መምህራን የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅምና መብት በማስጠበቅ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር አስታወቀ

የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር 7ኛው ዙር የመምህራን ቀን በዓል “Together For Teachers, Together For Tomorrow” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ በርታ ያረቢ እንደገለፁት፤ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ በተማሪዎች ውጤት መሻሻልም ሆነ ማሽቆልቆል ላይ የመምህራን ብቃትና ተነሳሽነት ትልቁ ስፍራ ይይዛል።

ስለሆነም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት በመስራት ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት ይጠበቃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ መምህራን የሚገባቸውን ጥቅምና መብት በአግባቡ ከመከታተልና ከማስጠበቅ አኳያ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና ተወካይ አቶ ዳርጌ ተክሉ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በሃገር ደረጃ አንጋፋና ግንባር ቀደም መሆኑን በመግለፅ አላማውም ሙያተኛው የተጣለበትን መብትና ግዴታውን በማወቅ በሃላፊነትና በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል ያለመ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ትምህርት ለሰው ልጅና ለሃገር እድገትና ለውጥ መሰረት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳርጌ፤ እንደ ሃገር የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ መምህራን የማይተካ ሚና እንዳላቸውና በቀጣይ ለዘርፉ ውጤታማነት መሰል ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል በማለት አሳስበዋል።

እንደ ጉራጌ ዞን ትውልዱ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝና በእውቀት እንዲታነፅ ከማድረግ አንፃር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ዳርጌ የትምህርት ሙያተኛው ከመደገፍና ከማብቃት አኳያ በትኩራት መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ በዞኑ ባለፉት አመታት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ከፍ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት በጀት በማሰባሰብ ከ4 መቶ 85 ሺህ በላይ የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሀፍትን በማሳተም ለተማሪዎች ማዳረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

በዞኑ ከ7 ሺህ 8 መቶ በላይ መምህራን እንዳሉ በማንሳት እነዚህ መምህራንን ማክበር፣ መጠበቅና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

በዞኑ ሞዴል መምህራን ማበረታታትና እውቅና መስጠት በቀጣይ የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባር ለማሻሻል የበለጠ ስራ እንዲሰሩ ከማድረጉም በላይ በሌሎች መምህራን ላይ መነሳሳት ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የዞኑ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ አግዛ ግርማ፤ ትምህርት ለአንድ ሃገር ሁለተናዊ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረው፤ መምህራን ንቁ፣ ጤናማና ባለ ራዕይ እንዲሁም ሃገር ተረካቢ ዜጋን የመቅረፅ ሃላፊነት የተጣለባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

መምህርነት የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አግዛ፤ ማህበሩ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም በማስከበርና ክህሎታቸውን በማዳበር በትምህርትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሚገኝ አውስተዋል።

በመድረኩ ላይ ከታደሙ መምህራን መካከል እንዳሉት የመምህራን ቀን መከበሩ በቀጣይ ስራቸው በንቃትና በጥራት እንዲሰሩ የሚያበረታታ መሆኑን በመግለፅ የመምህራን ጥቅማ ጥቅምን በማስከበር በክህሎት የመገንበትና የማብቃት ጉዳይ ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ተማሪዎች በእውቀትና በስነ ምግባር በማነፅ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት ይሰራል በማለት ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወልደማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን