በግብርናው ዘርፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በግብርናው ዘርፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታውቋል።
ማዕከሉ ከቅመማቅመም ሰብሎች ምርምር ጎንለጎን የሸኮ ዳልጋ ከብት ዝርያ መጠበቅና ማባዛት ላይ እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።
የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ሺፈራው ተምትሜ እንደገለጹት፤ የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በሰብል በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ዘርፍ ብዙ ምርምሮችን በማካሄድ ቴክኖሎጂውን ለአርሶ አደሩ እያደረሰ ይገኛል።
የምርምር ማዕከሉ ይህንን ተግባር ላለፉት አርባ አመታት እያከናወነ መቆየቱን አቶ ሺፈራው ጠቁመው ልዩ የሚያደርገው በሀገር ደረጃ ቅመማ ቅመም ሰብሎች ላይ የሚካሄደውን ምርምር በበላይነት የሚያስተባብር መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም ቁንዶ በርበሬ የተባለውን የቅመም ሰብል ከውጪ ሀገር በማስገባት ምርምር በማካሄድ ለአርሶ አደሩ እያዳረሰ መቆየቱን አብራርተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታትም በተካሄደው ምርምር ከደቡብ ምዕራብ የተገኙት ሁለት የኮረሪማ ዝርያዎችን ቤንች ማጂ ዋን እና ካፋ ዋን የሚል ሲያሜ በመስጠት አውጥተናል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አፈር በአብዛኛው አልሙኒየም በተባለ አሲድ የተጠቃ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሩ አፈርን በኖራ አክሞ እንዲጠቀምና አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ ሰብል ዝርያዎችን እንዲጠቀም በምርምር ማዕከሉ የማስተዋወቅ ስራም እየተሰራ እንዳለም ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በወተት ምርትና በሽታን በመቋቋም የሚታወቀውን የሸኮ ዳልጋ ከብት ዝርያን የመጠበቅና የማባዛት ተግባርም እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለሚገኙት አምስት ወረዳዎች ላይ 23 ኮርማዎችን በመላክ 70 ጥጆች እንዲወለዱ መደረጉን አቶ ሺፈራው አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
የአርባምንጭ ከተማ ሰላማዊና በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገለች መሆኗ ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ያደርጋታል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ
የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ
መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑ ተገለጸ