የድምቀት ምክንያቶች

የድምቀት ምክንያቶች

በአለምሸት ግርማ

ሰዎች አቅደው አሊያም በአጋጣሚዎች ሊዝናኑ ይችላሉ። ብዙ ሰዎች ከሚዝናኑበት አንዱ የጥበብ ስራዎች (ሙዚቃ፣ ድራማ፣ ግጥም…) ተጠቃሽ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ የህዝብ በዓላት ሲካሔዱ የጥበብ ስራዎች የዝግጅቱ አካል ወይም የዝግጅቱ የድምቀት አካል ይሆናሉ። ሰዎች እንዲዝናኑ ታስቦ የሚዘጋጁ ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው። በተለይም የመድረኮች ድባብ ባህላዊ ሽታ እንዲኖራቸው የባህል ኪነት ቡድን ስራዎች ትልቅ አበርክቶ አላቸው። በዛሬው ፅሁፋችን የጌዴኦ ዞን የኪነት ቡድንን የስራ እንቅስቃሴ ዳሰናል፦

የጌዴኦ የባህል ኪነት ቡድን የተመሰረተው በ1984 ዓ.ም ነው። ቡድኑ በአሁኑ ወቅት 21 አባላት ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 13ቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው። የባህል ኪነት ቡድኑ የአካባቢውን ባህል ለማስተዋወቅ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በቡድኑ የባህላዊ ዜማዎችና ውዝዋዜዎችና ግጥሞች ይቀርባሉ። ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡት የተለያዩ ሁነቶች ሲኖሩ መሆኑን አባላቱ ይናገራሉ።

የባህል ቡድኑ አባላት በቋሚነት ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ ልምምዳቸውም በስልጠና የታገዘ ነው፡፡ ስልጠናቸውን እርስ በርስ በመተጋገዝ እንደሚያደርጉም አጫውተውናል። ሥራቸውን የሚያከናውኑባቸው በቂ የሙዚቃ መሳሪያዎችም አሏቸው፡፡ አባላቱም እንደየተሰጥአቸው የተሻለ ነገር ለመስራት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ትክክለኛውን ቱባ ባህል በማየትና በማጥናት ለማቅረብ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡

የባህል ኪነት ቡድኑ አስተባባሪ ወጣት ገዛኸኝ ገመዴ ይባላል። ስለቡድኑ ሲናገር፦ “በቡድኑ ውስጥ ያሉ አባላት ስራቸውን በትጋትና በፍላጐት ነው የሚሰሩት። ለዚህም የምናቀርባቸው ስራዎች ተወዳጅነት ያላቸው ናቸው። ብዙዎችም በርቱ፣ በዚሁ ቀጥሉ ይሉናል።”

ከቡድኑ ከቀድሞ አባላት አንዳንዶቹ የራሳቸውን ስራ ለህዝብ በማቅረብ ተወዳጅነትንና እውቅናን ያተረፉ ሲሆን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ትልልቅ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የቡድኑ አስተባባሪ አጫውቶናል።

የተለያዩ ብሔር ብሄረሰቦችን የሙዚቃ ስራዎች እንደሚሰሩና እስከ አሁንም የተለያዩ የባህል ሙዚቃዎችን በመድረኮች ለታዳሚ ማቅረባቸውን ይናገራል፡፡

በቡድኑ በተወዛዋዥነት ለረጅም ዓመታት ያገለገለችው ትዕግስት ተካ ልዩ የሆነ የውዝዋዜ ፍቅርና ችሎታ እንዳላት ትናገራለች። ልምዷንም ያዳበረቸው ከቡድኑ ባገኘችው ስልጠና መሆኑን የገለፀች ሲሆን “የባህል ቡድኑ ወደ ሙያው እንድገባና ተሰጥኦዬን እንዳወጣ አድርጎኛል”፣ በማለት ስለሁኔታው ታብራራለች።

ወደፊት የብሔረሰቡን ቱባ ባህል የሚያንጸባርቁ ሙዚቃዎችን በመስራት ባህሉ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት እንዳላትም ሃሳቧን አጋርታናለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራዊ ይዘት ያላቸውን ግጥሞች በመፃፍ በመድረክ የማቅረብ ስራ እንደምትሰራም ነግራናለች።

ሌላኛዋ ያነጋገርናት የቡድኑ አባል ወጣት ንጋቷ ገዴቼ ትባላለች። ወጣቷ በተወዛዋዥነት እያገለገለች ሲሆን ለዚህ ደረጃ የበቃችው በቡድኑ ታቅፋ ስልጠና በመውሰዷ መሆኑንም ጨምራ አጫውታናለች።

በቡድኑ የሚሰጣትን የትኛውንም ሙያዊ ስልጠና እንደምትከታተል የገለፀችልን ወጣቷ ይህም በሙያ የታገዘ ችሎታ እንዲኖራት ማስቻሉንም ትናገራለች።

ወጣት ካሳሁን ጥላሁን በቡድኑ የሳውንድ ሲስተም ቴክኒሻን ነው። ከዚህ ቀደም በፈቃደኝነት  በረዳት ቴክኒሻንነት ሲሰራ መቆየቱን ይናገራል። በዚያም ልምድ መቅሰሙን ያጫወተን ሲሆን ዋና ቴክኒሻኑ የጤና እክል ስለገጠመው ስራውን መስራት ባለመቻሉ እሱ መተካቱን አጫውቶናል። በቴክኒሻንነት መስራት ከጀመረ 5 ዓመታትንም አስቆጥሯል።

የኪነት ቡድኑ የተሟላ የሙዚቃ መሳሪያ እንዳለው የሚናገረው ወጣቱ ይህም የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው ነው የተናገረው። የተሟላ የሙዚቃ መሳሪያ መኖሩን እንደበጎ ያነሳው ወጣቱ ክፍተት የሆነባቸውን ሃሳብም እንዲህ ሲል ይናገራል፦

“የሙዚቃ መሳሪያ ያለ ጀነሬተር መጠቀም አይቻልም። ዝግጅቶች ሲኖሩ በተለያየ ቦታ ተዘዋውረን ስለምናቀርብ በዚያ የምንጠቀምበት የራሳችን የሆነ ጀነሬተር የለንም። እስካሁንም በተውሶ ነው እየሰራን ያለነው። ስለዚህ ጀነሬተር ቢኖረን በነፃነት ስራችንን መስራት እንችላለን።”

ወጣቶቹ እንዳጫወቱን ተወዳጅነትን ያተረፉት ጌዴኦ ጀባቲን እና ሻላይቱ የሚለውን ሙዚቃ የተጫወቱት አርቲስቶች የዚሁ የቡድኑ ፍሬዎች ናቸው። ሌሎችም በርካቶች የቡድኑ አባላት የነበሩ ሰዎች በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ መሰማራታቸውንና ስራዎቻቸውን ለህዝብ ማበርከታቸውን ነግረውናል። ይህም አሁን ላለው ወጣት የኪነት ቡድን አባላት የነገ ተስፋ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በርካታ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ለህዝብ ለማድረስ ጅምር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አባላቱ ይናገራሉ። በቡድኑ የሚያገኙት ስልጠናም ወጣቶች አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን መስራት እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን ነው የተነገረው።

የባህል ኪነት ቡድን ሰዎችን ከማዝናናት ባለፈ ቱባው ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ባህላዊ ክዋኔዎች በአዳዲስና ዘመናዊ ሙዚቃዎች ታጅበው አዲስ መልክ እንዲኖራቸው ዕድል ይሰጣል። አዳዲስ የጥበብ ሰዎችን ለማፍራትም ሁነኛ መንገድ ነው።