ለሁለንተናዊ የአካል ጤንነት ሁሉም ሰው ዘውትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል – የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከዲር
ሀዋሳ፡ የካቲት 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለሁለንተናዊ የአካል ጤንነት ሁሉም ሰው ዘውትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል ሲሉ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከዲር አሳሰቡ።
በክልሉ “ወንድማማችነት ከዋንጫ በላይ ነው”በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው 10ኛው የስልጤ ዞን ልዩ ልዩ የስፖርት ሻምፒዮና በሰላም ተጠናቋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አሊ ከድር እንደገለፁት በየደረጃው የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ሠላምን፣ ፍቅርን፣ አብሮነትንና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ መከናወን ይገባቸዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮች በሚካሄዱበት ወቅት መሸነፍና ማሸነፍ ምን ጊዜም በተጋጣሚዎች መካከል የሚከሰት ተግባር መሆኑን በመረዳት መሸነፍን በፀጋ በመቀበል ጥሩ ስነ ምግባር በመላበስ ቀጣይ አሸናፊ ለመሆን በሚያስችል መልኩ መትጋት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልፀዋል።
ዞን አቀፍ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በሰላም ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የጸጥታ አካላት፣ ለኮሚቴዎችና ለመላው የወራቤ ከተማ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መዝረዲን ሁሴን እንደገለጹት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚተው ተግባር ሳይሆን በትምህርት ቤቶች፣ በማረሚያ ተቋማት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የስራቸው አንድ አካል በማድረግ ተግባራዊ ሊያደርጉት የሚገባ ተግባር ነው።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከጤና አንጻር የሚያበረክታውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ሁሉም ሰው የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከልና ጤናማ ለመሆን ዘውትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በዞኑ በወራቤ ከተማ ሲካሄድ በነበረው ስፖርታዊ ሻምፒዮና 10 ወረዳዎችና 5 የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን በማሳተፍ በ13 የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ እንደነበር የገለፁት ደግሞ የስልጤ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ኑረዲን ሶንችላ ናቸው።
ውድድሩ ዞኑን ብሎም ሀገርን የሚወክሉ ስመጥር ስፖርተኞችን ለማፍራት ከማገዙም ባሻገር ቀጣይ በክልል ደረጃ በሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚሳተፉ ስፖርተኞችን መለየት የተቻለበት መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ኑረዲን አክለውም የተሉያዩ ዘመናዊና ባህላዊ የስፖርት አይነቶች ከ2ሺ በላይ ስፖርተኞችን በማሳተፍ ከጥር 28 እስከ የካቲት 13/2016 ዓም ድረስ ያለምንም የጸጥታ ችግር ኢንዲጠናቀቅ ለማድረግ በቅድመ ዝግጅት ወቅት የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀርና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት በመቻሉ የተጠበቀውን ውጤት ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በማጠቃልያ ስነሥርዓቱ የጦራ ከተማ አስተዳደር የእግር ኳስ ቡድን ከአቻው የአሊቾ ውሪሮ ወረዳ እግር ኳስ ቡድን ለዋንጫ የተገናኙ ሲሆን የጦራ ከተማ አስተዳደር 1ለ0 በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል።
ዘጋቢ: ሳሊክ አህመድ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ