የኤች አይ ቪ ኤድስን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የማስገንዘብ ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኤች አይ ቪ ኤድስን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የማስገንዘብ ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ መሆኑን በኣሪ ዞን የጂንካ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ገልጿል።
የጂንካ ከተማ አሰተዳደር ጤና ጽ/ቤት የዘርፈ ብዙ ኤች አይ ቪ ኤድስ የ6 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩን በጅንካ ከተማ አካሄዷል።
በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ወልዴ እንደተናገሩት፤ እንደ አጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ኤችአይቪ ኤድስን ከመከላከል አንፃር በተደረገ ምርመራ 8 መቶ 45 ያህል ሰዎች ውስጥ 47 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ቫይረሱ በደማቸው የተገኘ ሲሆን እንደ ጂንካ ከተማ የስርጭት ምጣኔው 5.37 በመቶ ደርሷል፡፡
በሽታው ወደ ወረርሽኝ የደረሰ በመሆኑ በተለያየ መንገድ ሰዎች የግንዛቤ ለውጥ እንዲያመጡ የመከላከሉ ሥራ በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በኤች አይ ቪ ላይ በቫይረሱ በይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑት ማለትም የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ወጣቶች ፣ የማረምያ ተቋም ታራሚዎችን ጨምሮ ሌሎችም ተጠቂ የሆኑ አካላት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደምሠራም አክለው ገልፀዋል።
ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ አካላትም እንደ ተቋም ሰልጠና ሰጥቶ በማስመረቅና አጠቃላይ የባህሪ ለውጥ ላይ ሥራዎች የተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኃላፊው አክለውም የቫይረሱ ስርጭት መጨመር ተጨማሪ የግንዛቤ ሥራው እንዲጠናከር የሚያሳይ መሆኑንም አመላክተዋል።
የግሎባል ፈንድ ድርጅት ባለሙያ ሲስተር ኖሀሚ ተስፋዬ በበኩላቸው ድርጅቱ በኤች አይ ቪ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማስገንዘብና ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ከተሣታፊዎች መካከል መላከ ፅዮን ቄስስ ከባዱ አበበ፣ አቶ ሶይቲ አንክሽና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት ከመድረኩ ትልቅ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና በቀጣይም በየድርሻቸው ህብረተሰቡን በማስገንዘብ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻ የማሳ ዝግጅት ቢያደርጉም በቂ ግብዓት አለማግኘታቸውን ገለጹ
ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የህዝብና የመንግስት አገልግሎቶችን የሚያፋጥን በመሆኑ ለሁሉም ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ