የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ በጋሞ ዞን ጨንቻ ማረሚያ ተቋም የመስክ ምልከታ አደረገ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት ማሻሻያ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አባይነህ ከዳ እንደተናገሩት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታስቦ በውስን መሬት ላይ የጨንቻ ማረሚያ ተቋም እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በመስክ ምልክታቸው የጠበቁትን መሬት ላይ ማግኘታቸውን የገለፁት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በቀጣይ ተቋሙ ሥራውን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዲችል በቴክኒክም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የማረሚያ ተቋሙ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አጥናፉ አሰፋ በበኩላቸው በማረሚያው ተቋሙ ያሉ የህግ ታራሚዎች የኢኮኖሚ ባለቤት መሆን እንዲችሉ ሥራዎች በስፋት ይሰራሉ።
በዋናነትም በጓሮ አትክልት፣ በእንሰሳት እርባታ፣ በበግ ማሞከት፣ በከብት ድለባ ፣ በንብ ማነብ እና በእንጨትና ብረታብረት ሥራ በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው ብለዋል።
የመስክ ምልከታው ያሉብንን የተቋም ጥያቄዎች ከመመለስ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።
የህግ ታራሚ መታሰቢያ ከበደ ከአኘል ምርት አሰራር ጀምሮ በቂ ዕውቀት በተቋሙ መጨበጡን ገልፆ በጓሮ አትክልት ምርትም ሆነ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከብቶች እርባታ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንደጨበጠም አስረድቷል።
የእስር ጊዜውን ጨርሶ ሲወጣ በራስ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ መሰማራት እንዲችል አቅም የፈጠረለት መሆኑን ተናግሯል ።
ሌላኛው የህግ ታራሚ ጌታሁን አንጁሎ በበኩሉ የእስር ጊዜአችንን ጨርሰን ወደ ማህረሰቡ ስንቀላቀል ሥራ መስራት እንድንችል ተቋሙ አቅም ፈጥሮልናል ብሏል።
መሀመድ ሸጎ ታራሚ ሲሆን በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በማረሚያ ተቋሙ በኩል እስከ ደረጃ አራት መማሩን ተናግሯል።
በተቋሙ አሁን ላይ የእንጨት ሥራ እየሰራ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ጠቁሞ በቀጣይም ማህበረሰቡን ለመካስ እንደሚሰራ ገልጿል።
ዘጋቢ ፡ ታምሩ በልሁ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ