አርሶ አደሩ በመኸር እርሻ የተዘሩ ሰብሎችን ከአረምና ተባይ ለመከላከል የሚያደርገውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ
አርሶ አደሩ በምርት ዘመኑ የመኸር እርሻ የተዘሩ ሰብሎችን ከአረምና ተባይ ለመከላከል የሚያደርገውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገልጿል።
በልዩ ወረዳው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል እንደገለፁት፤ በ2017/18 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ በጤፍ፣ በስንዴና በሌሎችም ሰብሎች በዘር ከተሸፈነው 12 ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡
ለዚህም የአረምና ተባይ ቁጥጥርና የመከላከል ስራ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት አቶ አብድልሽኩር፤ አሁን ላይ የጤፍ ማሳ አስከ 3ኛ ዙር የአረም የቁጥጥር ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የጤፍ ትል በልዩ ወረዳውም ሊከሰት ስለሚችል አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ የጤፍ ማሳውን በአግባቡ አሰሳ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የአረምና ተባይ ቁጥጥር ስራውን የቤተሰብ ጉልበትን በመጠቀም በእጅ ማከናወን ተመራጭ መሆኑን ያስታወቁት አቶ አብድልሽኩር፤ በተለይም 2 ሄክታርና ከዛ በላይ የጤፍ ማሳ ያላቸው አርሶአደሮች ኬሚካል መጠቀም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም አርሶ አደሩ አስፈላጊ የሆኑ የኬሚካል ግብዓቶችን በልዩ ወረዳው የግብርና ግብዓት ማዕከል ማግኘት እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ አብድልሽኩር፤ በልዩ ወረዳው በጤፍ ሰብል በዘር ከተሸፈነው 10 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 7 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አርሶአደሩ በምርት ዘመኑ በመኸር እርሻ የዘራቸውን ሰብሎች ከአረምና ተባይ ከመጠበቅና ከመከላከል ስራ ጎን ለጎን ለመስኖ ልማት ስራ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በመስኖ ልማት በልዩ ወረዳው 8 ሺህ 50 ሄክታር መሬት የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ለማልማት ግብ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት አቶ አብድልሽኩር፤ ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ የጀኔሬተር፣ የሞተር ፖምፕና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በጎፋ ዞን ኢሲፔ ዲቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ሥራ ዩኒየን ካፒታሉን 62 ሚሊየን ብር በማድረስ ዓመታዊ ትርፉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን አስታወቀ
የአየር ፀባይ መረጃ ስርጭት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሁሉም ብሔረሰቦች ቤት እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ