በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ውጤት ማምጣታቸው ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የቦሮቦር መከላከያና የጋቦን ሽቦዎችን በመጠቀም፥ የመሬት መጎዳትን ለመከላከል በተሠራው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባላቸው ሥነ-አካላዊ እና ሥነ-ህይወታዊ ስራዎች ለአርሶ አደሩ የገቢ አማራጭ መሆናቸው ተመልክቷል።
በሀላባ ዞን ዌራዲጆ ወረዳ የተከናወነው የአከባቢ ጥበቃና የስነ-ህይወታዊ ስራ ለሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች ጥሩ አብነት እንደሚሆን የተናገሩት፥ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው።
ተፈጥሮን የሰው ልጅ ከጠበቃትና ከተንከባከባት መልሳ የምትከፍልና ጸጋን የምታላብስ መሆኗን የጠቆሙት ኃላፊው፥ ተፈጥሮን መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ማልማትና መጠቀም የሰው ልጆች ኃላፊነት መሆኑን አውስተዋል።
የተተከሉ ዛፎች ለአፈር ለምነትና ለእንስሳት መኖነት ጠቀሜታ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ፥ የአርሶአደሩን የገቢ አቅም ማሳደጊያ አማራጭ በማስፋት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራችንን በውጤት ማጀብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የግሪን ክላይሜት ፈንድ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሁሴን ኑረዲን በበኩላቸው፥ በ120 ሄክታር መሬት ላይ የተሠራውን የሥነ-አካላዊ እና ሥነ-ህይወታዊ ስራ በዝቅተኛ ተፋሰስ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
የተረጋጋ መሬትና ምርታማነቱ የማይቀነስ የተረጋጋ እርሻ በታችኛው ተፋሰስ ላይ መፍጠር መቻላቸውን የሚናገሩት አቶ ሁሴን፥ በዌራዲጆ ወረዳ ወጤጣ ቀበሌ የተሠራው የአከባቢ ጥበቃ ስራ ወደ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ልቀትን መምጠጥ የሚችሉ የደን ዝርያዎችን የያዘ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በሚሸፍናቸው ዞኖችና ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ የአከባቢ ጥበቃ ስራ ተስፋፍቶ መቀጠሉን ጠቁመው፥ እስካሁን 704 ሄክታር መሬት እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ