በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ከወባ በሽታ ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚታየው የመድኃኒት ዕጥረት ሊፈታ እንደሚገባ የጤና ጣቢያ ተገለጋዮች ገለፁ
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት በበኩሉ የመድኃኒት ዕጥረት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በሸኮ ወረዳ በሸኮ ጤና ጣቢያ ካነጋገርናቸው ተገልጋዮች መካከል አቶ ሻንበል ዱዱንሳ፣ አቶ ሳምሶን ቶርሳ እና ወይዘሮ ፅዮን ዚና በሰጡት አስተያየት በተቋሙ በሚደረገው ምርመራ የወባ በሽታ ቢገኝባቸውም መድኃኒት ቢታዘዝላቸውም በህክምና ጣቢያው ማግኘት አልቻሉም፡፡
አብዛኛው ህብረተሰብ የጤና መድህን ተጠቃሚ ቢሆኑም ለአገልግሎት ሲመጡ በብዛት የወባ በሽታ እንደሚገኝባቸውና በተቋሙ ውስጥ የወባ በሽታ መድኃኒት የለም ተብሎ ወደ ውጭ ሲታዘዝ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ በመሆናቸው ዕጥረቱን መንግስት ሊፈታ እንደሚገባ ተገለጋዮቹ ጠይቀዋል።
በጤና ጣቢያው ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር ደረጀ ይረጋ እና የላብራቶሪ ክፍል ኃላፊ አቶ ታህሳስ እንዳለ በበኩላቸው በተቋሙ ከሚደረጉ የምርመራ ዓይነቶች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የወባ በሽታ ውጤት በመሆኑ የሁሉንም ትኩረት ይሻል ብለዋል።
በተለይም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን ታካሚዎች በሚታዘዘው መሰረት መውሰድ እንዳለባቸውና በመከላከያ ዘዴው ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።
የሸኮ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ካሳ በበኩላቸው ተቋሙ ለ38 ሺህ 965 የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና የወባ በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የመድኃኒት ዕጥረት እየታየ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመቀናጀት እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ጤናማና አምራች ዜጋን በማፍራት ረገድ በሚደረገው ርብርብ ፖሊሲውን መነሻ በማደረግ እየተሠራ ቢሆንም በአሁን ሰዓት ወቅታዊና ወረርሽኝ እየሆነ ያለው የወባ በሽታ በህብረተሰቡ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን የሸኮ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ተናግረዋል።
በወባ ወረርሽኝ በዓመት ከ5 እስከ 6 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚታመሙ ኃላፊው ገልፀው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታየውን የመድኃኒት ዕጥረት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በወረዳው ከሚገኙት ሶስቱም ጤና ጣቢያዎች በሸኮ፣ በኢተቃና በግዝመሬት ያለውን ውስን በጀት መድቦ መድኃኒት የመግዛት ሥራ እየተሰራ ቢሆንም ከበሽታው ስርጭት አኳያ መድኃኒት እንደማይቀመጥና ከሚገዛበት ማዕከልም ጭምር ያለመገኘትና የዋጋ መናር ተፅዕኖ መፍጠሩን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።
እንዲሁም በቅርቡ ግዝመሬት ጤና ጣቢያ ከ300 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ መድኃኒቶች መገዛታቸውን ኃላፊው አውስተው ከበሽታው ስርጭት አኳያ የወባ መድኃኒት ቶሎ በማለቁ ዕጥረት እየተሰተዋለ ነው ብለዋል።
የወባ በሽታ መድኃኒትና ሌሎችንም ዕጥረት ለመፍታት ከ12 ሺህ 740 በላይ የሚሆኑ አባወራና እማወራዎችን የጤና መድህን አባል በማድረግ በሚፈፀመው ቅድመ ክፍያ መድኃኒቶችን ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግም አቶ ዳንኤል ገልፀዋል።
የወባ በሽታን በመከላከል ረገድ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን መተግበር ከሁሉም ይጠበቃልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ