በትር (ቦኩ) ጥንተ ታሪክ
…ካለፈው የቀጠለ
በጌቱ ሻንቆ
ለዚህ ዘገባችን ዋቢ ያደረግነው “Faster capital “፣ ድረ -ገፅ ላይ ተከታዮቹን ዝርዝሮች እናገኛለን :-
1. Power and authority
በትሩን የመጨበጡ ወይም የመያዙ ተምሳሌታዊ መገለጫዎች መካከል የመጀመሪያው የሀይለ ልዕልና እና የስልጣን የበላይነት ናቸው። ባህላዊ ንጉሡ በሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ በተፃፈም ይሁን ባልተፃፈ ህግ መነሻ ፍርድ የመስጠት ወይም ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ በትሩ ወይም ቦኩው ያመላክታል። ፍርድ የመስጠት ብቻ ሳይሆን ፍርዱን ተከትሎ የማስገደድም ስልጣን የተሰጠው ስለመሆኑ ምልክት ነው። ይህ ተምሳሌታዊ ምልክት ፣ ቦኩ ምንጩ ብሄረሰቡ ወይም ነገዱ አምላኬ ብሎ የሚጠራው አካል ወይም ሀይል ነው።
በዚህም ሀይለ ልዕልና እና ስልጣኑን ፈጣሪውን በመፍራት ይገለገልበታል። ፍርዶቹ ወይም ውሳኔዎቹ የተጣመሙ ፈሪሀ ፈጣሪን ይዞ ፣ ሰጪውን ፣ አምላኩን እያሰበ በጥንቃቄ ፣ ሚዛናዊነትን ጠብቆ ይገለገልበታል።
2. Sovereignty
ቦኩ ወይም በትር የሉዐላዊነት ወይም የነፃነት ምልክት መገለጫ ነው። መገለጫነቱ በሚያስተዳድረው አፅመ ርስት ላይ የበላይነት ያለው ስለመሆኑ ምልክት ነው። በብሄረሰቡ ባህላዊ ክብረ በዓላት ወቅት ንጉሡ በትሩን ይዞ ወይም አስይዞ የመታየቱ መነሾ ህዝብን በበላይነት የማስተዳደር ተምሳሌታዊ አስረጅነት ነው።
ብቻም አይደለም ። አገረ ግዛቱን ወክሎ ማንኛውንም ውሳኔ የማሳለፍ ልዕለ ሀይል ባለቤትነቱ ማሳያ ነው።
3. Life and death
በጥንት ዘመን ቦኩ ወይም በትር ከህይወትና ሞት ጋር የተገናኙ አመስጥሮቶችም ነበሩት። በሰሯቸው ወንጀሎች ምክንያት ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች ይቅርታ የሚያገኙት ከንጉሡ ነበር። ይቅርታ መስጫ ምልክት ወይም ተምሳሌቱ ደግሞ ይኸው በትሩ ነበር።
እነዚህን ከብዙ በጥቂቱ አነሳን እንጂ ቦኩ ወይም በትረ መንግሥት በሂደት ደግሞ የተለያዩ ሀይለ ልዕልናዎች መገለጫ እየሆነ መጥቷል። በዚህም ነገስታትም ይሁኑ የሀይማኖት መሪዎች ተምሳሌታዊ ዕቃውን የሚጠቀሙበት በሙሉ አንድ ዓይነት ቅርፅ ያለው በትር ሲይዙ አይታይም።
ወታደራዊ መሪዎች የሚይዙት በትር አገረ -ገዢዎች ከሚይዙት ይለያል። በወርቅ የተለበጡ ወይም ከውድ የብረት ዓይነቶች የተበጁ ሊሆኑ ይችላሉ። መጠኑም የተለያየ ሊሆን ይችላል። በክብረ በዓላት የሚያዘው በትር ወይም ቦኩ በአዘቦት ቀን ከሚያዘው ተለይቶ ሊገኝም ይችላል።
ወደ ቁም ነገራችን እንመለስ። ባህላዊ የብሄረሰብ ነገሥታት የሚይዙት ቦኩ ወይም በትረ መንግሥት እንደምን ያለ ነው?
እነዚህ ነገሥታት የሚይዙት በትረ መንግሥት ግን ከዕንጨት የተሰራ ነው። ከወደ አናቱ ደቦልቦል ያለ ጌጥ የተበጀለት፣ እዚህ አናቱ ላይ ላባና መሠል የተፈጥሮ ጌጦች የተሰኩበት ወይም የተንጠለጠሉበት ሊሆን ይችላል። ይህንኑ ጉዳይ “Faster capital .com” ያትታል።
የጌዴኦ ንጉሥ የሚይዙት ቦኩ ወይም በትረ መንግሥት ከዚህ የተለየ አይደለም። ከእንጨት የተበጀና ከወደ አናቱ ድቡልቡል ጌጥ የተቀረፀበት።
የጌዴኦ ባህላዊ ንጉሥ ራስ አድርጎ ብሄረሰቡ የሚተዳደርበት ያልተፃፈ ህገ – ስርዓት መጠሪያ ስም አለው ። “ባሌ” ይባላል። የባሌ ስርዓት ፍትህ አሰጣጥ ፣ ሀብት አስተዳደርና መንፈሳዊ ስነ ስርዓቶችን ያጠቃልላል። በጥልቅ ፍልስፍናዎች ላይ የተመሠረተ የህይወትና የኑሮ መንገድ ነው።
ይህንን መንገድ ከኋለኞቹ (በዕድሜ አመጣጥ) ሀይማኖታዊ እሴቶች ጋር የሚጣረሱ ነገሮች እንዳሉት፣ ከዚያም አልፎ እንደ ባዕድ አምልኮ የሚቆጥሩት አሉ። በተለይም መንፈሳዊ ስነ ስርዓቱን። ይህ አመለካከት ግን ትክክል አይደለም።
ዲላ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ፣ ዋለሜ ካምፓስ የዘንድሮው የ”ደራሮ”፣ የጌዴኦ የዘመን መለወጫ በዓል በተከበረበት ዋዜማ ብሄረሰቡን የተመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ነበር። ከቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል አንደኛው የባሌ ስርዓት ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ያፈነገጡ ነገሮች እንደሌሉት አመላክቷል። ከነዚህም አንዱ “በባሌ ስርዓት ውስጥ ያሉ ፍልስፍናዎች ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር መጣረሶች የሉትም”፣ የሚለው ጉዳይ ሊመዘዝ ይችላል።
ጥናቱን እንደ ጠቋሚ ወይም እንደ መነሻ ይዘን ቦኩ ወይም በትረ መንግሥት በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ተዛማጅ ጥቅሶችን እንውሰድ።
“Knowing jesus” የተሠኘ ድረ ገፅ በትረ መንግሥት ወይም ቦኩ ሀያ ሁለት ጊዜያት መጠቀሱን ይጠቁማል ።
ከነዚህ ጥቅሶች ውስጥም የተወሰኑትን እንጥቀስ፦
በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 15፣ ቁጥር 6 ላይ:-
በትር የእግዘብሔርን ስልጣን ያመለክታል። “እግዚአብሔር ሆይ! ዙፋንህ ዘላለማዊ ነው፤ የፍርድህም በትር የመንግሥትህ በትር ነው።”
በዕብራውያን ምዕራፍ አንድ ቁጥር 8 ላይ:-
የእግዚአብሔር ፍርድ መሻር የሌለው የፍርዶች ሁሉ ፍርድ እንደሆነ የተመላከተው በዚሁ በትር በኩል ነው።
የነፃነት ተምሳሌት መሆኑ ደግሞ ሙሴ እስራኤላውያንን ቀይ ባህርን በከፈለ ጊዜና ህዝቡን ባሻገረ ወቅት ተብሎ ሊነሳ ይችላል።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው