“አደረጃጀት ልማትን የምናፋጥንበት ስልት ነው” – አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል

“አደረጃጀት ልማትን የምናፋጥንበት ስልት ነው” – አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል

የዛሬ የንጋት እንግዳችን አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል ይባላሉ፡፡ የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ጋራ የም በቅርቡ ከልዩ ወረዳነት ወደ ዞን ማደጉን ተከትሎ በዞኑ ስላሉ የልማት እንቅስቃሴዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በመለሰች ዘለቀ

ንጋት፡- እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሳሙኤል፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ለመግቢያ ያህል ከውልደትና እድገትዎ እንጀምር?

አቶ ሳሙኤል፡- ተወልጄ ያደግኩት በየም ዞን ፎፋ ወረዳ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ሰሙናማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ጅማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ፡፡

በ1997 ዓ.ም ከሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በዲፕሎማ ከተመረኩ በኋላ ወደ ስራ አለም ተቀላቀልኩ፡፡ በመምህርነት፣ በሱፐርቫይዘርነት፣ በትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊነት እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ አገልግያለሁ። በመቀጠልም በቀድሞ ደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተር በመሆን ለአራት ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ በስራ ላይ እያለሁ አንደኛ እና ሁለተኛ ድግሪዬን የመከታተል እድል አግኝቻለሁ፡፡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የቀድሞው የየም ልዩ ወረዳን ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፡- አጠቃላይ የዞኑ ገጽታ ምን ይመስላል?

አቶ ሳሙኤል፡- ዞናችን በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምስረታ ተከትሎ ቀደም ሲል ከነበረበት የልዩ ወረዳ አደረጃጀት  ወደ ዞን መዋቅር የማደግ ዕድል አግኝቷል፡፡ ከነሐሴ 2015ዓ.ም ጀምሮ የዞን መዋቅሩ ጸድቆ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ከዚህ አንጻር በአሁኑ ሰዓት ዞኑ በሶስት ወረዳዎች ማለትም የቶባ፣ የዳሪ ሳጃ ዙሪያ እና የፎፋ ወረዳ እንዲሁም የሳጃ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን ይዞ ተደራጅቷል፡፡ በዞኑ አራት የከተማ መዋቅር ቀበሌዎችና ሰላሳ ሶስት የገጠር ቀበሌያት በድምሩ ሰላሳ ሰባት ቀበሌዎችን ያቀፈ ነው፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ ለዘመናት ህዝቡ ሲጠይቅ የነበረው የዞን አደረጃጀት ምላሽ በማግኘቱ ከፍተኛ የሆነ ደስታና መነሳሳት ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ የተነሳ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የልማት ስራዎች ላይ አሻራውን እያሳረፈ ይገኛል፡፡

ንጋት፡- በዞኑ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሳሙኤል፡- ዞኑ ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሉበት ነው፡፡ ለአብነትም የቻሎ ባህላዊ ዳኝነት፣ የቦራ መድሃኒት ለቀማ እና ቅመማ ፣ የብርብርሳ ፏፏቴ፣ የወማ ፍል ውሃ፣ የመሳሰሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ዞኑ በሀገር በቀል እውቀትም ጭምር የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ የቦራ መድሃኒት ለቀማ በየአመቱ ጥቅምት 17 ይካሄዳል፡፡ ይህም የቱሪዝም ብቻ ሳይሆን ለዩኒቨርሲቲ ምሁራን የጥናትና ምርምር  ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ይህንን የቱሪዝም ሀብት ይበልጥ ለማጎልበት እራሱን የቻለ የባህል መድሃኒት ህክምና ማእከል ተገንብቶ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በቅርበት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህንንም በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሰፊ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም ከኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት እያደረግን እንገኛለን፡፡

በሌላ በኩል በዞኑ ያለውን እምቅ የግብርና ዘርፍ አቅም ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ለአብነትም የስንዴ መስኖ ልማት ስራ በ2016 የምርት ዘመን ወደ 400 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በአሁኑ ሰዓት ወደ 360 ሄክታር ማሳ ታርሶ ዝግጁ ሆኗል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ ተራራዎች ላይ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከል እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎችም በትኩረት የሚሰሩ ተግባራት ናቸው፡፡

ንጋት፡- ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ሳሙኤል፡- ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለአብነትም በ2016 በጀት አመት በ6 ወር እቅድ አፈጻጻም ወደ 930 ለሚደርሱ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በገጠር ወደ 70 ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት በጊዜያዊና ቋሚ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በከተማ ወደ 44 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው 57 ሄክታር መሬት እንዲያለሙ ተደርጓል፡፡

ንጋት፡- ልዩ ወረዳው ወደ ዞን እንዲያድግ የነበረው የህዝብ ፍላጎት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሳሙኤል፡- እውነት ለመናገር መዋቅር የህዝቡ ጥያቄ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የወጣቱ፣ የህዝቡ፣ የምሁራኑ ጥያቄ ያለምንም ግጭት ሰላማዊና በሰከነ መልኩ ምላሽ እንዲያገኝ ለአመታት ሲጠየቅ ቆይቷል። በትግል አመታት ምንም  የጸጥታ ችግር ሳይፈጠር ህገ-መንግስታዊ ሂደቱን ጠብቆ ሲካሄድ ነው የቆየው፡፡  ነባሩ የደቡብ ክልል ወደ ማዕከላዊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲከፈል የዞኑ የመዋቅር ጥያቄ አብሮ ምላሽ በማግኘቱ ህዝቡ ደስታውን በተለያዩ ሁነቶች ገልጿል፡፡

ንጋት፡- የመዋቅር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

አቶ ሳሙኤል፡- ትልቁ ፋይዳ ልማቱን የማሳለጥ ጉዳይ ነው፡፡ አደረጃጀት ልማትን የምናፋጥንበት ስልት ነው እንጂ ሌላ ግብ የለውም፡፡ ከወንድም እህት ህዝቦች ጋር በተለይም ከጠምባሮ፣ ከከምባታ፣ ከሀዲያ፣ ከጉራጌ እና ከስልጤ ህዝቦች ጋር በቅርበት በመገናኘት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ተቀናጅቶ ለመስራት እድል ይፈጥራል፡፡  የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የውሃ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ጉዳዮች ጭምር ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል መውጫ መንገዳችን ከጉራጌ ዞን ከወልቂጤ ከተማ ጋር ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀዲያ ዞን እና በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጭምር የመግቢያና የመውጫ በሮችን የምናሰፋበት የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ስራ ይሰራል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኝነቱ የበለጠ የተጠናከረ የሚሆንበት እድል ተፈጥሯል፡፡

ንጋት፡- በዞኑ ያለው የመሰረት ልማት ተደራሽነት ምን ይመስላል?

አቶ ሳሙኤል፡- ከመሰረተ ልማት አኳያ የህዝብ ጥያቄ ያለበትና በቀጣይ  መስራትን ይጠይቃል፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት በውስን መልኩ የተፈታ ቢሆንም በቀጣይ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ከሳጃ ፎፋ እና ግልገል ግቤ ቁጥር ሁለት  ሀይል ማመንጫ ድረስ የሚወስደው መንገድ አስፓልት እንዲሆን ህዝቡ በተደጋጋሚ ይጠይቃል፡፡ እንደሚታወቀው እዚያ ጋር ያለው ፕሮጄክት ሀገራዊ እንደመሆኑ መጠን ከባባድ መኪናዎች የሚያልፉበት በመሆኑ የአስፓልት መንገድ ጥያቄ በስፋት ይነሳል፡፡

ሁለተኛ ከጠምባሮ ልዩ ወረዳ እና ከከምባታ ዞን ጋር የሚያገናኝ በቶባ ወረዳ የሚያልፍ መንገድ ጉዳይ የዘመናት ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ሌላኛው ከውሃ ተደራሽነት ጋር ያለው ጉዳይ ሲሆን በዞኑ ያለው የህዝብ ብዛትና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ዞኑ የክልል ቢሮዎችም መቀመጫ እንደመሆኑ መጠን የውሃ ችግር አፋጣኝ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ በዞኑ ያለው የንጽህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት 45 መቶ ላይ ነው፡፡ የውሃ መሰረተ ልማት ጉዳይ በቀጣይ ትኩረት የሚፈልግ ሲሆን ይህም በክልል እና በፌደራል ደረጃ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ እንደሚፈልግ ያመላክታል፡፡

ከመብራት ተደራሽነት ጋር ያለው ችግር ሌላኛው ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በዞናችን ካሉ 37 ቀበሌዎች 19ኙ ቀበሌዎች መብራት አልባ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዞኑ ህዝብ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የሀይል ማመንጫ ጊቤ አንድና ሁለት የመብራት መስመር 26 ኪሎ ሜትር  የም ዞንን አቋርጦ ነው የሚያልፈው፡፡ ከዚህም የተነሳ ህዝቡ ስለ መብራት ተደራሽነት በተደጋጋሚ ጥያቄ ያነሳል፡፡ የተደራሽነት ችግር ብቻ ሳይሆን የመቆራረጥ ሁኔታዎችም ይስተዋላሉ፡፡

አዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እያደረገ ያለው የድጋፍና ክትትል ሁኔታ የሚበረታታ ሲሆን የፌዴራል መንግስትና አጋር ድርጅቶችም ድጋፋቸውን ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለ፡፡

ንጋት፡-  የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ሳሙኤል፡- ከማህበራዊ ሴክተሮች ተደራሽነት አንጻር የተሻለ ነገር አለ። የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት በተመለከተ አበረታች ሥራዎች ተሰርተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እስከ 50 በመቶ ማድረስ ተችሏል።  በሁሉም ወረዳዎች ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ማዳረስ የተቻለ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ በቀበሌ እስከ 3 ማድረስ ተችሏል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የትምህርት ግብአት የማሰባሰብ ተግባር በጥሩ አፈፃፀምነት ይጠቀሳል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጽሐፍትን ለማሳተም ሀብት ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ የትምህርት ተቋማትንም ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ ነው፡፡ ለአብነትም የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ፎፋ ወረዳ ላይ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመቀበል ግንባታ ተጠናቆ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ከጤና ተቋማት ተደራሽነት ረገድ በዞኑ 6 ጤና ጣቢያዎችና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አሉን፡፡ በሁሉም ቀበሌዎች ላይ የጤና ኬላዎች ተደራሽ ሆነዋል፡፡ በተለይ ከማአጤ /ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን/ ለማጠናከር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው። አዳዲስ አባላት የማፍራት ስራ 83 ከመቶ መድረስ ተችሏል፡፡ አጠቃላይ ምጣኔውን ስንመለከት 62 ከመቶ ደርሷል፡፡ የጤና ጉዳይ በዞኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተመራ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የሳጃ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ማደግ አለበት የሚል ጥያቄ ህዝቡ ያነሳል፡፡ ካለው የተገልጋይ ቁጥርና አገልግሎት አንጻር ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል የማደግ መስፈርቱን አሟልቷል፡፡ ለዚህም የክልሉ መንግስት ድጋፍ ማድረግ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፡- ዞኑን ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ከማድረግ አኳያ የተሰሩ ስራዎች ካሉ?

አቶ ሳሙኤል፡- ዞናችን ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ነው፡፡ ይህም የሚገለጸው ከሰላምና ጸጥታ አንጻር ያለው ምቹ ሁኔታ ነው፡፡ በአካባቢው ሰላም የህዝብ ቅቡልነት ካለ ለንግድና ለልማት አመቺ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከ10 በላይ ኢንቨስተሮች ወደ ኢንቨስትመት ገብተዋል፡፡ እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ትልቅ ፋይዳ አላቸው፡፡

ንጋት፡- በዞኑ ህብረ ብሄራዊነትን ከማስጠበቅ ረገድ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ሳሙኤል፡- የየም ብሔረሰብ ህብረ ብሄራዊ አመለካከትን በተግባር ያረጋገጠ ህዝብ ነው፡፡ ህብረ ብሔራዊነትን በመኖር የሚገልጽ ነው፡፡ ህብረ ብሔራዊነት የሚገለጸው የብሔረሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆን አጎራባች ዞኖችን ጨምሮ የሌሎች ክልል ተወላጆችም የሚኖሩበት ዞን ነው፡፡ ህዝቡ ትላንት የነበረውን አብሮነት ዛሬም እንዲቀጥል ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡  የሰላምና ጸጥታ ስራ በዞኑ ህዝባዊ መሰረት ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዞኑን የሰላም ቀጠና ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየን ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት ከኦሮሚያ፣ ከሀዲያ፣ ከጉራጌ እና ሌሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር ውይይት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ቀጠናዉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል በቀጣይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚተገበሩ ስራዎች የ100 ቀን ዕቅድ ወስጥ በማስገባት ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ የብዘሃነት ጉዳይ በዞኑ እንደ ሞዴልነት ሊወሰድ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፡- የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገልፃሉ?

አቶ ሳሙኤል፡-  የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማሳደግ አኳያ በእቅዳችን መሰረት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይ ሴቶች በአደረጃጀት እንዲጠናከሩ በማህበር፣ በሊግ፣ በፌደሬሽን ታቅፎ እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡ የሴቶች ልማት ጥምረት በየቀበሌዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገናል፡፡

ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡና ከፍተኛ የስራ ቦታዎች ላይም ጭምር የማሳተፍና ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡

በገጠር አካባቢ በማህበር ተደራጅተው በመስኖ ልማት ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ተግባራት ተከናውኗል፡፡ በከተሞች አካባቢ በከተማ ግብርና ላይም እንዲሳተፉ እና የዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ እንደ አጠቃላይ የሴቶችን ተጠቃሚነትንና ተሳትፎ ለማሳደግ በእቅድ የተደገፈ ሥራ እንዲሠራ  በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ንጋት፡- እንግዳችን በመሆን ስለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሳሙኤል፡-  እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡