀሱት፡፡

አፕል ወደ ኢትዮጵያ መቼ እንደገባ በውል ባይታወቅም ወደ ጨንቻ የገባው ግን በ1943 ዓ.ም ነው። የአርሲ ክፍለ ሀገር ገዢ የነበሩ ካፒቴን ደምሴ የተባሉት ግለሰብ በኤስ.ኤይ.ኤም ሚስዮን አማካይነት የአፕል ምርት “ሚሽነሪዎች” ከኬኒያ እንዲያመጡ መጠየቃቸውን ተከትሎ የሚሽነሪዎቹ ኃላፊም ከብዙ ትግል በኋላ አፕል እና የፔር ዝርያዎች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ነው የጠቀሱት፡፡

ተክሉ ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባ ሰው እንዳልፈለገው የተናገሩት አስተባባሪው፥ በብዙ ገንዘብ የመጣውን ችግኝ በሜዳ ላይ ከምንጥል ወደ ኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች በወንጌል ስርጭት ለወጡ ሚሽነሪዎች ብናሰራጭ ይሻላል፤ በማለት በወቅቱ የሚሽኖቹ ኃላፊ ሚስተር ራስ ላስ አፕሎችን ወደ ጨንቻ ይዘው መምጣታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

በወቅቱም በጓሮ ውስጥ የተለያዩ ዝርያዎችን መትከላቸውን አስታውሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኚህ ሚሽነሪ የተከሏቸው የአፕል ተክሎች በማሳው ውስጥ የነበሩ ሲሆን “ፔር” የተባለችውና የ73 ዓመታትን ያስቆጠረችው ተክል በወቅቱ ከነበሩት ዝርያዎች መካከል አንዷ እንደሆነች ነው ያስረዱት፡፡

በ1967 ዓ.ም ሌሎች ዝርያዎች ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን የሚነገሩት አቶ መሰለ ውጤታማ እና ተፈላጊ መሆኑ ሲታወቅ ወደ መንግስት የልማት ጣቢያዎች በመወሰድ የማልማት ሥራዎች በስፋት መጀመራቸውን ነው የገለፁት፡፡

ያም ሆኖ የደርግ አብዮት መነሳቱን ተከትሎ ከሀይማኖት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ውዝግቦች በመነሳታቸው ምክንያት የልማቱ እጣ ፋንታ ተቋርጦ እንደነበር አቶ መሰለ ጠቁመዋል። በደርግ መንግስት ውድቀት ማግስት ሁሉም ወደ አምላኩ ይፀልይ፥ የቆሙ ልማቶች ይጀምሩ ሲባልና ቤተክርሲቲያኒቱ ስትከፈት ልማቱም አብሮ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡

በወቅቱም ዶክተር ቶፊሎስ ተስፋዬ የሚባሉት ግለሰብ ሁለት ፕሮጀክቶችን የቀረፁ ሲሆን አንዱ የደጋ ፍራፍሬ እና በወተት ከብቶች በተለይም ሆሊስትንና ጀርሲ የሚባሉትን ሁለት ዝርያዎች፥ ከመንግስት ወደ 10 ሄክታር ቦታ በመውሰድ የልማትና የእርባታ ሥራዎችን እንደጀመሩ ነው የሚነገረው፡፡

በተለይም የአፕል ልማቱን በተመለከተ ችግኙን የመትከል፣ የማባዛት እና የማዳቀሉን ነገር በወቅቱ የመንግስት መስሪያ ቤት ላይ ይሰሩ የነበሩ አቶ ጎታ ጎዳ የሚባሉ አባት ኋላ ላይም ስራቸውን ለቀው እስከ ዩጋንዳ ድረስ በመሄድና ስልጠና በመውሰድ በቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ማሳ ላይ በስፋት የሰሩ ስለመሆናቸው ነው ያስረዱት፡፡

የሆነ ወቅት ላይ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አንዲት ጋዜጠኛ መጥታ ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የ30 ደቂቃ ዶክመንተሪ ፊልም ሰሩ። በዚህም የአፕል አመራረትን በተመለከተ ስልጠና እና ችግኝ ጥያቄ ወደ ጋሞ ቃለ ህይወት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከኢንቨስተሮችም እና ከባለሀብቶች ጭምር መቅረብ ጀመረ፡፡

በወቅቱም “አረንጓዴው ወርቅ” በመባል የጨንቻ ከተማን ከዞንና ከክልል አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዳስተዋወቀ ያስታወሱት አቶ መለሰ አፕል ለጨንቻ ልዩ መለያዋ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡

በተለይም ዶክተር ቶፊሎስ ተስፋዬ አጭር ስልጠና ሰዎች የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረው ለ13 ተከታታይ ዓመታት ስልጠናው በጨንቻ ሲሰጥ እንደነበረ አቶ መለሰ አስታውሰዋል። በዚህም አርሶ አደሮች ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ፣ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች በመምጣት በአግባቡ ስልጠናውን እያገኙ ጨንቻን በመላው ኢትዮጵያ በማስተዋወቅ እና አፕል ተወዳጅ ሆኖ እንዲታይ ዕድል የፈጠረ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

ያም ሆኖ የተፈለገውን ያህል ሳይመረትና ብዙም ሳይታወቅ ቆይቶ እንደነበር አንስተው አፕል በስፋት መመረት የጀመረው ወርልድ ቪዥን የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሰፊ ማሳ ወስዶ ችግኙን በማባዛት ለአርሶ አደሩ በነፃ ማከፋፈል ከጀመረ በኋላ ነው፡፡

በወቅቱ በጨንቻ ወረዳ ላይ ባሉት ከ50 በላይ ቀበሌያት በነፃ ሲከፋፈል እንደነበር አስታውሰው አርሶ አደሮች የተለያዩ ስልጠናዎችን ወደ ከተማው መጥተው በመውሰድም ይሁን ባለሙያዎችን ወደ ማሳቸው ጠርተው በማስተከል ሰፋ ያሉ ሥራዎች መስራታቸውን ገልፀዋል። በተለይም ወሎ ላይ፥ ደሴ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች “ወሎን ዳግማዊ ጨንቻ እናረጋለን” ብለው እስኪነሱ ድረስ አፕልን በስፋት ማምረት እንደተቻለ ነው የተናገሩት፡፡

በተለይም ከ1994 ዓ.ም በኋላ የደጋ ፍራፍሬዎች ማህበራት በስፋት መደራጀታቸውን ተናግረው በርካታ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በችግኙም ይሁን በፍሬው ሽያጭ ሀብትና ንብረት አፍርተዋል፡፡

“ብዙውን ጊዜ ቆለኛ የገንዘብ እጥረት አያጋጥመውም” ያሉት አቶ መለሰ ቆለኛ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ አቮጋዶ የመሳሰሉት ፍራፍሬዎችን በስፋት የሚያለማ ሲሆን የተዘራም ሆነ የተተከለ ነገር ቶሎ እንደሚደርስላቸው ነው የጠቀሱት፡፡

ደገኛው ግን ብዙም የገቢ ምንጭ የሌለው ነው ያሉት አቶ መሰለ ገቢ የሚያገኘው ከድንች፣ እንሰት፣ አተር፣ ባቄላ እና ገብስ ሲሆን ይህም በዓመት አንድ ጊዜ የሚደርስና የአካባቢው ህብረተሰብ ለኑሮው በቂ የሆነ ገቢ የማያገኝበት እንደነበር ነው የተናገሩት።

ከዚህ በተቃራኒ የአፕል ችግኝ ከጨንቻ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ይጫን እንደነበር አስታውሰው በወቅቱም የብዙዎችን ህይወት እና የኑሮ ደረጃቸውን እንደቀየረ ነው የገለፁት፡፡

ከዚህ በፊት ደህና ጎጆ ቤት እንኳ የሌለበት አካባቢ ከተማ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ግን እሳቸውም የተሻለ እና ደረጃውን የጠበቀ የቆርቆሮ ክዳን ቤት መስራታቸውንና፣ ልጆቻቸውን በተሻለ ትምህርት ቤት በማስተማር ለወግ ማዕረግ ማብቃት ችለዋል።

በከተማው ካለው የአፕል ልማት ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቶችና የንግድ አውታሮች መከፈት መቻላቸውን ጠቅሰው ከቀን ሰራተኝነት ተነስተው መኪና እስከመግዛት ደርሰዋል፡

ለጊዜያዊ ገንዘብ ብለው ሥራ የጀመሩ ማህበራት መጥፋታቸውን ተናግረው ጠንክረውና ዓላማዬ ብለው የሰሩ የወጣቶች ማህበራት እና ህብረት ሥራ ማህበራት ግን አሁን ላይ አፕል የጨንቻ መታወቂያ እንዲሆን እየተጉ ነው፡፡

ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መሰለ አንድ ልጃቸው ለትምህርት ያልደረሰ ቢሆንም ሶስት ልጆቻቸውን ግን በጥሩ ትምህርት ቤት እያስተማሯቸው ይገኛሉ። ሁሉም ልጆች የደረጃ ተማሪዎች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል፡፡

“አፕልን ካላየሁ እና ካልሰራሁ ብሎም በአፕል ተክሎች መሀል ካልተመላለስኩ እንቅልፍም አይወስደኝም” ያሉት አቶ መሰለ በተለይም ጨንቻ አካባቢ መኖራቸው ለእርሳቸው እና ለቤተሰባቸው በረከት እንደሆነ እንደሚያስቡ ነው የሚናገሩት፡፡

“ስለ አፕል ማውራት የማልሰለች ሰው ነኝ” ሚሉት አቶ መሰለ ብዙዎች ተደራጅተው የሚሰሩ ማህበራት፣ ከመንግስት፣ ከድርጅትም፣ ፕሮጀክት እና ጥናታዊ ጽሑፍ የሚሰሩ ግለሰቦች ፈልገው እንደሚያማክሯቸው ነው የገለፁት፡፡

“አፕል ለእኔ ተብሎ የተሰጠ መክሊቴ ነው” ያሉት አቶ መሰለ ከጓሮአቸው ባሻገር አቻአምና በቤተ-መንግስት ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ድረስ በመሄድ የአፕል ችግኝ አስተክለውና ለእንክብካቤው በቂ ስልጠና ሰጥተው መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ግማሽ ሄክታር የሚሆን የአፕል ማሳ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ መሰለ ከዚህ ስራቸው ጎን ለጎንም የወተት ከብቶች አላቸው። አርባ ምንጭ ላይ የወተት ቤት በመክፈት ለአካባቢው ህብረተሰብ ትኩስ ወተት እያከፋፈሉ እና እርጎም እየሸጡ ስለመሆናቸው ነው የገለፁት፡፡

በአፕል ዙሪያ ያላቸውን እውቀት በአጭር እና በረጅም ጊዜ ስልጠና እንዳገኙ የተናገሩት አቶ መሰለ አሁን ላይ በሁሉም ክልሎች በመንቀሳቀስ ለአርሶ አደሮች ስልጠና እንደሚሰጡ ነው የገለፁት፡፡

ቀድሞም ከአፕሉ ጋር አብረው ያደጉ ቢሆንም ስልጠናና ንባብ ሲታከልበት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እንዳስቻላቸው ነው የጠቀሱት፡፡

በተለይም ደግሞ ከዩኒቪርሲቲ ለሚመጡ ተማሪዎች በተግባር በአፕል ዙሪያ ሙሉ ስልጠና በመስጠት፣ከአፕል ማር ማላታ እንደሚሰራ በማስገንዘብ ተያያዥ ስልጠና እንደሚሰጡአቸው ተናግረዋል። ሥራውን ለረጅም ጊዜ መስራታቸው በራሱ ከወረቀት ሥራው የተሻለ እውቀት እንዳስገኘላቸው ነው የተናገሩት፡፡