በደረሰ አስፋው
በለጋ ዕድሜዋ ላጋጠማት አካል ጉዳት በባህላዊ እና በዘመናዊ ህክምና የመፈወስ ህልሟ ከንቱ ሆነ፡፡ ቤተሰቦቿ በህክምናዋ አለመሳካት ቢያዝኑም የፈጣሪ ቁጣ ነው ብለው በጓዳ ሸሽገው አላስቀመጧትም፡፡ የአካል ጉዳቷ ተምራ ያሰበችው ቦታ ለመድረስ አይገድባትም አሉ፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት እንድትገባ ፍላጎት አደረባቸው፡፡ በመንደራቸው በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት የኔታ ስር ቁጭ ብላ የፊደል ገበታን መቁጠር ጀመረች፡፡
የፊደል ቆጠራውን ጨርሳ ማንበብና መጻፍ ስትጀምር የመደበኛ ትምህርት ቤት ገባች፡፡ ሩቅ መንገድ እየተጓዘች ከ1ኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተማረች፡፡ ምቹ ባልሆነው የገጠሩ መንደር በዱላ እየተደገፈች በመጓዝ ትማር እንደነበርም ነው ያጫወተችን፡፡ ውጣ ውረድ በበዛበት የገጠሩ መንደር ባሳለፈችው የትምህርት ዘመን ጥንካሬን ያጎለበተችበት፣ አልሸነፍ ባይነትን የፈጠረችበት ጊዜ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ “ሰዎች ሊጥሉኝ ቢፈልጉም እኔ ግን አልወደኩላቸውም” በማለት ነው የገለጸችው፡፡
በአካባቢዋ ተምሮ ለመለወጥ የነበራትን ምኞት የሚፈትን ግን አልጠፋም፡፡ የትምህርት ቤቱ ርቀትና የመሰረተ ልማት ችግር ቀዳሚዎች ተግዳሮቶቿ እንደነበሩ በማስታወስ፡፡ በተለይ ክረምት በመጣ ጊዜ ፈተናው ያይል እንደነበር በመጠቆም፡፡ ይህ ችግርም ወደ አዲስ አበባ ለመሰደድ አነሳሳት፡፡ ከተማ የተሻለ ነገር የሚገኝበት፣ ለአካል ጉዳቷም መፍትሄ ይገኛል በሚል ለስደቱ ምክንያት እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡
ታምራለች ጌታቸው ትባላለች፡፡ የተወለደችው ጎጃም ሲሆን አሁን ላይ መኖሪያዋ አዲስ አበባ ነው፡፡ ላጋጠማት የአካል ጉዳት ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ለማሰራት ወደ አርባ ምንጭ የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል በመጣችበት ወቅት ነው ያገኘናት፡፡ በትውልድ አካባቢዋ እስከ 4ኛ ክፍል መማሯን ገልጻ አዲስ አበባ ደግሞ እስከ 10ኛ ክፍል ተምራለች፡፡
ከ10ኛ ክፍል በኋላ ግን ኑሮዋን የሚፈታተን ነገር አጋጠማት፡፡ እራስን ወደ መቻል ደረጃ መሸጋገር እንዳለባትም ተገነዘበች፡፡ ለዚህም ስራ ማፈላለጉን ተያያዘችው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የማስታወቂያ ቦርዶችን መቃኘትም የዘወትር ተግባሯ ሆነ፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀንም ምኞቷ ሰመረ፡፡ አንድ የጋርመንት ድርጅት ባወጣው ማስታወቂያ ተመዝግባ አለፈች፡፡
በሸሚዝ ማምረት ስራ ላይ የተሰማራ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ የመስራት ዕድሉ አጋጠማት፡፡ በቀኝ እግሯ ላይ የተከሰተው አካል ጉዳት በልጅነቷ ወድቃ የተከሰተ ቢሆንም አካል ጉዳቱ ከልጅነት እስከ እውቀት ያመጣባት ተጽእኖ እንደሌለ ነው የተናገረችው፡፡ ለዚህም ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ ያዳበረችው የመንፈስ ጥንካሬ እንዳገዛት በመግለጽ፡፡
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮየ አልተጎዳም። ህብረተሰቡ ውስጥ ያለው የግንዛቤ እጥረት እና የመሰረተ ልማት ችግር ተሸናፊ ሊያደርገኝ ቢዳዳም እኔ ግን ተሸናፊ አልሆንኩም፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ጥንካሬ ለዛሬው ማንነቴ ሀይልና ጉልበት ሆኖኛል፡፡ ሴትነትና አካል ጉዳት ለፈተና ቢዳርጉኝም እነዚህንም በጥበብ አልፌያቸዋለሁ”
በአካል ጉዳቷ ተጸጽታ እንደማታውቅ የተናገረችው ታምራለች ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ግን ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው አመለካከት የተለየ እንደሆነ ታነሳለች፡፡ የምትሰራውና የምትኖረው እንደ ጉዳት አልባው ሰው ቢሆንም ማህበረሰቡ ግን ልዩ እንደሆነ፣ እንደተረገመ ፍጡር አድርጎ እንደሚመለከት ነው ትዝብቷን የገለጸችው፡፡
“አካል ጉዳተኛ ሳይሆን አስተሳሰቡ ግን የተጎዳ ሰው አለ፡፡ አእምሮው ተጎድቶ እንደ አካል ጉዳተኛ የሚያስብ እንጂ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ሰርቶ እራሱን የለወጠ አካል ጉዳተኛ ሊባል አይገባም፡፡ አካል ጉዳተኞች አካላችን ቢጎዳም አእምሯችን አልተጎዳም፡፡ አካል ጉዳተኛ መሆን ሰርቶ ለመለወጥ የሚገድበው ነገር የለም፡፡ ይህ አስተሳሰብ እንዲለወጥም ተቀጥሬ በምሰራበት ቦታ በስራዬ ግንባር ቀደም ነኝ፡፡
“ምስጋና ይድረሰውና ለአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል” ያለችው ታምራለች ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ተደርጎላት እንደምትንቀሳቀስ ነው የተናገረችው፡፡ ወደ አርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ለሁለተኛ ጊዜ መምጣቷን ገልጻ በማዕከሉም ጥሩ አገልግሎት እያገኘች እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡ ከገጠሩ ወደ ከተማ መምጣቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳስገኘላት እና ይህም ቀድሞ የነበረውን ችግሯን እንዳቀለለላት ነው የተናገረችው፡፡
በምትሰራበት የጋርመንት ድርጅት የ5 ሺህ 500 ብር ደመወዝተኛ እንደሆነችና በዚሁ እንደምትተዳደር ነው የተናገረችው፡፡ ከዚህም ቤት ተከራይታ ነው የምትኖረው፡፡ ከዕለት ጉርስ እስከ ማህበራዊ ህይወት ያለውን መስተጋብሯን የምትሞላውም በዚሁ ደመወዝ ነው፡፡ በስራዋም ለሌሎች ሰራተኞች በምሳሌነት የምትጠቀስ ታታሪ ሰራተኛ መሆኗን ነው የተናገረችው፡፡ ይህ ተግባሯም እንደሚያኮራት በመግለጽ፡፡
“አካል ጉዳቴ ለመስራት ገድቦኝ አያውቅም። ቀጣሪዎቼም ቢሆን እንደ አካል ጉዳተኛ አይመለከቱኝም፡፡ የ8 ሰዓት ግዴታየን እወጣለው፡፡ የሚሠጠኝን ተግባር በጊዜው አከናውናለሁ፡፡ እንዲያውም ከጉዳት አልባው የተሻለ አፈጻጸም ነው ያለኝ፡፡ የሰዎችን አስተሳሰብ መለወጥ የሚቻለው እኔ በማሳየው ተግባር ነው፡፡ አካል ጉዳተኛ ማለት ተመጽዋች ሳይሆን ሰርቶ መኖር እንደሚችል ማሳየት ነው ፍላጎቴ”
አካል ጉዳተኞች መገንዘብ የሚገባቸው ጉዳይ እንዳለ የምትገልጸው ታምራለች አካል ጉዳተኛ ነኝ ብሎ እራስን ዝቅ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ አካላችን እንጂ አእምሯችን ባለመጎዳቱ ከልመና ይልቅ ሰርቶ መኖር አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ትመክራለች፡፡ ስራን ፈጥረው ለብዙዎች አርአያ የሆኑ በርካቶች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም በማለት፡፡
“አካል ጉዳተኛ ብሆንም የተለየ ስሜት ውስጥ ገብቼ አላውቅም፡፡ ጉዳቴን ተጠቅሜ በሌሎች ላይ ጫና ፈጥሬ አላውቅም፡፡ እራሴን ለመቻል ከመጣር ውጪ፡፡ የአካል ጉዳት አይነት ቢለያይም አእምሯቸውን ካሳመኑ የሚገድባቸው ነገር የለም፡፡ አስተሳሰባችን የተጎዳ ከሆነ ነው አካል ጉዳተኛ የምንሆነው፡፡ ማንም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚገድበን ነገር የለም”
ወደፊት ምን አቅደሻል? ብለን ላነሳንላት ጥያቄም ስትመልስ፡-
“ያሰብኳቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ሀሳቤ እውን እንዲሆንም በስራ የሚያምን ጠንካራ ማንነትን መፍጠር ይገባል፡፡ ታታሪዎች ያሰቡትን አውን ለማድረግ የሚገድባቸው እንደሌለ እረዳለሁ፡፡ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ከጉዳት አልባዎች ዝቅ ብዬ መታየትን አልፈልግም፡፡ ህይወትን መለወጥ የሚቻለው በመስራት እንደሆነ እምነቱ አለኝ፡፡ በምሰራበት ተቋም በርካታ ልምዶችን አካብቻለሁ፡፡ ይህ ለኔ ለወደፊት ህልሜ በር የሚከፍት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
“በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃው አለኝ፡፡ ይህ ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ሰርቶ እራሱን መለወጥ ካልቻለ ለሀገርም ቀውስ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞችንም ለከፋ ጉዳት ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ከመለመን ይልቅ ሰርቶ እራስን መለወጥ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች ላይ የቆየውን ዘርፈ ብዙ ችግር ማሸነፍ የሚቻለው በመስራት ብቻ በመሆኑ የልመናን አስተሳሰብ መለወጥ ይገባል” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ