በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በዓሣ እርባታ የተሰማሩ ዓሣ አርቢዎች አሁን ከሚያገኙት ጥቅም በበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በዓሣ እርባታ የተሰማሩ ዓሣ አርቢዎች አሁን ከሚያገኙት ጥቅም በበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በዓሣ እርባታ የተሰማሩ ዓሣ አርቢዎች አሁን ከሚያገኙት ጥቅም በበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የከተማው አስተዳደር በበኩሉ የዓሣ ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ተጠቃሚነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው ብሏል።

ወጣት መሠረት በየነ በከተማው ሕብረት ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ኩሬ በማዘጋጀት ዓሣ በማርባት ጫጩትና የደረሱትን ለምግብነት በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ከጀመረ ሶስት ዓመት ሆኖታል።

አሁን ባለው ኩሬ ላይ ከሶስት ሺህ በላይ ዓሣ እንደሚያገኝ የሚናገረው ወጣት መሠረት ሌላ ኩሬ ለመጨመር ከ15 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማውጣት ቢቆፍርም ጫጩቶችን ጨምሮ ለማርባት ኖራ እና የውሃ ማስተላለፊያ ፕላስቲክ ቱቦ በማጣቱ ጉድጓዱ ክፍት ሆኖ ይገኛል ብሏል።

ሌላው ዓሣ አርቢ አቶ ንጉሴ ሳፕምቴት እነሱ በሚኖሩበት መንደር ከአምስት በላይ ዓሣ አርቢዎች እንዳሉ ገልጾ ለምግብነት የደረሱ ዓሣዎችን አውጥቶ ለመሸጥ በዓሣ መረብ ማጣት ምክንያት ትልልቆቹ ዓሦች ጫጩቶችን እየተመገቡ ነው ብለዋል።

በከተማ አስተዳደር የግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ ጽ/ቤት የእንስሳት ልማት ዘርፍ ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ወይንሸት ብርሃኔ ዓሣ አርቢዎች የሚያነሱትን የዓሣ ማጥመጃ መረብ ለመግዛት በጀት የተያዘ ሲሆን ግዥ ሲፈጸም ለዓሣ አርቢዎች እናደርሳለን ብለዋል።

የጽ/ቤቱ ሀላፊ አቶ ምስራቅ አስናቀ በበኩላቸው 48 ያህል የለማ የዓሣ ኩሬ በከተማው አስተዳደር እንደሚገኝ ገልጸው አብዛኞቹ ኩሬዎች አዲስ ቢሆኑም ምርታማነቱ እንዲጨምርና አርቢዎች ከቤት ፍጆታ አልፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ከንቲባው ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም በበኩላቸው በከተማው በትኩረት ከሚከናወነው የከተማ ግብርና መካከል አንዱ የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው ዓሣ አርቢዎች ምርታቸውን አቅርበው ለከተማው ማህበረሰብ የሚሸጡበትን ቦታ ለይቶ ለመስጠት ስለታቀደ እናመቻቻለን ብለዋል።

አሁን በከተማው በማህበራትና በግለሰብ ደረጃ እየተመረተ ያለውን ዓሣ ባለሀብቶችም ተሳትፈውበት ምርቱ ከተማ ላይ በበቂ እንዲቀርብ ለማስቻል ቦታ ተመቻችቶ እየተሰጣቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ መምሪያ የእንስሳት ዓሣ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ባይከዳ ሽሩዋብ በዞኑ በቁጥር 210 የለማ የዓሣ ኩሬ መኖሩን ተናግረው በዚህ ዓመት 76 ኩሬ ለመጨመር ታቅዶ እስካሁን 41 ኩሬ መጨመሩን አብራርተዋል።

በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ስድስት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ዓሣ በኩሬ የማርባት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ባይከዳ ተናግረው ዓሣ ከ5 ወር እስከ 7 ወር ባሉት ወራት ለምግብነት የሚደርስና እንደ ሀገር የተያዘውን የሌማት ትሩፋት ለማሳካት ሚናው የጎላ ስለሆነ ባለድርሻ አካላት አርሶ አደሩን በተገቢው እንዲደግፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን