የግብርናውን ሥራ ለማዘመን
በደረጀ ጥላሁን
የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲሻሻል በግብአት አቅርቦት ረገድ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ግብርናውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየሰሩ ከሚገኙ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች አንዱ የሆነውንና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን የሚገኘውን መሊቅ ዩኒየን የሥራ እንቅስቃሴ እንቃኛለን፡፡
መሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን በ1996 ዓ/ም በ13 ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት የተደራጁ 3 ሺህ 101 አባላትን በማቀፍ በ 65 ሺህ ብር ካፒታል ነበር የተመሰረተው፡፡ ዩኒየኑ አሁን ላይ ከ13 ወደ 86 ህብረት ሥራ ማህበራት ሲያድግ አባላትን ወደ 99 ሺህ 559 ማድረስ ችሏል፡፡ ካፒታሉም ከ 82 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ዩኒየኑ በተሰማራባቸው የሥራ መስኮች ለ 51 ቋሚ እና 157 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
መሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ገግሰቦ ረዲ ዩኒየኑ የተሻሻሉና የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን እና አገልግሎቶችን ለአባል ማህበራት በማቅረብ አባል የህብረት ስራ ማህበራቱ ለብቻቸው ሊፈቱት ያልቻሏቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመፍታት ተልእኮ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ይላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ለአርሶ አደሩ ምርት የተሻለ ገበያ አፈላልጎ በመሸጥ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡ አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብአቶች የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ኬሚካል፣ የጓሮ አትክልት ዘሮችና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን በማቅረብም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የመደገፍ ሥራ ይሰራል።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ የማህበራት ትልቁ ችግር የገንዘብ በመሆኑ ዩኒየኑ ያለምንም ወለድ የብድር አቅርቦት የሚያቀርብ ሲሆን ባለፈው አመት ከ 25 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ 50 ለሚሆኑ ማህበራት ማበደሩን ነው የገለጹት፡፡
ዩኒየኑ የመኖ ማቀነባበሪያን ፋብሪካ ጨምሮ ሁለት ወፍጮ እና ሁለት የስንዴ ማበጠሪያዎች በመጠቀም እሴቶች ይጨምራል፡፡ ስድስት አይነት መኖዎችን በማምረት ለተጠቃሚውና ለአርሶ አደሩ ያደርሳል፡፡ በ2015 ዓ/ም 15 ሺህ 411 ኩንታል የተለያዩ መኖዎች በማምረት ለተጠቃሚዎቹ ማድረስ ችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ሥራው ተመጋጋቢነት ስላለው የእንስሳት ሀብት ልማቱ እድገት እንደሚፋጠንም ገልጸዋል፡፡
ዩኒየኑ ዓላማው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት ስለሆነ የዋጋ ሁኔታው እንዳይዋዥቅ ይሰራል፡፡ በዚህ መሠረት ለወራቤ ዩኒቨርስቲ በ2015 ዓ/ም 4 ሺህ 345 ኩንታል የጤፍ ዱቄትና 2 መቶ ኩንታል ሽሮ ቀርቧል፡፡ ከዚህ ሌላ ለ‹‹አይረንዚ›› አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር፣ ለወራቤ ማረሚያ ተቋም፣ ለፋብሪካዎችና ለሌሎች ድርጅቶችም የማቅረብ ሥራ ተሰርቷል። በተጨማሪም የፍጆታ እቃ በተለይ ዘይትና ስኳር ከክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በተሰጠ ውክልና መሰረት በ2015 ዓ/ም ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይትና 1ሺህ 561 ኩንታል ስኳር ማቅረብ ተችሏል፡፡
የሜካናይዜሽን አገልግሎት የግብርናው ሥራ የሚዘምንበት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ደቡብ ማእከል ጋር በመተባበር እየሰራ ነው፡፡ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሠረት የሚሆን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዩኒየኑ ሶስት ኮምባይነር እና፣ ሁለት ትራክተር ያለው ሲሆን የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖች፣ ጋሪዎችንም ለሚካናይዜሽን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ለማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚያገለግል ለሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚውል የማእከል ግንባታ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ደቡብ ማእከል ጋር እያከናወነ ሲሆን ግንባታው ተጠናቆ ለሥራ ዝግጁ ሆኗል። ዓላማውም የሜካናይዜሽን ዘርፍ ችግር የሆነው የመለዋወጫ እቃዎች እጥረትን ለመፍታት ይረዳል፡፡ በዚህም የጥገና አገልግሎት መስጠት፣ ማሽነሪዎች ሲበላሹ ወደ ሌላ አካባቢ ሳይኬድ እዚሁ መስራት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል የማብቃት ሥራ መስራትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት በስፋት መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ማሽኖኞችን የሚያንቀሳቅስ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ስለሚስተዋል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ደቡብ ማእከል በስልጠና እያገዘ ይገኛል፡፡ ከዚህ ሌላ የዞኑ መንግስትም መሬት በማቅረብ፣ በገንዘብ እና የህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ዩኒየኑን እንደሚያግዙ አቶ ገግሰቦ ተናግረዋል፡፡
ዩኒየኑ በንብረትና ሂሳብ አያያዝ፣ የፋይናንስ አጠቃቀም እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለማህበራት አባል አርሶ አደሮችና አመራሮች የአቅም ግንባታና የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚረዱ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥም ተመልክቷል፡፡
የኒየኑ ለጊዜው ባሉት ሁለት ኤፍ.ኤስ.አር መኪኖች ከማህበራት ምርት የማመላለስ ስራ የሚሰራ ሲሆን ክፍተት ያለባቸው ጣቢያዎች ላይም የአፈር ማዳበሪያ የማድረስ ስራ ይሰራል። በአንድ የምርት ዘመን ብቻ ለትራንስፖርት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ስለሚወጣ ይህንን ለማሰቀረት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ሁለት ተሳቢ መኪኖች ከባንክ በተደረገ የብድር ስምምነት በቅርቡ ስለሚገቡ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ለዚህም ዪኒየኑ የድርሻውን 7 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ቅድመ ክፍያ መፈጸሙንም ጠቁመዋል፡፡
የሰብል ዋጋ መቀያየር፣ ህገ ወጥ ንግድና የደላሎች ከቁጥጥር በላይ መሆን፣ የፋይናንስ ችግር ፈጥኖ ከማመቻቸት አንጻር ከፍተኛ ውስንነት ነበረበ፡፡ ይህም የምርት መቀነስ በተለይ የበቆሎ ምርት፣ የምርት ጥራት ችግር፣ ቅንጅታዊ ስራዎች መዳከም፣ ስንዴን አስመልክቶ ከላይ የወረደው ዋጋ ዩኒየኖችን ከገበያ እንዲወጡ ማድረጉ እንዲሁም ለዩኒየኑ ኮምባይነሮች እና ትራክተሮች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አለመሆን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በስልጤ ዞን ላንፉሮ ወረዳ የሚገኘው ‹‹ጦራ አራቱ›› ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር በ1991 ዓ/ም ተመሰረተ፡፡ በ76 አባላት እና በ66 ሺህ ብር ካፒታል የተቋቋመው ማህበር አሁን ላይ የአባላቱን ቁጥር ወደ 3 ሺህ 52 አድርሷል። የካፒታል መጠኑም ኦዲት ላይ ካለው ውጪ ከ 3 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ብር በላይ ደርሷል፡፡
አቶ መሐመድ አሸቦ የጦራ አራቱ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ መሊቅ የስልጤ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ለአባል ህብረት ሥራ ማህበራት የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው ማህበራቸው ከአባላት የገዛውን ምርት ለዩኒየን በማስረከብ ዩኒየኑ ደግሞ ምርቱን በመሸጥ ከትርፉ 70 በመቶውን በስሩ ላሉ ማህበራት እንደሚያከፋፍል ያስረዳሉ፡፡
መሊቅ ዩኒየን የተለያዩ ግብአቶችን፣ የእርሻ መሳሪዎችን፣ ጸረ አረምና የፈንገስ መድሐኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለአርሶ አደሮች ያቀርባል፡፡ ከዩኒየኑ የሚቀርቡ ግብአቶች ደረጃቸውን የጠበቁና በዋጋም የተሻሉ በመሆናቸው አባላት ተጠቃሚዎች ናቸው። የዘር አቅርቦትን እንኳን ስናይ ከውጪ አንድ ኩንታል ምርጥ ዘር 3 ሺህ ብር የሚሸጥ ሲሆን ዩኒየኑ በ 1 ሺህ 7 መቶ ብር እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ እንዲጠቀምና ምርታማነትን እንዲያሳድግ ማህበራት መደገፍ አለባቸው የሚሉት አቶ መሐመድ÷ ማህበራት የአርሶ አደሩን ድህነት ለመቅረፍ የሚጫወቱት ሚና ቀላል ባለመሆኑ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ትብብሮቻቸውን ቢያጠናክሩ ከዚህ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብለዋል፡፡
‹‹ጎራ ቲቲ›› ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ይገኛል፡፡ በ1992 ዓ/ም ሲመሰረት 2 መቶ በሚሆኑ አባላት እና በ3 ሺህ ብር ካፒታል ነበር ሥራ የጀመረው። አሁን ላይ የአባላቱን ቁጥር ወደ 1ሺህ 5 መቶ ከፍ ያደረገ ሲሆን ካፒታሉንም ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡
አቶ ቃሲም የሱፍ የጉራ ቲቲ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ መሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ግብአቶች የማቅረብ ሥራ ይሰራል፡፡ ለአባላት ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የፍጆታ እቃዎች፣ መድሀኒትና ሌሎችንም በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል፡፡ በአካባቢው በዋናነት ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ በብዛት እንደሚመረት ገልጸው ማህበሩ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በአግባቡ ተረክቦ ለዩኒየኑ በማስረከብ ዩኒየኑ በመሸጥ ትርፉን በህጉ መሰረት ያከፋፈላል፡፡
የማህበሩ አባላት የተለያዩ ማሽነሪዎች ከዩኒየኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ይጠቀማሉ። ከዚህ በተጨማሪ ዩኒየኑ ብድር በማመቻቸት አባላት እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ አርሶ አደሩ ለብቻ ሆኖ ግብአት ማግኘትም ሆነ ምርትን መሸጥ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው ለብቻ ሆኖ ከመስራት ይልቅ በማህበር ተደራጅቶ መስራት ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮች የሚያመርቱት ምርት የተሻለ እንዲሆን ግብአት በማቅረብና ገበያ በማፈላለግ የሚሰሩ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለምና ሊበረታቱ ይገባል።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው