በሸኮ ወረዳ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል- የወረዳው አስተዳደር

በሸኮ ወረዳ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል- የወረዳው አስተዳደር

ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ወደ ሥራ መግባቱን የሸኮ ወረዳ አስተዳደር አስታወቋል።

የወረዳው ዋና አስተዳደር አቶ አሪ ጉረሙ ወረዳው ከዚህ ቀደም በነበረው በተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ሳይለማ መቆየቱን ገልጸው አሁን ላይ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናገረዋል።

በከተማው ዙሪያ 600 ኪሎ ሜትር መንገድ መከፈቱን የወረዳው ዋና አስተዳደሪው ገልፀዋል።

የከተማው ነዋሪው ጥገናና አዲስ የመንገድ ከፈታ ሥራ ሲከናወን የቡናና የባህር ዛፍ እንዲሁም የተለያዩ አታክልቶችን ያለምንም የካሳ ክፍያ ማንሳታቸው ለልማት ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያሳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ለወረዳው የልማት ሥራ ከ350 ሚሊዬን ብር በላይ በጀት ታቅዶ በህብረተሰቡ ድጋፍ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

“ደስታዬና ሀዘኔ የሚከበረው መንገድ ሲኖር ነው” በሚለው መሪ ቃል የሸኮ ከተማን መልሶ የማልማት ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ የወረዳው ምክትል አስተዳደሪና የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ኑራ ተናግረዋል።

የከተማውን ለማልማት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት 29 ኪሎ ሜትር የጥገናና 6 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአዲስ መንገድ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በወረዳው ከታቀዱ 6 ፕሮጀክቶችና በህብረተሰብ ተሳትፎ ከሚከናወኑ ልማቶች መካከል የከተማው ልማት አንዱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየዘርፉ የሚገኙት አካላት ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የሸኮ ወረዳ መልሶ ማልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታምራት ምናሴ ተናግረዋል።

ለልማቱ ከአንድ ቀበሌ እስከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እየተሰበሰበ ከመሆኑም ባለፈ እስካሁን ባለው ሂደት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መደረጉን የኮሚቴ ሰብሳቢው አውስተው ለልማቱ የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

የከተማው ነዋሪዎች የተጀመረው ልማት እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ- ከሚዛን ጣቢያችን