ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚሆንበት ከድንኬ-ሣውላ- ሸፊቴ እና ቱርጋ -ያላ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በይፋ ተጀመረ
ሀዋሳ: የካቲት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚሆንበት 85 ነጥብ 68 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ከድንኬ-ሣውላ- ሸፊቴ እና ቱርጋ -ያላ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በይፋ ተጀምሯል::
የመንዱ ግንባታ ቀደም ሲል ተጀምሮ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተጏትቶ ቆይቷል:: አሁን ላይ ከመጀመሪያው ተቋራጭ ጋር የነበረው ውል ተቋርጦ ለአዲስ ተቋራጭ መሰጠቱ ተገልጿል::
በመንገዱ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር አክሊሉ አዳኝ “መንገድ የኢኮኖሚ ደምስር ነው፤ ያለ መንገድ ሌሎች ልማቶች አይታሰቡም” ብለዋል::
የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ወደ አካባቢው የሚገቡበት መንገድ በመሆኑ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል::
የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታው 24 ሰዓት ሊያሰራ የሚችል በመሆኑ በተሰጠው የሶስት አመት ጊዜ ውስጥ መንገዱን እንዲያጠናቅቅ ለተቋራጩ ጥሪ ያቀረቡት ኢንጅነር አክሊሉ ህብረተሰቡም ከኮንትራክተሩ ጎን በመሆን የድርሻውን እንዲያበረክት አሳስበዋል::
የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት::
የኢትዮጵያ መንዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድ አብዱራህማን የመንገዱን የግንባታ ሂደት ቀድመን ለመጀመር አስበን የነበረ ቢሆንም ከአበዳሪ ተቋማት ጋር የነበረው ሂደት መዘግየት አስከትሏል ብለዋል::
መንገዱ በመዘግየቱ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ይገባል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከእንግዲህ የመገድ ሥራውን በቅርበት እየተከታተልን በፍጥነት ለመገንባት አቅም ፈጥረን እንንቀሳቀሳለን ሲሉ ተናግረዋል::
ከድንኬ-ሣውላ- ሸፊቴ እና ቱርጋ -ያላ የሚገነባው የአስፓልት መንገድ 85 ነጥብ 68 ኪ.ሜ እርዝማኔ ያለው ሲሆን ቀደም ሲል ግማሹ የመንገድ ክፍል የተጠናቀቀ ነው::
የመንገዱ መጓተት በድክመት የሚታይ ቢሆንም በአዲስ መልክ ሥራው ሲጀመር ከቱርጋ እስከ ያላ ያለው የ9 ነጥብ 5 ኪ.ሜ መንገድ አዲስ የፕሮጀክቱ አካል እንዲሆን መደረጉ በበጎ ጎን የሚወሰድ ነው ብለዋል::
በመንገድ ፕሮጀክቱ 12 ድልድዮች እንደሚገነቡም ተናግረዋል
በቀጣይ ሶስት አመታት ውስጥ የመንገድ ግንባታው ህዝብን የሚያስደስት እንዲሆን ተደርጎ እንዲሰራ ድጋፍና ክትትላችን የተጠናከረ ይሆናል: ህብረተሰብ ሊያግዘን ይገባል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል::
ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ቋሚና ጊዜያዊ ሀብት ሊነካ የሚችል ቢሆንም መንገዱ ሊያመጣ የሚችለውን ጥቅም በአግባቡ በመገንዘብ ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ናቸው::
መንግስት የፕሮጀክት ፅህፈት ቤቶችን በቅርበት የከፈተ በመሆኑ ፕሮጀክቱን በቅርበት ለመከታተል እድል የሚሰጥ መሆኑንም ገልፀዋል::
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ በበኩላቸው ለፕሮጀክቱ የኮንትራት ውል የማዛወር እና በጀት የመመደብ ሥራ ላከናወነው የፌዴራል መንግስት ምስጋና አቅርበዋል::
የማዜ ብሔራዊ ፓርክ የቱሪስት መዳረሻ በመሆኑ የፍጥነት መቀነሻ ብሬከር በፓርኩ አካባቢ ቢሰራ የተሻለ እንደሚሆንም ተናግረዋል::
የመንገድ ፕሮጀክቱን የተረከበው ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሊ መንገዱን በጊዜ እና በጥራት ማጠናቀቅ ነው ዋና አላማችን ስትል ተናግራለች::
ከመንግስት ከሚሰጠን ድጋፍ በተጨማሪ የአካባቢው ህዝብና አስተዳደር ድጋፍም እንደሚያስፈል ገልፃለች::
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በህገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩና ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ
በጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ
የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ሊውል እንደሚገባ ተገለጸ