ቢሮው በጉዳዩ ላይ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሰጠ ሲሆን መድኃኒቶች የታዘዙለትን ዓላማ እንዳያሳኩ የሚያደርገው ይህ ችግር በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ጤና ላይ ከፍተኛ ሥጋት እየደቀነ መሆኑ ተመላክቷል።
በሥልጠናው ላይ የተገኙት የቢሮው የመድኃኒት ግብዓት ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ይስሃቅ፤ መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድና አቋርጦ መተው ጀርሞች መድኃኒቱን እንዲላመዱና በሽታዎች በቀላሉ እንዳይድኑ እያደረገ ይገኛል። ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቀልበስም የሚዲያ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ ግንዛቤ የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሥልጠናውን የሰጡት ዶ/ር ታምራየሁ ሾንዴ እና አቶ ሠራዊት ዲባባ በበኩላቸው፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒት መላመድ የሕክምና ወጪን ከመጨመሩም በላይ ለሞት የመጋለጥ ዕድልን እንደሚያሰፋ አስረድተዋል። ችግሩን ለመቅረፍም “አንድ ጤና” የተሰኘውን መርህ በመከተል በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል ጥላሁን ጌታቸው እና ስመኝ አክሊሉ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደነበር ገልጸው በቀጣይ ግን የተሳሳቱ የአጠቃቀም ልምዶችን ለመለወጥና ኅብረተሰቡን ለማንቃት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
ይህ ሥልጠና ከተለያዩ የክልል ሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይም መሰል የግንዛቤ መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት በ2018 በጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ከዞኑ ንግድና ትራንስፖርት መምሪያዎች ጋር የህዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሄደ
የወጣቶቻችንን ያልተገደበ ምናብ እና የእጆቻቸውን ጥበብ ወደ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሣይንስ፣ የፈጠራ ስራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ መካሄድ ጀመረ