የወቅቱ የአየር ጸባይ ለአረምና ነፍሳት ተባይ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል የምርት ብክነት እንዳይከሰት ባለድርሻ አካላት የመከላከል ስራ በትኩረት እንዲሰሩ የሚዛን እጽዋት ጥበቃ ክሊኒክ ማዕከል ገለጸ
ማዕከሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚገኙ 6 ዞኖች የዕጽዋት ተባይ፣ በሽታና አረም ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን በመሰብሰብ ወደ ላብራቶሪ በማስገባት ምርምር በማድረግ መፍትሄ እንዲፈለግ እንደሚያደርግና ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
በተለይ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አመቱን ሙሉ ዝናባማ ስለሆነ በሰብሎች ላይ የዕጽዋት ተባይ፣ በሽታና አረም ሊከሰት ስለሚችል ክትትል እንዲደረግ ያሳሰቡት በማዕከሉ የዕጽዋት ጥበቃ ክሊኒክ ነፍሳት ተባይ የቴክኒክ ቡድን መሪ አቶ ሳሙኤል ሩጋ ናቸው፡፡
አሁን ወቅቱ በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ በስፋት እየለማ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ጠቁመው ከዚህ ጋር በተያያዘ የስንዴ ዋግ በሸታ መከሰቱ ታውቆ የመከላከሉ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
አርሶ አደሩም የሰብል እድገት ደረጃን ተከትሎ ማሳውን እያሰሰ ከሰብል ተባይ በሽታና አረም ማሳውን እንዲጠብቅ መክረወል።
የሰብል ተባይና በሽታ ከተከሰተ በኋላ ለመከላከል ከመሄድ ይልቅ ሰብሉ የሚያሳየውን ምልክት እየተከተሉ መከላከል ተገቢ እንደሆነም አስረድተዋል።
በተለይ በክልሉ ትኩረት ያልተሰጠው የአረም ጥቃት እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ጠቁመው አረም በወቅቱ ካልታረመና ክትትል ካልተደረገ ከ30 እስከ 40 በመቶ የምርት ብክነት ማስከተል እንደሚችል በጥናት መረጋገጡንም ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩም ሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ደጋግሞ ማረስ፣ እንዲሁም ኬሚካል ከመጠቀም ይልቅ ባህላዊ የመከላከያ መንገድን መጠቀምን ጥሩ አማራጭ አድርጎ በመውሰድ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሶስት አመታት በወባ ወረርሺኝ ሳቢያ ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዳቸው ለከፍተኛ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ
በ2016 የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው ተራራ የማልማት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ጎላ ቀበሌ ተካሄደ
የታዳጊዎች የአዕምሮ ስነ-ጤና