“ለሀገር ክብር የተከፈለ መስዋዕትነት” – አቶ ተፈራ ፈለቀ
በአንዱዓለም ሰለሞን
ለዛሬው በዚህ አምድ ስር ታሪካቸውን ከማወጋችሁ ሰው ጋር የተገናኘነው መኪና ውስጥ ነበር፡፡ ያገናኘን መንገድ ነው፡፡ ለስራ ጉዳይ ወደ ባስኬቶ ዞን ዋና ከተማ፣ ላስካ ባመራሁበት ወቅት ከሳውላ ወደ ላስካ በሚሄደው መኪና ውስጥ ተቀምጬ ሳለ ባለታሪካችን ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ትውውቃችን ከእዚያ ጀምሮ፣ መኪናው እስከሚሞላና ጉዞ እስከምንጀምር፣ ብሎም በመንገዳችን በነበረን ቆይታ ብዙ ተጨዋውተናል፡፡
ጨዋታ አዋቂና የማይከብዱ፣ ተግባቢ ሰው ናቸው፡፡ በህይወታቸው ካሳለፉት ውጣ ውረድ ባሻገር የአንድ ታላቅ ታሪክ ባለቤት መሆናቸው ከተራ ጭውውት ባለፈ መቅረጸ ድምጼን ካኖርኩበት አውጥቼ ወጋቸውን እንድካፈል አድርጎኛል፡፡
ለ34 ዓመታት የላስካ ነዋሪ የሆኑት እኚህ ሰው አቶ ተፈራ ፈለቀ ይባላሉ፡፡ ትውልድና እድገታቸው አማሮ ኬሌ ቢሆንም በዚያ የቆዩት እስከ 9 ዓመታቸው ብቻ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ ሀሳብ ወደ አእምሯቸው መጣና ለማንም ሳይናገሩ የትውልድ ቀያቸውን ጥለው የጌዴኦ ዞን ካለችበት ከተማ ጨለለቅቱ ወደሚባል አካባቢ፡፡
ይህ ጉዞ ውሳኔያቸው ትክክል እንዳልነበር ያስገነዘባቸው ብቻም ሳይሆን በእጅጉ የተፈተኑበት መሆኑን ያስታውሳሉ፡-
“ቀኑ የገበያ ቀን ነበር፡፡ ነጋዴዎችን በቅርብ ርቀት ተከትዬ ነበር የምጓዘው። ለጉዞዬ የሚረዳኝን ባትሪና የሚበላ ነገር ገዝቼ ይዣለሁ፡፡ በዚህም ያን ያህል ችግር እንደማይገጥመኝ አስቤ ነበር፡፡ በመሀል የምከተላቸው ነጋዴዎች አዩኝና ገርፈው አባረሩኝ፡፡ እያለቀስኩ ተመለስኩና ጫካ ውስጥ ገባሁ፡፡ ከዛም በርቀት እያየኋቸው ተደብቄ እከተላቸው ጀመር፡፡ አመሻሽ ላይ ገላና የሚባል ወንዝ አጠገብ ስንደርስ ግን ያልጠበኩት ነገር አጋጠመኝ፡፡
ነጋዴዎቹ ወንዙን ተሻግረው ሄደው እሳት እያነደዱ ነበር፤ አውሬ ለመከላከል፡፡ ድንገት አንበሶች መጡብኝ፡፡ አማራጭ ስላልነበረኝ ዘልዬ ወንዙ ውስጥ ገባሁ፡፡ ዋና መቻሌ ቢጠቅመኝም ነገሩ ከባድ ነበር፡፡ ሁኔታውን የተመለከቱት ነጋዴዎቹ እሳት የያዘ እንጨት አንበሶቹ ላይ በመወርወርና እኔን በማገዝ ህይወቴን ታደጓት፡፡ ከዚያም ከእነርሱ ጋር በመሆን ጉዞዬን ቀጠልኩ” በማለት አሁንም ድረስ የተለየ ስሜት የሚፈጥርባቸውን የልጅነት ትዝታቸውን አወጉኝ፡፡
ጨለለቅቱ እህታቸውን አግኝተው እዚያ አንድ ዓመት ከተቀመጡ በኋላ ወደ አዲስ አበባ አመሩ፡፡ አዲስ አበባ የሄዱት ከእህታቸው ጋር በመሆን ታላቅ ወንድማቸውን ለመጠየቅ ነበር፡፡ ታላቅ ወንድማቸው ግን እርሱ ዘንድ ሆነው እንዲማሩ ጠየቋቸው፡፡ እሳቸውም በወንድማቸው ሀሳብ ተስማምተው ኑሯቸውን በአዲስ አበባ በማድረግ ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡
በ1965 ዓ.ም አንደኛ ክፍል ገቡ፡፡ ከዚህ ቀደም፣ አማሮ ኬሌ ሳሉ የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል በመቁጠራቸው ትምህርቱ ብዙም አልከበዳቸውም፡፡ ከክፍል ክፍል ሲሸጋገሩ ያስመዘግቡ የነበረው ውጤትም ጎበዝ ተማሪ መሆናቸውን ያስመሰከረ ነበር። በወቅቱ በነበረው የትምህርት ስርዓትና ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት በአንድ ዓመት ሁለት ክፍሎችን በመማር ነበር የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት፡፡
በዚህ መልኩ ተምረው፣ ስምንተኛ ክፍል ጥሩ ውጤት በማምጣት 9ኛ ክፍል ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ከፈጸሙ በኋላ አስራ አንደኛ ክፍል እያሉ በእድገት በህብረት ዘመቻ ወደ ቀድሞ ኢልባቦር ክፍለ ሀገር አመሩ፡፡ በወቅቱ ኢልባቦር ክፍለ ሀገር፣ ሶርና ገባ አውራጃ፣ ኖጳ ወረዳ የእርሳቸውና ከእርሳቸው ጋር የዘመቱ ወጣቶች መቀመጫ ነበረች፡፡
ወጣቶቹ ህብረተሰቡን ለማገልገል በተፈጠረላቸው እድል ደስተኞች ነበሩ፡፡ ሁሉም በየምድብ ጣቢያዎቻቸው በመሆን በዘመቻው የተጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣትና ስምንቱን ተግባራት ለመፈጸም ደፋ ቀና እያሉ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ግን አንድ ክፍተት ተፈጠረ፡፡ ከእነርሱ ጋር ተመድበው የነበሩት የባለስልጣን ልጆች ውሎና ተግባር ከሌሎቹ ተማሪዎች ለየቅል ሆነ፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ውሎና አዳራቸው በካምፕ ውስጥ ሲሆን እነሱ ግን ቤት ተከራይተው ነበር የሚኖሩት፡፡ ትኩረታቸውም ከስራ ይልቅ መዝናናት ላይ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የሌሎቹን ተማሪዎች ሞራል የሚነካ ነበር። በዚህ የተነሳም ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ፡፡ ባለታሪካችንና የተወሰኑ ተማሪዎች ደግሞ ለተማሪዎቹ ጥያቄ የተለየ ትኩረት በመስጠትና ተማሪዎቹን በማስተባበር አመጽ ቀሰቀሱ፡፡ ባለታሪካችን ይህን ታሪካቸውን ሲያጫውቱኝ የነብይ መኮንንን አንድ ግጥም ማስታወሴ አልቀረም፡-
“… ዕድገት በህብረት ተብዬ
በህብረት ዕብደት አብቅዬ
ባልበሰለ የልጅነት ሩጫ፣ ባራዳ ጨርቅ ተጠቅልዬ
ገጠርክን ስልጡን ላደርገው፣ እንደኔው ከተሜ ብዬ
እኔው ለራሴው እንግዳ፣ ላንተ እንግድነት ተልኬ!!
ታወጅኩብህ “ሰው ላረግህ” በቃላት ዲስኩር ጮኬ!! …”
አመጹ የባለስልጣናቱን ልጆች በቁጥጥር ስር ወደ ማዋልና ቅጣት ወደ መፈጸም ተሸጋገረ፡፡ ይህ ድርጊታቸው በአውራጃው ፖሊስ ከሚሽን ጣልቃ ገብነት ቢቆምም በቀላሉ የተፈታ ጉዳይ እንዳልነበር ባለታሪካችን ያስታውሳሉ፡፡ በመጀመሪያ የመጡትን ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አውለው ትጥቅ እስከማስፈታት ድረስ ደርሰው ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ አስቀድመው ከመሬት ከበርቴዎች የተረከቡት መሳሪያ እንደረዳቸው ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ የወረዳው ፖሊስ ኮሚሽን ተጨማሪ ሀይል በመላክ ያመጹትን ተማሪዎች በቁጥጥር ስር አዋላቸው፡-
“በቁጥጥር ስር ካዋሉን በኋላ መቱ ከተማ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ለአንድ ወር ታሰርን። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተወስደን ለሶስት ወራት በእስር ቆየን፡፡ ቅጣታችንን ከጨረስን በኋላ ለድጋሚ ዘመቻ አዋጅ ሲታወጅ ዳግም ወደ ዘመቻ ተመለስን፡፡ እኔም ወደ ወላይታ አመራሁ” በማለት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡
አቶ ተፈራ በገሱባ ቆይታቸው ከሌሎች ዘማቾች ጋር በመሆን የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ በመወጣት የምስክር ወረቀትና የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡-
ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት “ለዘማች መምህራን” በሚል ባወጣው የስራ የቅጥር ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድረው በማለፍ ተቀጠሩ፡፡ ከቅጥሩ በኋላ ስልጠና በመውሰድም ለስድስት ወራት በኮንትራት ሰሩ፡፡ በወቅቱ ስልጠናውን የሰጧቸው ታዋቂው አርመናዊ የሙዚቃ ባለሙያ ሙሴ ነርሲስ ሳናልቫንዲያን ነበሩ፡፡ ስልጠናውን ከወሰዱ 200 ሰዎች አንዱ እንደነበሩ ያስታወሱት ባለታሪካችን በተለያዩ መድረኮች ላይ በመገኘት ሥራዎቻቸውን ያቀርቡ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የሄዱት ወደ ሀረር ነበር። በተለይም በሀረርና በኤጀርሳ ጎሮ የቴሌ ኦፕሬተር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በእዚያ ብዙም ሳይቆዩ ግን የሱማሊያ ወራሪ በሀረርጌ ክፍለ ሀገር የተለያዩ አካባቢዎች ሰርጎ በመግባት ጥቃት አደረሰ፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ ሲሄድ በርካታ ወጣቶች ሀገራቸውን ከወራሪው ለመከላከል በፍቃደኝነት ዘመቱ፡፡ ከእነዚህ ዘማች ወጣቶች መካከልም ባለታሪካችን አንዱ ነበሩ፡፡
ያለ በቂ ስልጠና የወራሪውን ሀይል በሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔ የተጋፈጡት እነዚህ ወጣቶች ማዕከላዊው መንግስት ያሰለጠናቸው ሚኒሻዎች እስከሚደርሱ ድረስ የጠላትን ጦር በመፋለም ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል። “የመቶ መሪ” የነበሩት ባለታሪካችንም በስራቸው ከነበሩት ወታደሮች ጋር በመሆን ለሀገራቸው ክብር ሲሉ በጫካና በዱር በገደሉ ከጠላት ሰራዊት ጋር ተፋልመዋል። ከሚኒሻውና ከጦር ሰራዊቱ ጋር በመሆንም ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡
የሱማሌ ወረራ በአንጸባራቂው የካራማራ ድል ተደምድሞ የሀገራችን ነጻነት ከተበሰረ በኋላ ባለታሪካችን የጅጅጋ መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ አባል በመሆን ሰርተዋል፡፡ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ከመንግስት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
“ይህ ለሀገር ክብር ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ ትውልዱ ይህን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በወቅቱ ብዙዎች ለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ ተሰውተዋል፡፡ በህይወት የተረፉትም አብዛኞቹ አስታዋሽ አጥተዋል፡፡ ያም ሆኖ የዚህ ታሪክ አካል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ”
ከዚህ በኋላ የባለታሪካችን ማረፊያ የሆነችው ሳውላ ከተማ ነበረች፡፡ በቀድሞ ስያሜዋ ፈለገ ነዋይ በመባል ትታወቅ የነበረችው ይህች ከተማ ለ9 ዓመታት የኖሩባትና ህይወታቸውን በተለየ መልኩ የመሩባት እንደሆነች ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት መተዳደሪያቸው የሆነውን የልብስ ስፌት ሙያ የጀመሩት በሳውላ ሳሉ ነበር፡፡
ከሳውላ ከተማ የዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ባስኬቶ፣ በማምራት ኑሯቸውን በላስካ ከተማ ካደረጉ እነሆ 34 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ትዳር መስርተው አምስት ልጆችን ያፈሩባትን የላስካ ከተማም “ብዙ በረከት ያገኘሁባት” በማለት ይገልጿታል። ከበፊቱ አንጻር ሲመለከቱት ከተማዋ አሁን በሚታይባት ገጽታና ለውጦች ደስተኛ መሆናቸውም ይናገራሉ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው