አዳኝና ታዳኝ
…ካለፈው የቀጠለ
በጌቱ ሻንቆ
ወደ ዲላ ከተማ መጓዝ የፈለገ ሁለት አማራጮች እንዳሉት በባለፈው ማስታወሻዬ ላይ ጠቁሜያችሁ ነበር።
አንድ ዕለት ታክሲ ጠፍቶ ከዋለሜ ካምፓስ ወደ ዲላ ከተማ የዕግር ጉዞ ጀመርኩ። የዋለሜ ወንዝን ተሻገርኩ። የዋለሜ ወንዝን ተሻግሮ የመምህራኖቻችን የመኖሪያ ግቢ አለ። እዚህ መኖሪያ ግቢ በራፍ ቆሞ አገኘሁት። የስነፅሁፍ መምህሬን ቴዎድሮስ ቦጋለን። የማይመጣውን ታክሲ እየጠበቀ ነበር።
የአንዳንድ የግቢያችን መምህራን ፀባይ ይገርመኝ ነበር። ፊውዳላዊ ባህሪ ነበራቸው። ተማሪዎቻቸውን እኛ ባለፍንበት መንገድ አትለፉ የሚሉ። ይህ መምህሬ ግን ይለያል። እኔን እንዳገኘ “እንኳንም መጣህ። እንኳንም ታክሲው ቀረ። እየተጫወትን በእግራችን እንጓዛለን”፣ አለኝ።
ደስ አለኝ። ምክንያቱም እኔ የፊውዳል ልጅ አይደለሁም። ጉዟችን ቀጠለ። ከፊትለፊታችን አንድ ከሠል የጫነ አህያ በርግጎ መንገዱን ለቀቀ። መንገዱን የለቀቀ ቢሆንም ግን ያስበረገገውን ነገር ዞሮ እየተመለከተ ነበር-ሽሽቱ።
እኔና መምህሬ ግራ ተጋባን። የተገደለ ዘንዶ ተጎትቶ መንገድ ላይ ተጥሎ ነው። አህያው ግን መሞቱን ያመነ አይመስልም። ዞሮ ዞሮ ግብረ ጉንዳን ፍሪዳ ወድቆላቸዋል። ያውም ጮማ ነዋ። ሻኛ የለውም እንጂ….
እኔና መምህሬ በገጠመኛችን ተደንቀናል። መደነቃችንን እያጣጣምን ጉዟችን ቀጥሎ በመሀሉ መምህሬ አንድ ጉዳይ አነሳ።
መምህሬ ወደ ዲላ ዩኒቨርስቲ ከመምጣቱ አስቀድሞ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል አስተምሯል። ወደዚህ የመጣውም እያስተማረ ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ለማግኘት በመፈለግ ስለመሆኑ አጫወተኝ። አንደበተ ርቱዕ ነው። ፈገግታ ገንዘቡ ነው። አይገላመጥም። ፊውዳል አይደለም።
መምህሬ ሁለተኛ አመት ተማሪዎች ሆነን ስነ-ፅሁፍን የተመለከተ የ3 ሰዓታት ኮርስ እየሠጠን ነበር። በዚህ ወቅት ተማሪዎቹን ከአስር መስመር ያልበለጠ ግጥም ፅፈን እንድናመጣ አዘዘን-ለቀጠዩ ክፍለ ጊዜ።
ፅፈን ያመጣነውን ሠብስቦ ወሰደ። በሚቀጥለው ጊዜ የመረጣቸውን ግጥሞች ይዞ ተመለሰ። ከተመለሱት ግጥሞች መካከል አንዱ የኔ ነበር። ግጥሜን መለሰልኝ። ቀጣዮቹ ደቂቃዎች በተማሪዎቹ የተፃፉትን ግጥሞች የማድነቅና የመተንተን ሆኑ።
“አንብበው!”፣ አለኝ ግጥሜን። እያነበብኩ እርሱ ሠሌዳ ላይ ፃፈ:-
ወዳጅ
በነበረኝ ጊዜ አለን አለን ያሉ
እንደ ሙሴ ታቦት ዙሪዬን የዞሩ
ማግኘትና ማጣት ሆነና ፈረቃ
ድንገት አገኙና ሻርክ ሲያካክሉ
ያሳድዱኝ ጀመር ትንሹ ዓሣ እያሉ።
መምህሬ በግጥሟ ተደስቷል። መንገዳችን ላይ ያነሳው ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
መምህሬ:-
“ግጥሟን እኔጋ አኑሬያታለሁ። አንዳንድ የወደድኳቸውን የተማሪዎቼን ግጥሞች እሰበስባለሁ። ፈቅደህልኛል አይደል?”
“የሚወደድ ሆኖ ተገኝቶ? ኧረ ቲቸር ለጥያቄም አይቀርብም”፣ ብዬ መለስኩለት።
“አመሠግናለሁ”፣ አለኝ። ደነገጥኩ። ምክንያቱም እኔ ተማሪው… ይቅርታ። ለካ ቴዲ ፊውዳል አይደለም። (ነፍስ ይማር)
ዲላ ደርሼ ተመልሻለሁ። ዲላ ዩኒቨርስቲ አጥር አልባ እንደነበር አንስቼላችዃለሁ። አጥር አልባ መሆኑ ሲመሽ ሲመሽ ያስፈራን ነበር። ፍም በመሠለ የባህር ዛፍ ፍልጥ መለሎ ሆኖ በታጠረ አጥር ግቢ ውስጥ ላደገ እንደኔ አይቱን ልጅ-በጣም! በዃላ ግን ዙሪያውን በሽቦ ታጠረ።
ግቢያችን ውስጥ ተቃውሞ አይጠፋም። የተቃውሞው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የካፌ ምግብ ጥራት መጓደል ነው። ተቀውሞዎቹ የሚቀሰቀሱት ደግሞ ከ “ቦዝኒያ” ብሎኮች ነው። በአንድ ወቅት ተመሳሳይ አመፅ ተቀሰቀሰ። ተቃውሞው አልረግብ አለ። የመንግሥት ሀይሎች ግቢያችን መጡ። በሀይል ከግቢው አስወጡን። ተገደን ወጣን።
ተማሪዎች ደነገጥንም ደነበርንም። ምክንያቱም ተከታዩ እርምጃ ምን እንደሚሆን አልታወቀም። የሆነው ሆኖ መውደቅ ካለም ተያይዞ ለመውደቅ ተወስኗል። እናም ፍርሀት አሰባስቦን፣ ችቦ መስለን እየተጓዝን ነው።
እንደምንም ዲላ ከተማ ደረስን። ምን አይነት ፈተና ነው! አህያ የማይችለው ዝናብ! ዲላና አካባቢው በዓመት ሁለት ጊዜ ክረምት ያለው ነው። ዶፍ ዝናብ ጣለ። እሱስ አንድ ነገር። ከፊትለፊታችን የዝናብ መከላከያ የለበሱና የታጠቁ ሀይሎች “ቁም! ቁም!” ድምፃቸው ሲያስፈራ! “ሀገ ወጥ። ህገወጥ ሰላማዊ ሠልፍ! ተቀመጥ በቂጥህ!”
“ምኑ ላይ?”
“ደግሞ ምኑ ላይ ይላል እንዴ!”
በሠደፍ አንዱን ጎሸሙት። ተቀመጥናት። ጎርፍ የሚወርድበት የዲላ ከተማ አንድዬ አስፓልት
መንገድ ላይ። ቀዘቀዘኝ የውስጥ ሱሪዬን አልፎ።
ደግሞኮ በመከራ መካከል የሳቅ ምክንያት አይጠፋም። እንደኔው ሁሉ እሱንም ለብ አርጎታል መሠለኝ። አየኝና ሳቀ። አስከተለና “ኦስትሪች”ን አሳየኝ። ኦስታ ረጅም፣ አርዝማ ውጤቷን የሠቀለች የግቢያችን ተማሪ ናት።
ጎርፍ የሚፈስበት አስፓልት ላይ እንደተቀመጠች በጎንዮሽ ቀስ ብዬ አየዃት። መቀመጫዋን የደፈረው ቅዝቃዜ ፊቷም ላይ ተረጭቷል። እኔና ጓደኛዬ አፋችንን ግጥም አርገን ያዝን-ሳቃችን ፈንድቶ ጀርባችን ላይ ሰደፍ እንዳይጫንብን።
የፀጥታ ሀይሎቹ በታተኑን። ቢበታትኑንም አቦ ቤተክርስቲያን ተሰባሰብን። በፀጥታ ሀይሎችና በዲላ ከተማ ህዝብ መካከል ፍጥጫ ነገሰ። የፀጥታ ሀይሎቹ “በመንግሥት ላይ አመፅ ያነሳ ሀይል እዚህ ገብቷል። እናወጣለን!”
ህዝቡ በበኩሉ” አታወጡም። የእግዜር ቤት ነው!”
ፍጥጫው እየረገበ ሄደ። ረሀቡን አልቻልነውም። የኪስ ብራችን የትም አላደረሠችን።
“አናምፅም ከእንግዲህ!” የሚል ግዴታ ፈርመን ተመለስን። አመዳችን ሌላ አመድ ጨምረን። ውይይት ተደርጐ ነበር-ከተመለስን በዃላ። ከሁለቱ “ሌክቸር ቲአትሮች”፣ ባንደኛው።
አንድ ተማሪ:-
“አንዳንድ ተማሪዎች ምግብ አትብሉ እያሉ፣ እነሱ ግን በሶሬሳ በር እየወጡ ሌላ ቦታ በልተው ይመለሳሉ”፣ አለ። ሶሬሳ የሚባለው ተማሪ:-
“እኔ ምን በር አለኝ?!!”፣ ብሎ አንቧረቀ። የዩኒቨርስቲው ዲን ግራ ገባው። የማያውቀው የበር ስም። ሶሬሳ ተማሪ ነው። እግሮቹ ግን ጥይት የጠባበሳቸው ናቸው። የሚፈልገውን ነገር ፍለጋ ሌትም ቢሆን ከግቢ ይወጣል። ከኛ ዶርም ጀርባ እሚገኘው የሽቦ አጥር ላይ ሾልኮ መውጫ አበጅቷል። ሾልኮ መውጫዋ ነች የሶሬሳ በር።
. . . ይቀጥላል
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው