በይበልጣል ጫኔ
በሰሞኑ የአንድ ወዳጃችን ሚሰት ወልዳ÷ አራስ ጥየቃ ሄደን ነበር። እኔ በግሌ አራስ መጠየቅ ላይ እምብዛም ነኝ። በተለይ “ገንፎ ካልበላህ” ብለው ካስገደዱኝ÷ ምነው ሳልጠይቅ በቀረሁ እላለሁ። ገንፎ ይጨንቀኛል። ክፉ ዘመን የፈጠረው ፈጣን የርሃብ ማስታገሻ ይመስለኛል። ቶሎ ለወስ ለወስ አድርገው÷ ሳይበስል የሚበሉት ዓይነት።
እናላችሁ÷ ወዳጃችን ቤት ደርሰን ሚስቱን እንደጠየቅን÷ የፈራሁት ሆነ። አራሷን ለመንከባከብ በተጠንቀቅ የቆሙት ሴቶች÷ በቅፅበት ትሪ ሙሉ ገንፎ ፊት ለፊታችን አስቀመጡ። ጓደኞቼ በምን ፍጥነት ማንኪያውን አንስተው እንደተሰለፉ÷ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው።
አዛዛቃቸውን ላስተዋለማ÷ አርማታ የሚያቦካ የግንባታ ባለሙያ ይመስላሉ። ገንፎውን ካቀረቡት ሴቶች አንዷ፦
“አያያዛችሁ በጣም ደስ ይላል÷ ብሉ እስኪ” እያለች ስትጋብዝ÷ ድንገት ተያየን። እኔ እየበላሁ አልነበረም።
“ብላ እንጂ ምነው?÷ የጓደኞችህ አበላል እንኳን አያስቀናህም እንዴ?” አለችኝ።
ገንፎ እንደማልወድ ነገርኳት። ቆሎ እና ውኃ ሰጠችኝ። ጓደኞቼ ትሪውን ታጥቦ የተወለወለ አስመስለው ሲመልሱት÷ የኔ ገንፎ አለመውደድ ርዕስ ሆኖ ጨዋታ ቀጠለ። እስከዚህ ሰዓት ድረስ ድምፃቸውን ያልሰማናቸው በዕድሜ ጠና ያሉ ሴትዮም÷ ወደ ጨዋታው ተቀላቀሉ። የመንደርደሪያ ሃሳባቸው የሚከተለው ነበር፦
“ገንፎ ጥሩ ምግብ ነው። ወገብ ይጠግናል። ይኼ ጓደኛችሁ ግን ምናልባት ስለ ገንፎ የሰማው ነገር÷ ሞትን ያስታውሰው ይሆናል። በዚያ መነሻነት ለምግብነት ባይመርጠው አይፈረድበትም” አሉ።
እንደሌላው የምግብ ዓይነት÷ ማናችንም ገንፎ ልንወድ አሊያም ልንጠላ እንችል ይሆናል። ገንፎን ከሞት ጋር ሊያዛምደው የሚችል አንዳች ነገር ስለመኖሩ ግን ማናችንም አላወቅንም። ለዚህ ይመስላል ሴትዮዋን በጥያቄ ዓይን ያየናቸው። አንዳችን እንኳን ስላሉት ነገር ፍንጭ እንደሌለን ሲያውቁ÷ ከታች ያሰፈርኩትን ሃሳብ ሰነዘሩ፦
የወለደችን ሴት ለመጠየቅ ሲኬድ የሚቀርበው ገንፎ እና የሚቀርብበት መንገድ÷ ትልቅ ምስጢር ያዘለ ነው። አዲሱን ህፃን ስናይ ህይወትን እናስባለን። ገንፎው ደግሞ ሞታችንን ወይም መቃብራችንን ያስታውሰናል። ዙሪያውን የሚቆለለው ገንፎ የመቃብር አፈርን የሚወክል ነው። መሃል ላይ ማባያ ቅቤ የሚደረግበት ስርጉድ ደግሞ የመቀበሪያ ጉድጓዳችን ምሳሌ ነው።
በጥንት ጊዜ በእንጨት ወይም በቀንድ የሚሰሩ ማንኪያዎች እንጠቀም ነበር። አሁን ደግሞ የምንገለገለው በብረት ማንኪያ ነው። በእነዚህ ማንኪያዎች ከክቡ ዙሪያ ገንፎውን እየዛቅን መሃል ላይ ማጥቀሳችንም÷ በአካፋ እየተዛቀ ወደ መቃብራችን የሚመለስን አፈር ይመስላል። በአጠቃላይ አራስ ቤት ሄደን የምንበላው ገንፎ÷ “የመወለድ ቀን እንዳለ ሁሉ የመሞት ቀን አለ” የሚል መልዕክት ያዘለ ነው።
ሴትዮዋ ያነሱት ሃሳብ ይገርማል። እንዲህ የሚባል ነገር ስለመኖሩ የሰማነው ዛሬ ነው። እኔ ከመገረም ውጪ የተሰማኝ ነገር የለም። ጓደኞቼ ግን ያንን ሁሉ ገንፎ ዝቀው÷ ነገርየው ከመቃብር ጋር ሲያያዝባቸው ለሆዳቸው ምቾት የሰጣቸው አልመሰለኝም። ቅድሚያ ሲግደረደሩ የነበሩት ልጆች ይኼንን ታሪክ ከሰሙ በኋላ አረቄ መጠጣታቸው÷ ያልተመቻቸው ነገር እንዳለ የሚያስረዳ ይመስለኛል። ቢሆንም… ቢሆንም… የመቃብር ጉድጓድ በአረቄ ምርኩዝ እንደማይዘለል÷ ላስታውሳቸው እወዳለሁ።
በነገራችን መካከል÷ የገንፎው ምሳሌ ቢሆንም ባይሆንም÷ “የመወለድ ቀን እንዳለ ሁሉ የመሞት ቀን እንዳለ” ማሰብ ጥሩ ይመስለኛል። ይመስለኛል ያልኩት ነገሩን ለማዋዛት ነው እንጂ÷ ባይመስለኝም የሚቀየር እውነታ አይኖርም። ምክንያቱም÷ መወለድም መሞትም የሰው ልጅ መንታ ተፈጥሮዎች ናቸው።
ዛሬ ዛሬ ግን አኗኗራችንን ላየ÷ ሟች መሆናችንን እንደረሳን ይገነዘባል። ተደጋግፎ ማለፍ ላያጎድለን፣ መተሳሰብ አንዳች ላያሳጣን÷ የዘመናችን ፈሊጥ ጥሎ ማለፍ ሆኗል። በብልኃት ማደሩ ቀርቶ÷ የሰው ልጅ መተዳደሪያው ብልጣብልጥነት ሆኗል።
ዘንድሮ ይዘህ ተገኝ እንጂ÷ እንዴትም ብታመጣው ነገሬ የሚልህ የለም። “ያመጣህበት መንገድ ትክክል አይደለም” ብሎ የሚከተልህ እንኳን ቢኖር÷ ድርሻውን ሊቀበልህ እንጂ ፍትህ ሊያሰፍን አይደለም። በዚህም ምክንያት÷ አብዛኛው ገበታ ላይ የሚቆረጠው እና የሚጨለጠው የድኃ እንባ እና ላብ አለበት። ምናልባትም እንደ ገንፎው ሁሉ ሌሎቹም ገበታዎቻችን ሞታችንን በሚያሳስብ አውድ ቢቀርቡ ሳይሻል አይቀርም።
በጥንት ጊዜ አንድ ንጉስ ሟች መሆኑን እንዳይዘነጋ እና ሰዎችን እንዳይበድል÷ አስታዋሽ መድቦ ነበር÷ አሉ። አስታዋሹ ሽማግሌ ስራው አንድ ብቻ ነው። ንጉሱ በመንበሩ ተሰይሞ እያለ ድንገት እየገባ፦
“ትሞታለህ!” ይለዋል።
ይኼ ንጉስ በማዕድም ይቀመጥ በችሎት÷ ሽማግሌው ሰዓት እየጠበቀ “ትሞታለህ!” ማለቱን አይተውም። ንጉሱም ዕለት ዕለት ሟች መሆኑን በማሰብ ድኃ ሳይበድል÷ ፍርድ ሳያጓድል ኖረ÷ ይላሉ።
እኔም ከዚህ ታሪክ በመነሳት ለባለ ብሩም÷ ለባለወንበሩም በየደረሱበት ሁሉ እየተከተለ “ትሞታለህ!” የሚል ቢኖር÷ ጥሩ ነው እላለሁ። ያነሳሁት ሃሳብ ቀጣዩን ለማለት ዕድል ስለሰጠኝ እንዲህ አልኩ እንጂ÷ ሰዎቹ ይህን ቢባሉ “ትሞታለህ!” ባዩን ሳይገድሉ÷ እንቅልፍ የሚወስዳቸው አይመስለኝም።
እርግጥ ባለ ብሩም ሆነ ባለ ወንበሩ አንዳች ነገር ለመናገር ስለሚመቹ እንጂ÷ ዘንድሮ ሟች መሆኑን ያልዘነጋ ሰው ፈልጎ ማግኘት ይቸግራል። ጥሎ ማለፍ ከኳስ ሜዳ ይልቅ በእውነተኛው የህይወት ሰልፍ ላይ በርትቷል።
የሆነ ሰው ሰርቆም ይሁን ቀምቶ አንዳች የሚታይ ነገር ሲኖረው÷ እንደ ጥንቱ ድርጊቱን የሚፀየፍ ሰው አይገኝም። ባይሆን “ምናለ እሱን ባደረገኝ!” እያለ የሚዘፍነው ብዙ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ሰው በሌብነት ድርጊት ቢያዝ÷ ለዘመዶቹ እና ለሚያውቁት ሰዎች ሁሉ እፍረት ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን “እገሌ እኮ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ተያዘ” ሲባል÷ ሰዉ ማፈሩን ትቶ ሂሳብ መስራት ጀምሯል። እስረኛውን ሊጠይቅ የሄደ ሰው፦
“ተሳስተሃል÷ እንዲህ ማድረግ አልነበረብህም” በማለት ፈንታ፦
“ጀግና ነህ÷ ይኼንን ያክል ብር ብትሰራም መያዝ ስለማትችል÷ አስርህን ጨርሰህ ስትወጣ የግል ‘ቢዝነስ’ ትጀምርበታለህ” ብሎ ያበረታታል። እንዲህ ያለው ሰው ዕድሉን ቢያገኝ÷ እጥፉን ይመዘብር እንደሆነ እንጂ ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም።
ወዳጆቼ÷ እዚህ ምድር ላይ ለመኖር ብዙ ነገር ያስፈልገናል። የሚያስፈልገንን ሁሉ ለማግኘት ግን ሰዋዊ ባህሪያችንን ማጣት ተገቢ አይደለም። እንደ ንጉሱ በራሳችን ላይ የምንሾመው “ሽማግሌ” ባይኖረን እንኳን÷ ህሊናችን ቅጥሩን ማፍረስ ሲሻ÷ ራሳችንን “ትሞታለህ!” እንበለው።
More Stories
የ28 ዓመታት ትዝታ እና ፈተናዎች
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ