የቀሰም ወግ

የቀሰም ወግ

በአለምሸት ግርማ

የህይወት የስኬት ማማ ላይ ለመድረስ አሊያም ሌሎችን ለመርዳት በሚሰንቁት ዓላማ ሰዎች ራዕያቸውን ዕውን ያደርጋሉ። ያሰቡትን ለማሳካትም ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠይቃል። በተለይም የፈጠራ ስራ ፍላጎትን የሚጠይቅ በመሆኑ ትዕግስትን፣ ትኩረትንና ጊዜን ይፈልጋል። የስራ ፈጠራ ባለቤት መሆን አድካሚ ቢሆንም ከራስ አልፎ ለሌሎች የስራ ዕድልን ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት። ተስፋ ሳይቆርጡ ጠንክረው የሰሩ ያሰቡበት እንደሚደርሱ ይታመናል። ከእነዚህ ጠንካራ ሰዎች መካከል የዛሬዋ እቱ መለኛችን አንዷ ናት። ስለስራው አጀማመር፣ አሁን ያለችበትን ሁኔታና ስለቀጣይ ዓላማዋ ያወጋችንን እናካፍላችሁ፦

ዲዛይነር ራህማ ኑር ትባላለች። ትውልድና ዕድገቷ አዲስ አበባ ከተማ ነው። መደበኛ ትምህርቷን ጨርሳ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም እስከ ደረጃ አራት ድረስ በዲዛይን ሙያ ስልጠና ወስዳለች። በአሁኑ ወቅትም የዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ተቃርባለች።

ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ስለምትሰማራበት ስራ ስታስብ ብዙ አማራጮችን አየች። ከሰዎችም ጋር ተማከረች። በሙያዋም በሆነ ድርጅት ውስጥ መቀጠር ቀላል ቢሆንም የውስጧ ፍላጎት ያን ሊያረካው ግን አልቻለም። ይልቁንም ከእህቷ ጋር በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያዩ በኋላ በአንድ ሃሳብ ተስማሙ። ሃሳባቸው የልብስ ዲዛይንና ስፌት ማሰልጠኛ መክፈት ነበር።

እንዳሰበችውም አሳካችው። ከእህቷ ጋር በመተጋገዝ ማሰልጠኛውን በሃዋሳ ከተማ መክፈት ቻለች። የዚህ ስራ ዋና ዓላማ በቀላል ገንዘብ ሰዎች(በተለይም ሴቶች) የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ እና የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው። ዲዛይነር ራህማ እንዳለችው ሴቶች በትንሽ ካፒታል የሙያና የስራ ባለቤት የሚሆኑበትን አማራጭ ስንመርጥ ብዙዎችን ይዘን አብረን ለመጓዝ በማሰብ ነው። በተመጣጣኝ ክፍያ የሙያ ባለቤት ሲሆኑ የስራ አጥነትን ከመቅረፍ ባሻገር ባለሙያን በማፍራት የራስ አሻራን ማሳረፍ እንደሚቻል ነው። ይህም በግል ተቀጥሮ ደመወዝ አግኝቶ ከመኖር ይልቅ የህሊና እርካታን ይሰጣል። በተጨማሪም ስራው ሲስፋፋ ለብዙዎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አልፎ አርኣያ ለመሆን ያስችላል።

ስልጠናው ምን ምን ሙያን ያካትታል ብለን ላነሳንላት ጥያቄ እንዲህ በማለት መልሳለች፦

በማሰልጠኛው የሶስት ወራትና የስድስት ወራት ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ስልጠናውን መውሰድ የሚችሉት ከ12 ዓመት ዕድሜ በላይ ያሉ፤ መረዳት የሚችሉ ሴቶችም ወንዶችም ሲሆኑ ስልጠናው የሚሰጠው በተመጣጣኝ ዋጋ ነው። በሌሎች ማሰልጠኛዎች ከወራዊ ክፍያ በተጨማሪ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ወጪ የሚሸፈነው በራሳቸው በሰልጣኞቹ ነው። እዚህ ግን ወረቀትና ጨርቅ ብቻ ነው ሰልጣኞች የሚገዙት። እሱንም በተቋሙ የሽያጭ አገልግሎት አቅርበናል።

በሙያው ተሰማርታ ሌሎችን ባለሙያ ለማድረግ ካላት ፍላጎት የመነጨው ስራ ዛሬ ላይ እሷና እህቷን ጨምሮ ለአምስት ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል። ለሌሎች ደግሞ የሙያ መቅሰሚያ ማዕድ ሆኗል። በዚህም መሰረት ብዙዎች እየሰለጠኑና የሙያ ባለቤት እየሆኑ ይገኛሉ።

የማሰልጠኛ ስራውን ከጀመሩ አንድ አመት ከሶስት ወራት መሆኑን ዲዛይነር ራህማ ያጫወተችን ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት የገጠሙ ተግዳሮቶች ካሉ ብለን ጠይቀናት እንዲህ በማለት ነበር የመለሰችልን፦

“በስራው የገጠመን ትልቁ ችግር የግንዛቤ ውስንነት ነው። ይህም ስራችንን በምንፈልገው ልክ እንዳናስኬድ እንቅፋት ሆኖብናል። በእርግጥ ስራችንን ስንጀምር ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች የማስተዋወቅ ስራ ሰርተናል። ይሁን እንጂ ሰዎች ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም። ይህም ስለሙያው የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን እንድንረዳ አድርጎናል።”

በእርግጥ በሀገራችን የዲዛይኒንግ ሙያ አሁን አሁን እየተሻሻለ ቢመጣም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ ብዙዎች በመስኩ ለመሰማራት አይደፍሩም።

ልክ እንደ“ቀሰም የፋሽን ዲዛይን ማሰልጠኛ” ተቋም በመስኩ ለተሰማሩ ብዙ መሰናክሎች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ ሊገነዘቡ ይገባል። ማንኛውም ስራ ሲሰራ መሰናክሎች ሊገጥሙ ይችላሉ። ነገር ግን ችግሮቹን አይቶ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ከችግሩ እንዴት መውጣት ይቻላል የሚለው ላይ ማተኮር ተገቢ ነው።

ዲዛይነር ራህማ እንዳጫወተችን ስራውን ሲጀምሩ ይመጣል ብለው ያሰቡትን ያህል የሰው ቁጥር አልመጣላቸውም። ይሁን እንጂ ችግሮቹን አይተው ከዓላማቸው አልተገደቡም። ይልቁንም ከችግር የሚወጡበትንና ስራቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገድ እየቀየሱ ይገኛሉ።

ለዚህም አጋዥ ይሆናል በማለት ያሰቡት ከስራቸውም ጋር ግንኙነት ያለው የጋርመንት ስራ ለመጀመር በሒደት ላይ ናቸው። አያይዘው በማሰልጠኛው ለሚሰለጥኑ ሰልጣኞች በጋርመንቱ የስራ ዕድል ለማመቻቸትም ማቀዳቸውንም አጫውተውናል።

ይህም ይበል የሚያሰኝና ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው። ተያይዞ መጓዝ ከእኔነት አልፎ የእኛነት ስሜትን ይፈጥራል። ከራስ አልፎ ለሌላው ማሰብ ሰዋዊ ባህሪ መሆኑን ያሳያል።

ማሰልጠኛው የልብስ ስፌት፣ ስኬች፣ ፓተርን፣ ቦርሳ፣ የሀበሻ ልብስ የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ያሰልጥናል። ለዚህም በሙያው ብቃት ባላቸው ሰዎች ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፃልናለች።

በቀጣይ ዕቅድሽ ምንድነው ስንል ላነሳንላት ጥያቄ በምላሽዋ፦

በቀጣይ ቁጥር 2 ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነን። እንዲሁም ለመከፈት በሂደት ላይ ያለው ጋርመንት ወደ ስራ ሲገባ ለብዙዎች የስራ ዕድል መፍጠር ነው። ሌላኛው ደግሞ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ አዛውንቶች የፈትልና የሽመና ሙያ በማሰልጠን ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በዚህም መስራት የሚችሉ ሰዎች ወደ ስራ እንዲሰማሩ ማድረግ እንዲሁም ከጥገኝነት ተላቀው በራሳቸው ሰርተው መኖር እንዲችሉ ማድረግ ነው ብላለች።

ከዚህ ቀደም በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በጋራ ስልጠና የምንሰጥ ሲሆን ሌሎችም በዚህ መልኩ አገልግሎት የሚፈልጉ ካሉ አብረን መስራት እንፈልጋለን።

እስካሁንም ያሰለጠኗቸውን ባለሙያዎች ከተለያዩ ጋርመንቶች በሚቀርብላቸው ጥያቄ መሰረት ወደ ስራ እያሰማሩ ይገኛሉ።

በስራ ዓለም ውስጥ መውደቅ መነሳት የሚያጋጥም እንደሆነ የብዙዎች ህይወት ይመሰክራል። የተለያዩ ፈተናዎችን መጋፈጥም ወደስኬት የሚያንደረድሩ ጎዳናዎች ናቸው። በንግድ ስራ ውስጥ ችግር ሲያጋጥም ወደኋላ መመለስ ስኬታማ መሆን አያስችልም። ይልቁንም ከችግሩ የሚወጣበትን መንገድ እንዲሁም የተሻለ ውጤት የሚያገኝበትን መንገድ በመዘየድ ውጤታማ ለመሆን የሚያልም ሰው ስኬታማ መሆን ይችላል።

ሌሎች ሴቶችም እንዲሁ እንዲሆኑ ነው የምፈልገው። በማንም ላይ ጥገኛ መሆን የለባቸውም። ጠንክረው ከሰሩ ፍላጎታቸውን አሟልተው መኖር ይችላሉ። የዕረፍት ቀናትን ጨምሮ በተዘጋጀው የስልጠና መርሃ ግብር በመጠቀም ራሳቸውን የሙያ ባለቤት ማድረግ ይችላሉ ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።