በኢያሱ ታዴዎስ
የዓለማችን ግዙፉ የስፖርት ውድድር ነው ኦለምፒክ፡፡ በዓለም አቀፉ ኦለምፒክ ኮሚቴ እውቅና የተሰጣቸው 206 ሀገራት ተሳታፊ ስለሚሆኑበት፣ በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ይኸው ውድድር እጅግ ተናፋቂ ነው፡፡
ይህንን ደማቅ ውድድር የማዘጋጀቱ ተራ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ፈረንሳይዋ ፓሪስ አነጣጥሯል፡፡ ፓሪስ ከፈረንጆቹ ሐምሌ 6 እስከ ነሐሴ 11/ 2024 ድረስ የሚካሄደውን የኦለምፒክ መሰናዶዋን ከወዲሁ እንዳጠናቀቀች እየተነገረላት ነው፡፡
የአውሮፓዋ ልዕልት ተደርጋ የምትወሰደው ፓሪስ፣ ኦለምፒክ ኮሚቴው በ2017 በፔሩ ሊማ ባዘጋጀው ስብሰባ ወቅት ነበር ተራው እንደደረሳት ያረጋገጠላት። ከ1900 እና 1924 ወዲህ 100 ዓመታትን ጠብቃ ነው ዕድሉን ያገኘችው፡፡ የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ግን እንደ መልካም አጋጣሚ ታይቶላታል፡፡ በተመሳሳይ ውድድሩን ለሶስት ጊዜያት ካዘጋጀችው ለንደን ጋርም ተስተካክላለች፡፡
እንደ ሀገር ደግሞ የኦለምፒክ ውድድሮችን በማሰናዳቱ ረገድ ፈረንሳይ ይህ ስድስተኛ ጊዜዋ ነው፡፡ 3 የበጋ እና 3 የክረምት ኦለምፒክ ውድድሮችን አሰናድታ በመድረኩ ትልቅ ስም መገንባት ችላለች፡፡
ታዲያ ለዘንድሮው ውድድር ፓሪስ፣ እምነት የጣሉባትን ላለማሳፈር ወገቧን ጠበቅ አድርጋ ነው የተነሳችው፡፡ በአጠቃላይ በ32 ስፖርቶች 329 የውድድር ዓይነቶችን ይዛ የምትቀርበው ከተማዋ፣ 10 ሺህ 500 ተሳታፊ ስፖርተኞችን ትቀበላለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ክብደት የተሰጠው ውድድሩ የሚካሄደው በፓሪስ እና በቀጠናዋ ስር በሚገኙ አካባቢዎች ነው፡፡ አንዳንድ ውድድሮች ደግሞ በሌሎች በፈረንሳይ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞች የሚካሄዱ ይሆናል፡፡ ከፓሪስ በ225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሊል ከተማ፣ የእጅ ኳስ ውድድር ይካሄዳል፡፡
በሌላ መልኩ የጀልባ ቀዘፋ እና የተወሰኑ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ከመዲናይቱ በ777 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማርሴይ ከተማ ይካሄዳሉ፡፡ ሌሎች የእግር ኳስ ጨዋታዎች የሚካሄድባቸው ከተሞች ቦርዶ፣ ሊዮን፣ ናንቴስ፣ ኒስ እና ሴይንት ኢቴን ናቸው፡፡
ከሁሉም በላይ የመዝጊያው ትርዒት፣ እንዲሁም ብዙ ውድድሮች የሚካሄዱበት ግዙፉና ማራኪው ስቴዲየም “ስታድ ደ ፍራንስ” (የፈረንሳይ ብሄራዊ ስቴዲየም) ነው፡፡ 80 ሺህ ታዳሚዎችን የመያዝ አቅም ያለውና ከኢፍል ማማ በመቀጠል የፓሪስ ምልክት እንደሆነ የሚነገርለት ስቴዲየሙ፣ ታሪክ የማይረሳውን የኦለምፒክ ድግስ እንደሚያሰናዳ ታምኖበታል፡፡
በውድድር ዓይነቶች ደረጃ የአትሌቲክስ፣ ረግቢ ውድድሮች፣ እንዲሁም የመዝጊያ ፕሮግራም ይዘጋጅበታል ስታድ ደ ፍራንስ፡፡
15 ሺህ ታዳሚዎችን የመያዝ አቅም ያለውና በፓሪስ አቅራቢያ የሚገኘው ስታድ ኦለምፒክ ኢቭጁ ማኑዋህ ደግሞ የሜዳ ሆኪ ውድድር ይካሄድበታል፡፡ ከኢቭጁ ማኑዋህ ጋር የተስተካከለ ይዘት ያለው ፓሪስ ላ ዲፌንስ አሬና፣ ፓሪስ አኳቲክ ሴንተር ከተሰኘው ስቴዲየም ጋር የውሃ ዋና የመሳሰሉ ውድድሮች ይካሄዱበታል፡፡
ጂምናስቲክ እና ባድሚንተን በዴላ ቻፔይ አሬና፣ እንዲሁም ቦክስ፣ ፈረስ ግልቢያ እና የተኩስ ኢላማ በአሬና ፓሪስ ኖርድ ስቴዲየሞች ሲዘጋጁ፣ ከፍታዎችን መውጣት በለቦርዥ መንደር ይዘጋጃል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግዙፉን ፓርክ ደ ፕሪንስን ጨምሮ በ12 ስቴዲየሞች ውድድሩ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ከስቴዲየሞቹ በተጓዳኝ ፓሪስ ለአሸናፊ ስፖርተኞች የሚሸለሙ ሜዳሊያዎችን አዘጋጅታለች፡፡ በአጠቃላይ 5 ሺህ 084 በኢፍል ማማ ምልክት የተዘጋጁ ባለስድስት ጎን ቅርጽ ሜዳሊያዎች አሸናፊ ስፖርተኞች ላይ ለማጥለቅ ተዘጋጅተዋል፡፡
ሜዳሊያዎቹ የፈረንሳይን ሳንቲም በሚያትመው ሞናይ ደ ፓሪስ ተቋም የተመረቱ ሲሆን ንድፋቸው ደግሞ ፓሪስ ውስጥ በሚገኘው ሾሜ የተሰኘው ጌጣጌጥ ድርጅት ነው የተነደፈው።
እያንዳንዱ ሜዳሊያ ከ455 እስከ 529 ግራም ክብደት ሲኖረው፣ 85 ሚሊ ሜትር ስፋት፣ እንዲሁም 0 ነጥብ 36 ኢንች ውፍረት አለው። የወርቅ ሜዳሊያዎቹ 98 ነጥብ 8 ከመቶ ከብር የተሰሩ ሲሆን 1 ነጥብ 13 በመቶ ነው የወርቅ መጠናቸው። የነሃስ ሜዳሊያዎቹ ደግሞ ከመዳብ፣ ከዚንክ እና ከቆርቆሮ የተሰሩ ናቸው።
ኦለምፒኩን በተመለከተ ፓሪስ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየተንቀሳቀሰችባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል የሀገሪቱ ደህንነት ነው። ለዚህም የፈረንሳይ መንግስት የአውሮፓ ትልቁ የህግ አካል ከሆነው ዩውሮፖል (EUROPOL) እና ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል። ከኳታር መንግስት ጋርም በጋራ ለመስራት በርካታ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
የሀገሪቱን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመከላከል ሌላኛዋ አውሮፓዊት ሀገር ፖላንድ ወታደሮቿን ለመላክ ቃል ገብታለች።
ከዚህ ውጪ አጠቃላይ በውድድሩ አጋዥ የሆኑ ወደ 45 ሺህ የሚጠጉ በጎ ፈቃደኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገምቷል። በኦለምፒኩ መክፈቻ ዕለት ተሳታፊ ስፖርተኞች ባህላዊ ትዕይንቶችን እያስመለከቱ የ6 ኪሎ ሜትር ጉዞ በፓሪስ በሚገኝ ወንዝ ላይ እንደሚያደርጉ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
ዋናው የመክፈቻ ፕሮግራም የሚሰናዳውም ኢፍል ማማ ፊት ለፊት በሚገኘውና በእጅግ ማራኪ ከባቢ በተሞላው ስቴዲየም መሳዩ “ትሮሳዴሮ” ነው። የኦለምፒኩ አዘጋጆች በመድረኩ ምርጡን የመክፈቻ ዝግጅት ለተመልካች ጀባ ለማለት እንደተዘጋጁ ይፋ አድርገዋል።
ዝግጅቱን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በነጻ እንዲታደሙ የተወሰነ ሲሆን 600 ሺህ ተመልካቾችን ማስተናገድ እንደሚቻል ተገልጿል። የመዝጊያውም ዝግጅት በተመሳሳይ በባህላዊ ትዕይንት ታጅቦ በግዙፉ ስታድ ደ ፍራንስ ስቴዲየም ይዘጋጃል።
ተሳታፊ ሀገራት ቢያንስ 1 ስፖርተኛ ለውድድሩ ያዘጋጃሉ። በዚህ ረገድ አሜሪካ 488፣ አዘጋጇ ፈረንሳይ 465፣ እንዲሁም አውስትራሊያ 359 ስፖርተኞችን በማሳተፍ ቀዳሚዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በተሳታፊ ስፖርተኞች ቁጥር 46ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስን ስፖርተኞችን ብቻ ይዛ በመድረኩ እንደምትቀርብ ነው። በተዘዋዋሪ አሁንም እንደ ሌሎቹ ጊዜያቶች ኦለምፒኩን የሚመጥን የተሳታፊዎችን ብዛት ይዛ አልቀረበችም። ለዚህ ነው በአትሌቲክሱ ብቻ ጮቤ እንድንረግጥ የተገደድነው።
ለማንኛውም በፓሪሱ ኦለምፒክ የመድረኩ ልማደኛ የሆነችው ሩሲያ እና ጎረቤቷ ቤላሩስ እንዲሳተፉ አልተፈቀደላቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከፍታለች፣ ቤላሩስ ደግሞ ሩሲያን ደግፋለች በሚል ክስ ነው።
በአንጻሩ ዓለም አቀፉ ኦለምፒክ ኮሚቴ ሩሲያዊያን እና ቤላሩሳዊያን ስፖርተኞች ጦርነቱን እንደማይደግፉ በግልጽ ከተናገሩና ሀገራቸውን ወክለው ሳይሆን በግል የሚሳተፉ ከሆኑ ብቻ እንደሚፈቀድላቸው ማስታወቁ አይዘነጋም።
በኦለምፒክ ታሪክ ምርጡን ዝግጅት እውን አድርጌያለሁ ያለችው ፈረንሳይ 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዩውሮ ወጪ ተደርጎበታል ብላለች። ምንም እንኳን መንግስት ቢሸፋፍነውም የኦለምፒክ ስራዎችን ሁሉ አካትቶ አጠቃላይ ወጪው ወደ 8 ነጥብ 8 ቢሊየን ዩውሮ እንደ ደረሰ እየተነገረ ይገኛል።
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ