የሀገሪቱ ሁለንተናዊ አቅሞችን ተጠቅሞ ሃብት በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

የሀገሪቱ ሁለንተናዊ አቅሞችን ተጠቅሞ ሃብት በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ የካቲት 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገሪቱ ሁለንተናዊ አቅሞችን ተጠቅሞ ሃብት በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መሃመድ ኑሪዬ አስታውቀዋል።

በወልቂጤ ክላስተር ለሚገኙ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ሰራተኞች “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ቃል ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የመሰረተልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መሃመድ ኑሪዬ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት፤ የሃገሪቱ ሁለንተናዊ አቅሞችን በመጠቀም ሃብት በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል።

በኢኮኖሚ ያላደገ ሀገር ተወዳዳሪ አይሆንም ያሉት ሃላፊው አንደ ሃገር ብሎም እንደ ክልል የኢኮኖሚ ምንጭ የሚሆኑ እድሎች ያሉ በመሆኑ እነዚህን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

በስልጠናው ያሉንን የሃብት ምንጮች መጠቀም እንዲቻል የተመላከተበትና እንዴት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚቻል ወይይት ተደርጎ መግባባት መደረሱን አመላክተው ይህንኑ ሃብት ለማስተዳደር ሲቪል ሰርቪሱን በማጠናከር ጠንካራ ተቋም መገንባት እንደሚገባም አስረድተዋል ዶክተር መሃመድ ኑሪዬ።

ችግሮችን ተቋቁሞ ተግቶ በመስራት ሀብት መፍጠር እንዲሁም ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ከሲቪል ሰርቫንቱ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ለማሳለጥ አሰራርን ተከትሎ ከመከወን ባለፈ ውጤታማ ስራዎችን ሰርቶ ህዝብና መንግስት ያላቸውን ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማእድንና ኤነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሃይሉ ናቸው።

የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ከመገንዝብ ባለፈ ከብልሹ አሰራሮች ተላቆ በአገልጋይነት መንፈስ ተግባራትን መከወን ከሰራተኛው ይጠበቃል ያሉት ሃላፊው የፐብሊክ ሰርቫንቱን ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የሰልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሃገሪቱ ብዙ ሃብት ለመፍጠር የሚያስችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውና ነገር ግን አነዚህን ሃብቶች በወጉ መጠቀም አለመቻሉን ከስልጠናው መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ሲቪል ሰርቫንቱ ችግሮቹን ቀርፎ ለማህበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ መንግስትም አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ፐብሊክ ሰርቫንቱን መደገፍ ይኖርበታል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን