ወጣቶችን በተለያዩ የስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች በማሰማራት ላይ የሚታየው ውስንነት ሊቀረፍ ይገባል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ

ወጣቶችን በተለያዩ የስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች በማሰማራት ላይ የሚታየው ውስንነት ሊቀረፍ ይገባል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ

ሀዋሳ፡ ጥር 28/2016 ዓ.2016 (ደሬቴድ) ወጣቶችን በተለያዩ የስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች በማሰማራት ላይ የሚታየው ውስንነት ሊቀረፍ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የክልሉን የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

ኢንተርፕራይዝ ቢሮው ለቋሚ ኮሚቴው የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከቅንጅታዊ ስራና ተግባርን ወርዶ ከመገምገም አኳያ ውስንነት መኖሩን አንስቷል።

እንደዚሁም የገጠር ስራ እድል ፈጠራና በጊዜ ወደ ስራ እንዲገቡ የብድር አቅርቦት ከማመቻቸትና አመላለስን ከመከታተል ረገድ ችግር መኖሩን ያነሱት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ዘርፉን በይበልጥ ውጤታማ ከማድረግ አኳያ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ገምግመዋል።

የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ሀላፊ ተወካይና የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ሀላፊ አቶ በለጠ ሙንኤ ለተጠየቁ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ከብድር ስርጭት ጋር ተያይዞ አፈጻጸሙን ለማስተካከል ጥረት መደረግ እንዳለበትና የገጠር መሬት አቅርቦቱ ላይም ሰፊ ክፍተት በመኖሩ በሚቀረፍ መልኩ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸው አደራጅ ባለሙያን ጨምሮ የሚታየውን የሰው ሀይል ውስንነት በቅርቡ ለማሟላት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በምክር ቤቱ የፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተደደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሀንስ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ በጥንካሬ የታዩ አፈጻጸሞችን አድንቀው በቋሚና ጊዚያዊ ስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች ውስንነት በመኖሩ ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም በገጠር ያለው ስራ እድል ፈጠራ የምርታማነትን ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

ተቋሙን ከማደራጀት ባለፈ የወጣቶች ስብእና ግንባታ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ያሉት አቶ እንቁ ታችኛው መዋቅር ላይ ወርዶ ከመገምገም አኳያ ሰፊ ጉድለት በመኖሩ የተጠናከረ ስራ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን