የ28 ዓመታት ትዝታ እና ፈተናዎች
በገነት ደጉ
መንግስት የንባብ ባህል እንዲዳብርና የህትመት መገናኛ ብዙሀን እንዲጎለብቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ በቅርብ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መግለፃቸው ይታወሳል።
የሀገራችን የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ እድገት እያሳየ ሲሆን በተቃራኒው ፈር ቀዳጁ የህትመት ሚዲያ ማደግ ባለበት ልክ እያደገ አይደለም። ለዚህም የማንበብ ባህል መቀነስ፣ መረጃን በቀላሉ በዲጂታል አማራጮች ማግኘት መቻል እና የህትመት ዋጋ መናር የህትመት ሚዲያው እንዳያድግ ከሚጎትቱ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
የህትመት ሚዲያው ለማህበረሰባዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ያለውና የማንበብ ባህልን የሚፈልግ ዘርፍ ቢሆንም በሀገራችን ያለው የማንበብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መምጣቱ ግን የተፈለገውን ያህል ርቀት ሊወስደው አልቻለም፡፡
ለመሆኑ የህትመት ዘርፉ ለማህበረሰባዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ምንድነው? ዘርፉ ያሉበት ችግሮችስ ምንድናቸው? መሠራት ያለባቸው ተግባራትስ ምንድናቸው? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የቀድሞ የደቡብ ንጋት የዛሬዋ ንጋት ጋዜጣ ምስረታ ላይ ተሳትፎ ከነበራቸው ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የቀድሞ “የደቡብ ንጋት ጋዜጣ” የፕሬስ ቡድን መሪ የነበሩት እና አሁን በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አህመድ ሙክታር በቀድሞ ስያሜው “የደቡብ ንጋት” በሚል ስያሜ የሚታወቀውና የአሁኑ “ንጋት” ጋዜጣ፣ በክልሉ በጣም ተነባቢነት ያለው እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡
በወቅቱ ተሰሚነት እንዲኖረው ካደረጉት አበይት ጉዳች መካከል በቀድሞ ደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ብቸኛው ጋዜጣ መሆኑ፣ እንዲሁም ክልሉ እንደ ነጋሪት ጋዜጣ ሲጠቀመው መቆየቱ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
“ተነባቢ ካደረጋቸው ጉዳዮች አንዱ የይዘት እና ከዓምዶች በተጨማሪ ክልሉ ብቸኛ የመረጃ ምንጭ አድርጎት ስለሚጠቀም፣ እንዲሁም እንደ ነጋሪት ጋዜጣ በክልሉ የሚወጡ አዋጆች በንጋት ጋዜጣ ሽፋን ያገኙ ስለነበር ነው” ይላሉ፡፡
የጋዜጣው ዓምዶችም በክልሉ በሚወጡ አዋጆች ላይ ያተኮሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አህመድ፣ ከዚህም በተጨማሪ የአፋልጉኝ፣ የወራሽ እንዲሁም የሀራጅ ማስታወቂያዎች ሁሉ ስለሚካተቱ እና ሌሎችም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ይዳሰሱ ስለነበር በክልሉ ፍርድ ቤት ጭምር ትኩረት የተሰጠው ጋዜጣ እንደነበር ነው ያስረዱት፡፡
በወቅቱ ጋዜጣውን ሁሉም ሰው ያነበው እንደነበር የገለፁት አቶ አህመድ፣ በደቡብ ክልል የነበሩ 56 ብሔር ብሔረሰቦችም እሴታቸውን ለማጎልበት ይጠቀሙበት ነበር ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሰዎች ከማንበብ ይልቅ ማየት እና መስማትን ምርጫቸው ማድረጋቸውን፣ እንዲሁም በሰዎች ዘንድ የነበረው የንባብ ባህሉም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መሸርሸሩን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባመጣቸው ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም በመሳሰሉት ማህበራዊ የትስስር ገጾች መረጃዎችን በእጁ በያዛቸው ስልኮች ስለሚከታተል አሁን ላይ ለሰዎች የመረጃ ምንጭ በእጃቸው ነው ብሎ በድፍረት መናገር ያስችላልም ብለዋል፡፡
ጋዜጣ ገዝቶ የማንበብ ፍላጐት መቀነስ የንጋት ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሚገኙ የህትመት ሚዲያዎች ችግር መሆኑን ነው የጠቆሙት አቶ አህመድ፣ የህትመት ሚዲያዎችን እየተገዳደሩ ካሉት መሰረታዊ ነገሮች የህትመት ዋጋ ንረት ሲሆን ይህም የህትመት ወረቀት ውድ መሆን፣ የማተሚያ ቀለም /ኘሌት/ አለም አቀፍ የዋጋ ጭማሪና እንዲሁም ከስርጭት ጋር ተያይዞ ያሉ ማነቆዎች ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በወቅቱ የፕሬስ ቡድን መሪ ሆነው ሲያገለግሉ የስርጭት ስራው የሚሰራው ሌሎችንም ጋዜጦች ያሰራጭ በነበረው “ሜጋ” ማተሚያ ድርጅት በመሆኑ ውጤታማ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
የዚያን ጊዜም ቢሆን የስርጭት ጉዳይ ችግር የለም ማለት ግን እንዳይደለ የሚናገሩት አቶ አህመድ፣ ጋዜጣው ወደተፈለገበት ቦታ በወቅቱ አለመድረስ ችግሮች አልፎ አልፎ ይታዩ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
ሌሎች እንደነ በኩር ያሉ ጋዜጦች በጋዜጣ ማሰራጫ ሱቆች በዋና ዋና ከተሞች ይሸጡ የነበረ ሲሆን ጋዜጣውን የመሸጥ ኃላፊነትም ይጣልባቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
አቶ አህመድ ሙክታር ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ፡-
“በወቅቱ የንጋት ጋዜጣንም በክልሉ በተመሳሳይ መልኩ ማሰራጨት ነበር፡፡ ሆኖም ግን የተለያዩ ኃላፊዎች በተለዋወጡ ቁጥር ጉዳዩ እንደገና ጥሬ እየሆነ ቢመጣም ለእያንዳንዱ ዞን የጋዜጣው ሽያጭ ቦታ እንዲሰጥ ጠይቀን ፈቃደኝነታቸውን አሳውቀውን ነበር።
“አሁንም የንጋት ጋዜጣ የስርጭት አድማሱን ማስተካከል አለበት፡፡ አሁንም በጋዜጣው የሚወጡ የውርስ አዋጆች አሉ፡፡ ይህ ጥሩ ቢሆንም፣ ጋዜጣው የራሱን አቅም እንዳያሳድግ በርካታ ውስንነቶች አሉበት፡፡
“በተለይም ከዋጋ ተመን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ዛሬም ያልተፈቱ ሲሆን በሌሎች ጋዜጦች ውርስ የመሳሰሉ ጉዳችዮን ለማሳወጅ እስከ 6 ሺህ ብር የሚያስከፍሉበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በንጋት ጋዜጣ ግን ከ60 ብር እስከ 120 ብር ብቻ ነው። ይህም ከሌሎች የህትመት ሚዲያዎች አንፃር ሲነፃፀር አልተሰራበትም፡፡
“በተለይም አሁን ካለው ከገበያ ሁኔታ እና ከወረቀት ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ እንዲሁም ሌሎች የህትመት ሚዲያዎች ከደረሱበት ደረጃ አንፃር አነፃጽሮ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት የሚጎድሉት ስራዎች እንዳሉ መናገር ይቻላል፡፡
“ስለዚህ ጋዜጣውም በሁለት እግሩ መቆም የሚችለው የራሱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ሲችል ነው። በእርግጥ ማንኛውም ሚዲያ ድጎማ ሳይደረግለት በራሱ የሚንቀሳቀስ የለም፡፡ አሁን ላይ አብዛኞቹ ከድጎማ የወጡ ሲሆን በተለይም ከሚያስከፍለው ተመን፣ ከስርጭት እንዲሁም የማስታወቂያ ስራን በስፋት ካለመስራት ችግሮች በመውጣት የህትመት ሚዲያው ሙሉ የተቋሙን ወጪ መሸፈን በሚያስችለው ቁመና ላይ እስኪደርስ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም መስራት አለበት፡፡
“ጋዜጣው በ28 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በሚፈለገው ደረጃ እና ቁመና ላይ ደርሷል ማለት አይቻልም ሚዲያው አንጋፋ እና ቀደምት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሌላውኛው አስተያየት ሰጪ በጋዜጣው የተለያዩ ዓምዶች ይፅፍ የነበረው ጋዜጠኛ ሞላ ረጋሳ በበኩላቸው፣ ከጋዜጣ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ የሚታየው ውስንነትን በተመለከተ አብዛኞቹ የህትመት ውጤቶች ችግር ላይ ያሉበት ሁኔታ ስለመኖሩ ጠቅሰው፣ አሁን ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ በእጅ ስልኮች የተለያዩ መረጃዎች የሚገኙበት ጊዜ በመሆኑ ጋዜጣ እና መጽሔት ለማንበብ የሚገፋፋ ሰው ብዙም ያለ አይመስለኝም ብለዋል፡፡ ከዋጋም አኳያ ቢታሰብ በፊት ላይ አማራጮች ስላልነበሩ እና የማንበብ ፍላጎትም ስለነበረ የሰዎች ገዝቶ ማንበብ ልምዳቸው የተሻለ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አያይዞ ማብራሪያውን ሲቀጥል፡-
“በሚፈለገው ልክ እየተሰራ ነው የሚለው ግን በጥናት መደገፍ አለበት፡፡ ቀድሞ ደቡብ ክልል በነበረ ጊዜ አብዛኛው የሀራጅ፣ የፍርድ ቤት፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በደቡብ ንጋት ጋዜጣ ነበር የሚወጡት፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ገንዘብ አመንጪ ነበር፡፡
“ይህም ተቋሙን የሚደግፍበት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ከዋጋ ጋር በተገናኘ በፊት ይከፈል የነበረው ዋጋ ነው ዛሬም የቀጠለው፡፡ ይህም በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ አሁን ላይ ያለውን የዋጋ ንረት ታሳቢ ያደረገ አይደለም፡፡
ሌሎች ጋዜጦች በዚያ ልክ ነው ወይ የሚሰሩት? ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ፣ በዚያ ልክ አይመስለኝም፡፡ ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ እንዲሁም ሌሎችም ጋዜጦችን ለዓብነት አንስተን በተለይም ከማስታወቂያ አንፃር ማየት ይቻላል፡፡
“ብዙዎቹ ጋዜጦች ከገበያ እየወጡ ያሉበት ምክንያት የወረቀት ዋጋ መናር ስለሆነ ዋጋውን ከፍ በማድረግ ማካካስ ይገባል” በማለት አስተያየቱን ሰጥተዋል፡፡
በተለይም ጋዜጣው በሳምንት አንድ ጊዜ፣ ወይም በወር አራት ጊዜ ሲታተም በድረገፅ- ሚዲያው አልፎ አልፎ ነው የሚታየው እናም በቴሌቪዥን እና በሬድዮ አምዶችን ጨምሮ በስፋት ትኩረት ተሰጥቶት ስለ ጋዜጣዋ ቢተዋወቅ እና ቀሪውን ዘገባ በጋዜጣው እንደሚያገኙ ቢገለፅ የተሻለ ዕድል እንደሚኖረው አመልክቷል፡፡
More Stories
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን