ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚጠይቀውን የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማፋጠን ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ታክስ በወቅቱና በታማኝነት መክፈል እንዳለበት የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ አዲስ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ዙሪያ የተጠናከረ ግንዛቤ እንዲያገኝ እየተደረገ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
በጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ የታክስ ትምህርት ኮሚኒኬሽንና ቅሬታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት አሰተባባሪ ወ/ሮ ሙርሺዳ አክመል፥ መምሪያው አዲስ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ላይ ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በየጊዜው የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀዋል።
እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ ከዚህ ቀደም 3 ደረጃ የነበረው የግብር ከፋዮች ደረጃ በአሁኑ ወቅት በሁለት ደረጃ ማለትም በ”ሀ”እና ”ለ”ደረጃ ብቻ ተወስኖ እንደሚገኝና ለእነዚህም ወቅቱን የጠበቀና ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ትምህርት እየተሰጣቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የክህሎት ስልጠናው አገልግሎት ሰጪዎች ለማህበረሰቡ መብትና ግዴታን፥ በግልጽ በማስረዳት ተገልጋዮችን ለእንግልት የሚዳርጉ አሰራሮችን ለማስቀረት የሚያግዝ እንደሆነም ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።
ለግብር ከፋዮች የተፈጠረው ግንዛቤ በተሻሻለው በአዲሱ የገቢ ግብር በውስጡ እንዲካተት መደረጉንና ይህም አማራጭ አነስተኛ ገቢ ግብር ላይ የተጣለውን ታክስ እንዲፈፀም ገደብ ማስቀመጡን ወ/ሮ ሙርሺዳ አስረድተዋል።
ይህም ህግና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ተገልጋዩ ቀላልና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት አስተባባሪዋ።
አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ የተሻሻለባቸው ሰባት አላማዎች መኖራቸውን ያወሱት ወ/ሮ ሙርሺዳ ከነዚህም መካከል አንዱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚፈጥረውን የገቢ ግብር ጫና መቀነስ እና የታክስ መሰረቱን ማስፈን እንዲሁም የፍትሃዊነት ችግር መቅረፍ የሚሉት ይገኙበታል ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ግብር ከፋዮች አመታዊ ግብራቸውን አሳውቀው በዓመት መጨረሻ በአንድ ጊዜ አጠቃለው ሲከፍሉ እንደነበር በማውሳት ይሁን እንጂ አዲስ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ላይ በዓመት አራት ጊዜ በየ 3 ወሩ እንዲከፍሉ መደረጉን አስረድተዋል።
አሁን ላይ የግብር ከፋዮች ምጣኔ በሠንጠረዥ ተሻሽሎ መቅረቡን የገለፁት ወ/ሮ ሙርሺዳ ይህም በዘመናዊ አሰራር የተደገፈና
የአገልግሎት አሰጣጥ ጽንሰ ሃሳብ በስልጠናው ላይ እንዲካተት መደረጉን አብራርተዋል ።
ስለሆነም ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚጠይቀውን የልማትና መልካም አሰተዳደር ተግባራትን ለማፋጠን ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ታክስ በወቅቱና በታማኝነት መክፈል እንዳለበት አስታውቀዋል።
በዞኑ በባለፋት 6 ወራት ከ17 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በአዲሱ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል።
በወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር አግኝተን ያናገጋርናቸው ግብር ከፋዮች በሰጡት አሰተያየት በአዲሱ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ላይ በየጊዜው በባለሙያዎች በኩል ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው እንደሆነ ተናግርዋል።
በዚህም በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ በሚያገኙት ገቢ ላይ ለመንግሥት የሚገባውን ታክስ በአመት አራት ጊዜ ከፋፍለው በወቅቱ በታማኝነት እየከፈሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን የዑባ ደብረፀሐይ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲውን በሀብት ለማጠናከር ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
የጓሮ አትክልትና የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻላቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሶያሜ ቀበሌ አርሶአደሮች ተናገሩ
በከተማው በተያዘው በጀት ዓመት በ5 ወራት ውስጥ 1 ቢሊየን 5 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ