የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሁሉም ብሔረሰቦች ቤት እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሁሉም ብሔረሰቦች ቤት እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ

‎”ብሔራዊ ቴአትር ለብሔራዊ ጥበብ መዳረሻ” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለተመለመሉ የኪነ-ጥበብ ባለ ተሰጥኦዎች የማጠቃለያ ምልመላ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ 32 ብሔረሰቦች የተለያዩ ብዝሃ ታሪክ፣ ቋንቋ እና እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት መሆናቸውን ጠቅሰው የክልሉ ባለተሰጥኦዎች ይህንን አድል እንዲጠቀሙ ብሔራዊ ቴአትር እድል ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባራክ ታደሰ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሁሉም ቤት ለማድረግ በማለም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሃገሪቱ ክልሎች በመዘዋወር በድምጽ፣ በውዝዋዜ እና በትወና ክልላቸውን የሚወክሉ ባለተሰጥኦዎችን በመመልመል ኢትዮጵያን እንዲያስተዋውቁ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የጥበባት ምዘናና ስልጠና ዋና አስተባባሪ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ፤ ኢትዮጵያ የምትተዋወቀው በኪነጥበብ መሆኑን አውስተው ይህንን አውን ለማድረግም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል።

‎ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በድምጽ፣ በውዝዋዜ እና በትወና 24 ወካይ ባለተሰጥኦዎች እንደሚመለመሉም ጠቁመዋል።

‎ከክልሉ 12 ዞኖች የተውጣጡ የድምጽ፣ የውዝዋዜ እና የትወና ባለተሰጥኦዎችን በመድረክ የመለየቱ ሂደት እንደቀጠለ ነው።

‎በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባራክ ታደሰ፣ በብሔራዊ ቴአትር የጥበባት ምዘናና ስልጠና ዋና አስተባባሪ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ፣ ከአርባምንጭ ትምህርት ኮሌጅ የዘርፉ መምህራን እና የኮሌጁ የትወናና ጥበብ ተማሪዎች ተገኝተዋል።

‎ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን