“አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ያጣሁት ነገር የለም” – አቶ ከፍያለሁ አሰፋ

“አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ያጣሁት ነገር የለም” – አቶ ከፍያለሁ አሰፋ

በገነት ደጉ

አካል ጉዳተኞች በማናቸውም የስራ መስኮች ተሰማርተው እራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የጀመሩባቸው ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

አሁን አሁን ከጠባቂነት ወጥተው እራሳቸው ሰርተው ሲለወጡ ማየት የተለመደ እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ያጣነው አንድ አካል መስራት የሚከለክለኝ አይደለም ሲሉም የደረሱበትን ስኬት ሲጠቅሱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ እኛም ለዚህ የዓይን እማኞች ሆነናል፡፡ የዛሬው የችያለው አምድም ባለታሪካችን የዚሁ ማሳያ ነውና አብራቹሁን ዝለቁ፡፡

አቶ ከፍያለሁ አሰፋ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በጌዴኦ ዞን፣ ገደብ ወረዳ ልዩ ስሙ ባንቆ ጐቲቲ ተብሎ በሚታወቀው ቀበሌ ነው፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በትውልድ አካባቢያቸው፣ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ተከታትለዋል፡፡

በልጅነት እድሜያቸው ወላጅ አባታቸውንና እናታቸውን በማጣታቸው ምክንያት ከ6ኛ ክፍል በላይ በትምህርታቸው ዘልቀው መሄድ አልቻሉም፡፡

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በተፈጥሮ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ከፍያለው አካባቢው ገጠር እና ለአካል ጉዳተኛ እምብዛም የሚመች ባለመሆኑ ባሳለፉት የህይወት ዘመን ውጣ ውረዱ በብዙ እንዳስቸገራቸው ያነሳሉ፡፡

ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ለትምህርት ቁሳቁስ እና ለአንዳንድ ነገሮች እንዲያግዛቸው ከነጋዴዎች በኪሎ ጨው ተረክበው በችርቻሮ አጣርተው በመሸጥ በትርፋ አንዳንድ ወጪያቸውን ይሸፍኑ ነበር፡፡

በጨው ንግድ ከስምንት ዓመታት በላይ እንዳሳለፉ የተናገሩት አቶ ከፍያለው ከዛሬ ነገ ያዋጣል ያሉትን ይህ ንግድ አላዋጣ ብሎ እያከሰራቸው ሲመጣ ወደ ሊስትሮ ስራ ገቡ፡፡

ምንም እንኳን አካል ጉዳተኛ ብሆንም ህይወት ትቀጥላለች የሚሉት አቶ ከፍያለሁ ዛሬ በልቶ ለማደር እና ነገን የተሻለ ለማድረግ ሌላ ዘዴ መዘየድ ግን ስላልቻሉ ነው የሊስትሮ ሥራ የጀመሩት፡፡

ትምህርታቸውን እየተማሩ ጎን ለጎን ለደብተርም ይሁን ለእስኪብርቶ መግዣ ሰዎችን ማስቸገር አለመፈለጋቸው እራስን ለመቻል መፍትሄው ከሰዎች ሳይሆን በራስ ቢሆን የተሻለ እና ጣዕም ያለው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በ1995 ዓ.ም ወደ ሊስትሮ ስራ መግባታቸውን የሚናገሩት አቶ ከፍያለው በስራ ከ20 ዓመታት በላይ መስራታቸውን ነው ያጫወቱን፡፡

ስራ ካለ በቀን ከ150 እስከ 200 ብር ድረስ እንደሚሰሩ ያጫወቱን ባለታሪካችን ገበያ ከሌለ ከ60 እስከ 80 ብር ድረስ እንደሚሰሩ በማንሳት የእለት ጉርስ እንደማያጡ ጠቅሰዋል፡፡

ባለትዳር እና የስድስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ከፍያለው ባለቤታቸው ጉዳት አልባ እንደሆኑና በእያንዳንዱ የህይወት ውጣ ውረዶች ሁሉ እንደሚያግዟቸው ያነሳሉ፡፡

ባለቤታቸው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ በመሸጥ ጐጇቸውን ለማቅናት እንደሚያግዟቸው ገልፀው ቤተሰቦቻቸው በአካል ጉዳት እየተቸገሩ በሰው ቤት ከሚንከራተቱ በማለት በገደብ ከተማ የመኖሪያ ቤት ስለሰጧቸው በኑሯቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ልጆች ገና ትምህርት ቤት እንዳልገቡ ያጫወቱን አቶ ከፍያለው አራቱን ልጆች ግን በተሻለ ትምህርት ቤት እያስተማሯአቸው መሆኑን ነው መንፈሰ ጠንካራው አቶ ከፍያለሁ የተናገሩት፡፡

የመካነኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ክረምት ሲሆን ዝናብ፣ በጋውንም ደግሞ ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው በማየቷ ላሜራ ቤት አሰርቶ በማበርከቷ ለሥራቸው እንዳገዛቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ቤተ-ክርስቲያኒቱንም በዚህ አጋጣሚ ላደረጉላቸው ድጋፍ ከልብ አመስግነዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ መሆን ከመኖር፣ ከማግባት እና ከመስራት እንዳላገዳቸው የሚናገሩት አቶ ከፍያለው አካል ጉዳተኛ መሆናቸው በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ከማንኛውም ማህበራዊ ጉዳዮች (ከእድር፣ እቁብ እና ከመሳሰሉት) ተግባራት እንዳላገዳቸው ይገልፃሉ፡፡

“እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ ብዬ የተፀፀትኩበት ወቅት የለም” የሚሉት አቶ ከፍያለሁ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ “የጎደለብኝ እና ያጣሁት ምንም ነገር የለም” በማለት ሰርቶ ለመለወጥ እንደሚጥሩ ገልፀዋል፡፡ እንደማንኛውም ሰው እራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ደፋ ቀና እያሉ ስለመሆናቸው ነው ያጫወቱን፡፡

ነገ የተሻለ ቀን ነው የሚሉት አቶ ከፍያለው ማንም ሰው ሊደርስ ከሚያስብበት ቦታ የማይደርስበት ምክንያት የለም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ”ልጆቼንም በጥሩ ትምህርት ቤት እያስተማርኳቸው ነው፡፡ ውጤታቸውም ጥሩ ነው” ሲሉ ልፋታቸው ከንቱ የሚያስቀሩ ልጆች እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

ወደፊት ከሊስትሮው ስራቸው ጎን ለጎን አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ከፍተው ለመስራት እቅድ አላቸው፡፡ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከሚያገኙት ገቢ ይቆጥባሉ፡፡

ዛሬ እዚህ ደረጃ ለመድረሳቸው ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ባለቤታቸው ስለመሆናቸው አንስተው ልጆችን ወልደው ከማሳደግ ጎን ለጎን በንግዱ ስራም ጠንካራ እንደሆኑ ነው የገለፁት።

የመጀመሪያ ልጃቸው የ12 ዓመት ልጅ ስትሆን ባለቤታቸውንም ይሁን እሳቸውን ከትምህርት ቤት መልስ ታግዛቸዋለች፡፡

ህብረተሰቡ አሁን ለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ቢሆንም ዛሬም ያልተሻሻሉ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው አንስተዋል፡፡

ወረዳው ሩቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አካል ጉዳተኞች ከመንግስትም ይሁን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምንም ዓይነት እገዛ እንዳልተደረገላቸው አጫውተውን ዛሬን ማየት መቻላቸው ከራስ ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ አካል ጉዳተኛ ልጅ አለኝ ብሎ አምኖ ከማውጣት አንፃር ሰፊ ጉድለቶች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ከፍያለው ለግንዛቤ መፍጠር ሥራ ትኩርት በመሥጠት ለመፍትሔው መሥራት ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የቡና እና የእንሰት ማሳ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ከፍያለው ተመላልሰው በማሰራት ተጠቃሚ እየሁኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ቡና እና ቆጮ ጨምሮ የሚያስፈልጋቸው ቀለብ ዓመቱን ሙሉ እንደማይገዙ ነው የተናገሩት፡፡

“አካል ጉዳተኞች ሰርተው የተለወጡ እና እራሳቸውን የቻሉ በርካቶች በመሆናቸው ሰርቶ ለመለወጥ መትጋት የዘወትር ተግባራችን ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክት አሰተላልፈዋል፡፡”

በተለይም በገጠሩ አካባቢ ቤተሰብም ይሁን እራሳቸው አካል ጉዳተኞች ልመናን እንደ ገቢ ማስገኛ የሚያዩ በርካቶች መሆናቸውን በማንሳትም መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

መንግስት እና የተራድኦ ድርጅቶች በአብዛኛው በከተማው አካባቢ ያሉትን አካል ጉዳተኞችን መደገፋቸው ጥሩ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜም ወደ ገጠሩ አካባቢ ጎራ በማለት ችግራችንን ለመቅረፍ የምናደርገውን ጥረት ቢያግዙ መልካም ነው በማለት ጠይቀዋል፡፡