በቴፒ ከተማ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የሐይማኖት አባቶች ከመንግስት ጋር በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ

በቴፒ ከተማ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የሐይማኖት አባቶች ከመንግስት ጋር በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ

ሀዋሳ፡ ጥር 28/2016 ዓ.2016 (ደሬቴድ) በቴፒ ከተማ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የሐይማኖት አባቶች ከመንግስት ጋር በትኩረት እንዲሰሩ ተጠይቋል።

የቴፒ ከተማ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቴፒ ከተማ መክሯል።

የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮሐንስ በንዲ በመክፈቻ ንግግራቸው የሐይማኖት አባቶች ምዕመናንን በመልካም ሥነ ምግባር ከመቅረፅ ባለፈ በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በማረቅ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዘላቂ ሠላም ይረጋገጥ ዘንድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይ በቴፒ ከተማ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የሐይማኖት አባቶች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የቴፒ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሐፊ አቶ ሳሙኤል ቶከኖ ለጉባኤው መወያያ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሐይማኖቶችና የተለያዩ ባህል ባለቤት ብትሆንም ህዝባቿ እነዚህ ልዩነቶች ሳይገድባቸው በአንድነት፣ በፍቅርና በሠላም ተከባብረው የሚኖርባት ከተማ ናት ብለዋል።

የቴፒ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሰይድ አህመድ በበኩላቸው የሐይማኖት አባቶችም ሆነ የእምነት ተከታዮች በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸዉ ሠላምን መፍጠርና በጎ ነገርን ማድረግ በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ እንዳለው ተናግረዋል።

አክለውም አሁን ላይ እንደ ሀገር በየአካባቢው የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተቀራርበን ልንወያይ ይገባል ብለዋል።

አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ስለሠላም ለመወያየት መድረክ በመዘጋጀቱ አመስግነው ይህም እስከታችኛው መዋቅር ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።

የሠላሙ ባለቤት እኛው ነን ያሉት ተሳታፊዎቹ በቀጣይም ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀው በሐይማኖትና በብሔር ካባ ግጭት ለመፍጠር አልመው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ግለሰቦችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ አንስተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ለአንዳንድ የሐይማኖት ተቋማት የአምልኮ ሥፍራ፣ የቀብር ቦታ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

የቴፒ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሪኩ የርማሮ የሐይማኖት ተቋማት እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት የቀብር ሥፍራ ተለይቶ የወሰን ማስከበርና የንብረት ካሳ ክፍያ እንዲፈፀም ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።

በተያያዘም ወደ ቀብር ቦታ መሄጃ መንገድ ከፈታ ሥራ ለማከናወን ቦታው ተለክቶ የወሰን ማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በቅርቡ የካሳ ክፍያ ተፈፅሞ ርክክብ እንዲደረግ ይሰራልም ብለዋል።

የቴፒ ከተማ ሠላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ አዝመራው በመቋጫው እንደገለፁት በሐይማኖት ተቋማት ውስጥም ሆነ ከሐይማኖት ተቋማት ውጭ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል በማስተማርና በመገሰፅ የሐይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ጌትነት ገረመዉ – ከማሻ ቅርንጫፍ